በምዕራብ አፍሪካ የአይኤስ መሪ መገደሉን ናይጄሪያ አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, BOKO HARAM VIDEO
የናይጄሪያ ጦር ኃይል በምዕራባዊ አፍሪካ የኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ክንፍ ቡድን መሪ የሆነው አቡ ሙሳብ አል-ባርናዊ መገደሉን ይፋ አደረገ።
"እሱ ሞቷል እንደሞተም ይቀራል" ብለዋል የጦር ኃይሉ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጄኔራል ላኪ ኢራቦር።
ጄኔራሉ ስለ ባርናዊ መገደል ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ቢቆጠቡም ባለፈው ወር ተገድሏል የሚሉ ዜናዎች ሲሰሙ ነበር።
ኢስዋፕ በመባል የሚታወቀው የኢስላሚክ ስቴት የምዕራብ አፍሪካ ክንፍ እስካሁን ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጠም።
የቦኮ ሐራም መሪ አቡባከር ሼካዎ መገደሉን ተከትሎ ኢስዋፕ ናይጄሪያ ውስጥ ጠንካራው አክራሪ ታጣቂ ቡድን ይሆናል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።
ከአቡበከር መገደል በኋላ በርካታ የቦኮ ሐራም ታጣቂዎች ለጦር ኃይሉና ለኢስዋፕ እጃቸውን ሰጥተዋል።
ባርናዊ ማነው?
ስለ ባርናዊ ዕድሜም ሆነ ገጽታ የሚታወቀው በጣም ጥቂት ነው።
የትውልድ ስሙ ሃቢብ ዩሱፍ ሲሆን የቦኮ ሐራም መሥራች ሞሐመድ ዩሱፍ ታላቅ ልጅ እንደሆነ ነው የሚታመነው።
እንደ ቦኮ ሐራም ሕፃናትን ለአጥፍቶ መጥፋታ የማይጠቀምና ሙስሊሞችን ለይቶ አለማጥቃትን የመሳሰሉ መርህዎች ስለሚከተል በተነፃፃሪ ቡድኑ አክራሪ ያልሆነ ተደርጎ ይወሰዳል።
በፈረንጆቹ 2009 አባቱ በፖሊስ እጅ ሳሉ መሞታቸውን ተከትሎ አቡበከር የቦኮ ሐራም መሪ ሆኖ ተሾመ።
በወቅቱ ባርናዊ የቦኮ ሐራም ቃል አቀባይ ሆኖ ያገለግል ነበር። ነገር ግን ከአቡበከር ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ቦኮ ሐራምን ጥሎ ከአል-ቃዒዳ ጋር ግንኙት ወዳለው ቡድን አመራ።
ምንም እንኳ ሁለቱ ቡድኖች ልዩነቾች ቢኖሯቸውም ብዙ ጊዜ አብረው ይሠሩ ነበር።
የቦኮ ሐራም ዓለም አቀፍ ዝና ይገዘፍ ዘንድ በፈረንጆቹ 2015 አቡበከር ከአይኤስ ጋር አብሮ ለመሥራት ወሰነ። በቀጣዩ ዓመት አይኤስ ባርናዊን የቦኮ ሐራም ዋሊ [በአረብኛ ገዥ እንደማለት ነው] አድርጎ ሾመ።
ነገር ግን ይህ ሹመት ውስጣዊ መከፋፈልን ይዞ መጣ።
የአይኤስ ጋዜጣ የሆነው አል-ናባ ከባርናዊ ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ነሐሴ 2016 ይዞ ወጣ። ባርናዊ በጋዜጣው ላይ በመስጅዶችና በገበያ ቦታዎች ላይ ለይቶ ጥቃት የመሰንዘሩ ስትራቴጂውን አንደሚያቋርጥ አስታወቀ።
ይሄኔ አቡበከር፤ ከሥልጣኑ ለማስወገድ ሴራ ጠንስሶብኛል ሲል ባርናዊን ከሰሰ።
ይህንን ውስጣዊ ክፍፍል ተከትሎ የኢስላሚክ ስቴት ታማኞች የነበሩ ሰዎች ኢስዋፕን ተቀላቀሉ። መሪያቸውም ባርናዊ ሆነ። አቡበከር ደግሞ የቦኮ ሐራም መሪነቱን ተቆናጠጠ።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሁሉቱ ቡድኖች ባላንጣ ሆነው ቆይተዋል።
ኢስዋፕ ባለፈው ግንቦት አቡበከር የሞተው ከኢስዋፕ ጋር በነበረው ጦርነት ምክንያት ነው ሲል መግለጫ አወጥቷል።
በዚያው ወር መጨረሻ ቦኮ ሐራም አቡበከር ሼካዎ መሞቱን የሚያረጋግጥ የተንቀሳቃሽ ምስል ለቀው በበርካታ የናይጄሪያ የዜና አውታሮች ታየ።
አይኤስም የአቡበከርን ሞት ይፋ ካደረገ በኋላ "በሺዎች የሚቆጠሩ" የቦኮ ሐራም ታጣቂዎች ኢስዋፕን እየተቀላቀሉ ነው አለ።
ኢስዋፕ በባርናዊ አገዛዝ ስር እያለ በሰሜናዊ ናይጄሪያ እንዲሁም በቻድ ሸለቆ ባደረሰው ጥቃት ቦታዎችን መቆጣጠር ችሎ ነበር።
ቡድኑ በቡርኪና ፋሶ፣ ካሜሩን፣ ኒጀርና ማሊም እንቅስቃሴ ያደርጋል።
ቡድኑ ከበርካታ ጦር ኃይሎች መሣሪያ ነጥቆ አከማችቷል። አልፎም በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ሥፍራዎች የሚኖሩ ሰዎች ግብር እንዲከፍሉ በማድረግ ዓሣ በማጥመድ በመሳሰሉ የንግድ መስኮ በመሠማራት ኪሱን አደልቧል።












