ዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ-19 ከ80 እስከ 180 ሺህ የሚደርሱ የጤና ሠራተኞችን ሳይገድል አይቀርም አለ

የኮቪድ ሕመምተኛ እና ታካሚ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የጤና ሠራተኞችን ክፉኛ መጎዳቱንና ከ80,000 እስከ 180,000 የሚደርሱትን ግድሎ ሊሆን እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

የጤና ሠራተኞች ለክትባት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ያሉት የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም፤ የክትባቱን ኢፍትሃዊ ስርጭትን ተችተዋል።

ሞቱ የተመዘገበው በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ከጥር 2020 እስከ ግንቦት ባለው ጊዜ ነው።

ቀደም ሲል ሌላ ከፍተኛ የዓለም ጤና ድርጅት ባለሥልጣን የክትባት እጥረት ወረርሽኙ እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ ሊያስቀጥለው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

በዓለም ዙሪያ 135 ሚሊዮን የጤና ሠራተኞች እንዳሉ ይገመታል።

"ከ 119 አገራት የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአምስት የጤና ሠራተኞች በአማካይ ሁለቱ ሙሉ በሙሉ ክትባት አግኝተዋል" ብለዋል ዶ/ር ቴድሮስ።

"ይህ ቁጥር በተለያዩ አገራት እና በኢኮኖሚ ቡድኖች ውስጥ ያለውን ትልቅ ልዩነት ይሸፍናል።"

በአፍሪካ ውስጥ ከ10 የጤና ሠራተኞች መካከል አንዱ ብቻ ሙሉ በሙሉ ክትባት ሲወስድ ከፍተኛ ገቢ ባላቸው አገራት ስምንቱ ተከትበዋል።

ቀደም ሲል ለድሃ አገራት በቂ ክትባት አለመስጠቱ የኮቪድ-19 ቀውስ "በቀላሉ ወደ 2022 ሊጎትት ይችላል" ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊ ዶ/ር ብሩስ አይልዋርድ ገልጸዋል።

በአብዛኛዎቹ አህጉራት 40 በመቶ ሰዎች ክትባት ሲያገኙ ይህ ቁጥር በአፍሪካ ከአምስት በመቶ በታች ነው።

አብዛኛው የኮቪድ-19 ክትባት ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ወይም በከፍተኛ መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ጥቅም ላይ ውሏል። አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተሰጡት ክትባቶች 2.6 በመቶውን ብቻ ትይዛለች።

ክትባቶችን በፍትሃዊነት ለማሰራጨት በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው ዓለም አቀፍ ፕሮግራም የሆነው የኮቫክስ የመጀመሪያው ሃሳብ ሃብታሞቹን ጨምሮ ሁሉም አገራት ከአንድ ማዕከል ክትባቶችን ማግኘት መቻላቸውን ለማረጋገጥ እንደነበር የቢቢሲ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዘጋቢ ኑሃሚን ግሪምሌይ ጽፋለች።

ነገር ግን አብዛኛዎቹ የቡድን 7 አገራት ከአምራቾች ጋር የራሳቸውን አንድ ለአንድ ስምምነት ማድረግ ከጀመሩ በኋላ ከስምምነቱ ወደ ኋላ ለመመለስ ወሰኑ።

የመድኃኒት አምራቾች ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አገራት ቅድሚያ እንዲሰጡ ሃብታም አገራት በክትባት ለመግዛት ያላቸውን ወረፋ እንዲተው ዶ/ር አይልዋርድ ጥሪ አቅርበዋል።

"በትክክለኛ በመንገድ ላይ እንዳሆንን ልንናገር እችላለሁ። በእርግጥ ማፋጠን አለብን። ካልሆነ ግን ምን እንደሚፈጠር ያውቃሉ? ይህ ወረርሽኝ ከሚያስፈልገው በላይ ለአንድ ዓመት ያህል ይቀጥላል" ብለዋል።

ዘ ፒፕልስ ቫክሲን የተባለው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሕብረት በመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች እና በሃብታም አገራት ቃል ከተገባው ከሰባት ክትባት አንዱ ለድሃ አገራት እየደረሰ መሆኑን የሚጠቁሙ አዳዲስ አሃዞችን አውጥቷል።

ኦክስፋምን እና ዩኤንኤድስን ያካተተው ሕብረት በኮቫክስ በኩል ለራሳቸው ሕዝብ ክትባቶችን እየገዙ ነው በሚል ካናዳ እና እንግሊዝን ነቅፈዋል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ዩናይትድ ኪንግደም 539,370 የፋይዘር ክትባቶችን ከኮቫክስ የተቀበለች ሲሆን ካናዳ ከአንድ ሚሊዮን ገደማ የአስትራዜኔካ ክትባት ወስዳለች።

ኮቫክስ በመጀመሪያ በዚህ ዓመት መጨረሻ ሁለት ቢሊዮን ክትባቶችን ለማድረስ ቢያቅድም እስካሁን ያሳካው 371 ሚሊዮን ብቻ ነው።