በኢስዋቲኒ ፖሊሶች ነርሶች ላይ በመተኮሳቸው ነርሶች ፖሊሶችን አናክምም አሉ

ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በኢስዋቲኒ የሚገኙ ነርሶች ባሳለፍነው ረቡዕ በአገሪቱ ተካሂዶ በነበረው ሰልፍ ወቅት ፖሊሶች ነርሶች ላይ ተኩሰው ነበር በማለት ለፖሊሶች እርዳታ አናደርግም ብለዋል።

በአፍሪካ ሙሉ በሙሉ በንጉሣዊ አስተዳደር የምትመራ ብቸኛዋ አገር የሆነቸው ኢስዋቲኒ ከባለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ በተቃውሞ እየተናጠች ነው። አገሪቱ ስሟን ከስዋዚላንድ ወደ ኢስዋቲኒ መቀየሯ የሚታወስ ነው።

በያዝነው ሳምንት የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎም እንደ ፌስቡክ ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎችና እንዳንድ የኢንተርኔት አገልግሎቶች በአገሪቱ እንዲቋረጡ ተደርጓል።

መንግሥት የፀጥታ አካላት ምንም አይነት የሚተኮስ መሣሪያ አልተጠቀሙም ያለ ሲሆን፤ በመላው አገሪቱም የተቃውሞ ሰልፎችን ከልክሏል።

"ነርሶች ላይ ስለመተኮሱ ምንም የደረሰን መረጃ የለም" ብለዋል የመንግሥት ቃል አቀባዩ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር አድርገውት በነበረው ቆይታ።

"ፖለሶች በየጎዳናው የተሰማሩት ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር ነው። ዝም ብሎ የሚተኩስ የፀጥታ ኃይል የለም" ብለዋል።

ቃል አቀባዩ አክለውም ኢስዋቲኒ በሰላም እና በንግግር ላይ የተመሠረተች አገር ነች ብለዋል።

ትናንት አርብ ዕለት በሦስት ሆስፒታሎች የሚገኙ የአገሪቱ ነርሶች አመጽ ላይ ናቸው የሚሉ ዘገባዎች ወጥተዋል።

በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ የጤና ባለሙያዎች እና ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ለመጠየቅ ያሰባሰቡትን ፊርማቸውን ለፓርላማ ለማስገባት በሚሄዱበት ወቅት በኃይል የተሞላ ምላሽ እንደጠበቃቸው የአገሪቱ የነርሶች ሕብረት አስታውቋል።

በወቅቱም 30 ነርሶች ጉዳት እንደደረሰባቸውና ጥቃቱን የፈጸመውም የአገሪቱ ፖሊስ መሆኑን ገልጿል። አክሎም አንድ ታዳጊ መንገደኛ ሕይወቱ አልፋለች ብሏል።

ይህንን ተከትሎም ሕብረቱ በነርሶቹ ላይ በደረሰው ጉዳት ምክንያት ሌሎች ነርሶች የፖሊስ አባላትን እንዳያክሙ ጥሪውን አስተላልፏል።

የሕብረቱ ፕሬዝዳንት ዌልከም ምዱሊ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ውሳኔው ከሥራቸው ሥነ ምግባር ውጪ መሆኑን ቢያውቁም ነርሶቹ ግን በአሁኑ ሰዓት ፖሊሶች ጥቃት እንዳይፈጽሙባቸው ይፈራሉ ብለዋል።

"ሆስፒታል ውስጥ ፖሊሶች የጤና ባለሙያዎች ላይ እንደተኮሱባቸው ሪፖርቶች ደርሰውናል። በጣም ነው እየፈራን ያለነው" ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።

አክለውለም ነርሶቹ ወደ ሥራ ገበታቸው ከመመለሳቸው በፊት የአገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ከሥራቸው እንደማይነሱ ሊያረጋግጥ ይገባል ብለዋል።

በኢስዋቲኒ የተከሰተውን ተቃውሞ ተከትሎ የአካካባቢው አገራት ጥምረት የሆነው የደቡባዊ አፍሪካ የእድገት ቀጠና ልዑካን ከንጉሥ ምስዋቲሦሶስተኛ ጋር ውይይት እያካሄዱ ነው።

የጤና ባለሙያዎቹ ከዚህ ቀደም የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎች ይደረጉ እንዲሁም የራሳችንን መሪዎች እንምረጥ በሚል ተማሪዎችና የትራንስፖርት አቅራቢዎች የጀመሩትን ተቃውሞ ተከትለው ነው ጥያቄያቸውን ማቅረብ የጀመሩት።

በዓለም ባንክ መረጃ መሠረት ኢስዋቲኒ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች ነው የሚኖረው።