ህወሓት የከፈተው ጦርነት በሁሉም ግንባሮች እየተካሄደ ነው፦ መከላከያ ሚኒስቴር

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ከቀናት በፊት እንደ አዲስ ተጠናክሮ ቀጥሏል የተባለውን ጦርነት የከፈተው የህወሓት አማጺ ቡድን ነው አለ።
የመከላከያ ሚኒስቴር ሐሙስ ምሽት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው አማጺው ህወሓት በሁሉም ግንባሮች ከሰኞ ጀምሮ ውጊያ በከፈተባቸው ግንባሮች ከባድ ጉዳት እየደረሰበት ነው ሲል ገልጿል።
መከላከያ ሚንስቴር በመግለጫው "በጀመሩት ውጊያ አይቀጡ ቅጣት እየደረሰባቸው ይገኛል" ብሏል።
ባለፈው ሰኞ የኢትዮጵያ ፌደራል ሠራዊት በሁሉም ግንባሮች የተቀናጀ ጥቃት መክፈቱን እና ዓለም አቀፉ ማኅረሰብ ይህንን እርምጃ እንዲያውግዝ የሚጠይቅ መግለጫ አማጺያኑ አውጥተው ነበር።
ህወሓት በኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች እየተሰነዘረበት ያለው ጥቃት "በከባድ ጦር መሳሪያ፣ በታንክ፣ በሮኬቶች፣ በድሮኖች እና በተዋጊ ጀቶች" የታገዘ እንደሆነ በመግለጫው አመልክቶ ነበር።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ማብቂያ ላይ የመንግሥት ሠራዊት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ ጦርነቱ ወደ አጎራባቾቹ የአፋርና የአማራ ክልል መስፋፋቱ ይታወቃል።
የፌደራሉ ጦር፣ የአማራ እና አፋር ኃይሎች ከተለያዩ ክልሎች ከተውጣጡ የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ከህወሓት አማጺያን ጋር ተከታታይ ውጊያዎች ሲያደርጉ ቆይተው፣ ጦርነቱ ለሳምንታት ጋብ ብሎ ከቆየ በኋላ ዳግም ተቀስቅሷል።
ህወሓት ከባድ ጥቃት እንደተከፈተበት ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ጀምሮ በቃል አቀባዩ በኩል ለዓለም አቀፍ ዜና ወኪሎች ሲናገር የቆየ ሲሆን ሰኞ ዕለትም መግለጫ አውጥቶ ነበር።
መንግሥት በበኩሉ አዲስ ተከፈተ ስለተባለው ጦርነት መግለጫ ሲሰጥ ይህ የሐሙሱ ምሽት የመከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ የመጀመሪያው ነው።
ቀደም ባለው የአማጺው ጥቃት "የጅቡቲን መስመር ለመቁረጥና ወልቃይት ጠገዴን በማጥቃት በሱዳን በኩል ኮሪደር ለማስከፈት" የሚል ዓላማ ይዞ ተደጋጋሚ መጠነ ሰፊ ማጥቃት መፈጸሙንና "በሁለት ሳምንት አዲስ አበባ ለመግባት" በሚል በሰሜን ወሎ በኩል ሙከራ ያደረገው ሙከራ አለመሳካቱንና "እጅግ ከባድ ኪሳራ" ደርሶባታል ብሏል መከላከያ ሚኒስቴር።
መግለጫው ጨምሮም ህወሓት ከቀናት በፊት በሁሉም ግንባሮች ውጊያ ከፍቶ ሌ/ጀ ጻድቃን " …ጦርነቱን እናሳጥረዋለን፣ በሁለት ሳምንት አዲስ አበባ እንገባለን ፤ ፖለቲካዊ ፣ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ሁኔታን እንቀይራለን …" በሚል ጦርነት አውጆ እየተካሄደ ይገኛል ብሏል።
የህወሓት ኃይሎች አዛዥ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ጄነራል ጻድቃን በዚህ ሳምንት ለኒው ዮርክ ታይምስ እንደተናገሩት "ጠላት ለወራት ሲዘጋጅ ነበር እኛም ተዘጋጅተናል" በማለት የሚካሄደው ውጊያ የቀናት ወይም የሳምንታት ጊዜ የሚወስድ እንጂ የተራዘመ እንደማይሆን ገልጸው፤ በውጤቱም ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ተጽእኖ ይኖረዋል ብለዋል።
የመከላከያ ሚኒስቴር እንዳለው ከቀናት በፊት በተጀመረው ጦርነት የህወሓት ኃይሎች በአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት እና በሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጥምረት ከባድ ጉዳት እየደረሰበት መሆኑን ገልጿል።
ህወሓት ጥቃት እንደተከፈተበት መግለጹን ተከትሎ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ማብራሪያ ተጠይቀው የነበሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ በየትኛውም ክፍል ከሚፈጸም የሽብር ድርጊት ዜጎቹን የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረው ነበር።
ጨምረውም "መንግሥት በህወሓት አማካይነት በአማራ ክልልም ሆነ በየትኛውም ቦታ የሚፈጸሙ ውድመቶችን፣ ጥቃቶችንና ግድያዎችን መከላከሉን ይቀጥላል" በማለት አብራርተዋል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ሳምንታት የቀሩት ሲሆን ጦርነቱ ከትግራይ ባሻገር በአማራና በአፋር ክልሎች እየተካሄደ ይገኛል።
በጦርነቱ የሞቱ ሰዎች አሃዝ በትክክል ባይታወቅም በሺህዎች ሊሆኑ እንደሚችል ይገመታል። በተጨማሪም በጦርነቱ ሰበብ በሰሜን ኢትዮጵያ ሚሊዮኖች የእርዳታ ድጋፍ ለመጠበቅ የተገደዱ ሲሆን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩት ደግሞ በረሃብ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።













