ኢትዮጵያ የተመድ ሠራተኞችን በተመለከተ ጽፌያለሁ ላለችው ደብዳቤ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ማስረጃ ጠየቁ

የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በኢትዮጵያ ተቀማጭነታቸውን አድርገው የነበሩ ሰባት የድርጅቱ ከፍተኛ ሠራተኞች ከአገር እንዲወጡ ለተደረጉበት ክሶች ማስረጃ እንዲቀርብላቸው ጠየቁ።

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ይህንን የጠየቁት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ትግራይ ጉዳይ ላይ ባደረገው ሁለተኛው ክፍት ስብሰባ ወቅት፣ በተመድ የኢትዮጵያ ልዑክ የሆኑት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ለድርጅቱ ደብዳቤ መላኩን መጥቀሳቸውን ተከትሎ ነው።

ሰባቱ የተመድ ሠራተኞች አገር ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ከመሰጠቱ አስቀድሞ፤ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን ባለፈው ሐምሌ ላይ ለመንግሥታቱ ድርጅት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ልከው እንደነበር አምባሳደሩ በዚህ ወቅት ተናግረዋል።

"አንዳንዶቹን ሠራተኞች ጠርተን ያልተገባ ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ አስጠንቅቀናል። ነገር ግን በድርጊቱ ቀጥለውበታል" ሲሉ በፀጥታው ምክር ቤት ተናግረዋል።

የአምባሳደር ታዬን ንግግር ተከትሎ የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ አምባሳደሩ ባቀረቡት ንግግር ላይ ምላሽ ለመስጠት ጠይቀዋል።

"የኢትዮጵያ መንግሥት የተመድ ሠራተኞችን ሊያባርር እንደሆነ የሚገልጽ ደብዳቤ ጽፎ ለየትኛውም የተመድ ቅርንጫፍ ድርጅት አስገብቶ ከሆነ የደብዳቤው ቅጂ እንዲሰጠኝ እጠይቃለሁ። ከዚህ በፊት አንዳችም ደብዳቤ አልደረሰኝም" ሲሉ ዋና ፀሐፊው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ከአንዴም ሁለቴ የተመድ ሠራተኞች "ወገንተኛ ናቸው" የሚል ቅሬታ አቅርበው ማስረጃ እንዲያቀርቡ ተጠይቆ ምላሽ አልተገኘም ሲሉ አምባሳደር ታዬ ላሰሙት ንግግር፤ ዋና ጸሐፊው ጉቴሬዝ ማስረጃ ጠይቀዋል።

"የተባበሩት መንግሥታትን ክብር መጠበቅ ግዴታዬ ነው" በማለት ለሪፖርተሮች አንቶዮ ጉቴሬዝ ተናግረዋል።

አምባሳደር ታዬ በትናንትናው ዕለት ለምክር ቤቱ የተባረሩት የተመድ ሠራተኞችን መረጃን በመፍጠር፣ በሐሰት ረሃብ የጦርነት መሳሪያ ተደርጓል በማለት፣ ሰዎች በረሃብ ሞተዋል የሚሉና የመንግሥት "ጠላት" የሆነውን ህወሓትን በመደገፍ ወንጅለዋቸዋል።

ዋና ፀሐፊው በበኩላቸው ለምክር ቤቱ ምላሽ በሰጡበት ወቅት እነዚህ የተባሉ ክሶችን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ምንም መረጃ አልሰማሁም ብለዋል።

የተባበበሩት መንግሥታት ሠራተኞች ገለልተኝነት ላይ የሚያሳስብ ነገር ካለ መረጃ እንዲሰጧቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ቢጠይቁም ምላሽ አላገኘሁም ብለዋል።

"ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግን እየጣሰች ነው ብለን እናምናለን። ሰባቱን የተመድ ሠራተኞች የማባረር ሥልጣን የላትም። የኢትዮጵያ መንግሥት አንዳንድ የተመድ ሠራተኞች ወገንተኛ ናቸው ወይም የሰብአዊ እርዳታ መርህን ጥሰዋል ብሎ የሚያምን ከሆነ ከመንግሥት ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ ነን" በማለት ጉቴሬዝ አብራርተዋል።

አምባሳደር ታዬ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ስለ ውሳኔዎቿ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ የመስጠት ሕጋዊ ግዴታ እንደሌለባት አስረድተዋል።

"ኢትዮጵያ ያባረረቻቸው የተመድ ሠራተኞች የሙያ ሥነ ምግባራቸውን ገሸሽ አድርገው ተገኝተዋል። የሰብአዊ እርዳታ መርህንም ጥሰዋል" ሲሉም ተናግረዋል።

ጥቂት የተመድ ሠራተኞች "ሙያዊ ሥነ ምግባር መጣሳቸው" አጠቃላይ የድርጅቱን አሠራር እንደማይወክል አምባሳደር ታዬ ገልጸው፤ "ሆኖም ግን ባለፉት 11 ወራት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለነበረው ሰብአዊ ድጋፍ ጥያቄ ያጭራል" ብለዋል።

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሰባት የድርጅቱ ሠራተኞች ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እንዲወጡ መደረጋቸውን ተችተው ሕይወትን በማዳን ላይ ትኩረት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

"እንዲህ ከፍተኛ ቀውስ ባለበት ወቅት ሁሉም ጥረቶች ሕይወትን ማዳንና ሊከተል የሚችለውን ሰቆቃ ማስቀረት ላይ ማተኮር አለባቸው" በማለት ዋና ጸሐፊው አፅንኦት ሰጥተዋል።

በትናንትናው ዕለት "ፒስ ኤንድ ሰኪውሪቲ ኢን አፍሪካ" በሚል የውይይት አጀንዳ ስር በትግራይ ክልል ተከስቶ በአጎራባቾቹ የአፋር እና የአማራ ክልሎች የተዛመተውን ጦርነትና ያስከተለውን ቀውስ በተመለከተ በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውይይት ተደርጓል።

በተለይም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከተከሰተው ቀውስ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በጣልቃ ገብነት፣ በወገንተኝነትና እንዲሁም ለብሔራዊ ደኅንነት ሰጋት ደቅነዋል በማለት የተመድ ሰባት ሠራተኞች ከአገር እንዲወጡ መደረጋቸው በምክር ቤቱ ሰፊውን ሰዓት ሸፍኖ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) የኢትዮጵያ ተወካይ አደል ኾደርን ጨምሮ ከአገር እንዲወጡ የታዘዙት ከፍተኛ የተመድ ሠራተኞች ከሰሞኑ አገሪቱን ለቀው ወጥተዋል።

"ታይቶ የማያውቅ መባረር"

አብዛኛዎቹ የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች ናቸው የተባሉት የተመድ ሠራተኞች መባረርን አስመልክቶ ዋና ፀሐፊው "የሚረብሽ ነው" ሲሉ ለፀጥታው ምክር ቤት አምባሳደሮች ተናግረዋል።

"ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ መባረር ነው" በማለት አሳሳቢነቱን የገለጹት ዋና ጸሐፊው ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ በተባበሩት መንግሥታት እና በአባል አገራቱ መካከል ካለው መሠረታዊ ግንኙነት ጋር ስለሚዛመድ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት መስከረም 20/2014 ዓ. ም ያሳለፈውን ውሳኔም አስመልክቶ፤ ተመድ ለኢትዮጵያ በጻፈው ደብዳቤ ሠራተኞቹ ያላቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥበቃ (ዲፕሎማቲክ ኢሙዩኒቲ) ተቀባይነት እንደሌለው (ፐርሶና ናን ግራታ) እና ግዛቲቷን ለቀው እንዲወጡ መጠየቁ በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር መሠረት ከአንድ አገር ግዴታ ጋር የማይጣጣም ነው ብለዋል።

ለተመድ ተቀጥረው የሚሠሩ ግለሰቦችን በሚመለከት መንግሥታት የተለየ ጉዳይ ካጋጠማቸው ሂደቱ በሚያዘው መሠረት ለተባበሩት መንግሥታት ማሳወቅ አለባቸው ብለዋል። ይህም ዋና ፀሐፊው አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ እርምጃ እንዲወስዱ እንደሚያስችል ቻርተሩን ዋቢ በማድረግ ጠቅሰዋል።

"በሌላ አነጋገር ትክክለኛ፣ መደበኛ አሠራር እና ሂደትን አልተከተለም" ብለዋል አንቶኒዮ ጉቴሬዝ።

የመንግሥታቱ ድርጅት በኢትዮጵያ ያለው አንድ አጀንዳ ብቻ ነው ያሉት ዋና ጸሐፊው ይህ አጀንዳም "የትግራይ፣ የአማራ፣ የአፋር፣ እና የሶማሊ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ናቸው" ብለዋል።

"የኢትዮጵያ ሕዝቦች እየተሰቃዩ ነው። ይህንን ሰቆቃ ከማስቀም ውጪ ሌላ አላማ የለንም" ሲሉም አክለዋል።

አምባሳደር ታዬ በበኩላቸው የፀጥታው ምክር ቤት በዚህ ጉዳይ ላይ ስብሰባ መጥራቱ እንደደነቃቸው በዚህ ወቅት ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የተባበሩት መንግሥታት ሠሰራተኞችን እና ሌሎች የዲፕሎማቲክ መልዕክተኞችን ይፋ በሆኑና ባልሆኑ ምክንያትቶ መንግሥታት ከግዛታቸው እንዲወጡ ማድረጋቸውን ጠቅሰው ነገርግን "ምክር ቤቱ በእንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ላይ ስብሰባ ተቀምጦ ያውቃል ወይ?" በማለት ጠይቀዋል።

"አንዲት ሉዓላዊ አገር የዓለም አቀፍ ሕግን ተከትላ በምትወስነው ውሳኔ ላይ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ መቀመጡ የማይጣጣም ሆኖ አግኝተነዋል" በማለት የመንግሥታቸውን አቋም አስረድተዋል።

ሚሊዮኖች ተርበዋል

የተባበሩት መንግሥታት ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከአጋሮቹ ጋር በመሆን በመላ አገሪቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እርዳታ ፈላጊዎችን መደገፍ መቀጠሉን አያቆምም ብለዋል ዋና ፀሐፊው።

"በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የምጠይቀው እርዳታ ያለ እንቅፋት እንድናደርስ እንዲፈቅዱልን እና ሁኔታው በሚጠይቀው አጣዳፊነት ሥራችንን እንዲያመቻቹ ነው" ብለዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በፌደራል ወታደሮች እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ተቀስቅሶ 11ኛ ወሩን ያስቆጠረው ጦርነት ያስከተለው ቀውስ ምን ያህል እንደሆነ በዚህ ወቅት ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

በትግራይ ተነስቶ በአጎራባች አፋር እና አማራ ክልል የተዛመተው ጦርነት በአጠቃላይ ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች የምግብ ዕርዳታ እና አስቸኳይ ድጋፍም ጥገኛ አድርጓቸዋል።

በተለይም በትግራይ ክልል ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በችጋር ያሉ ሲሆን 400 ሺህ ሰዎች በረሃብ አፋፍ ላይ ናቸው።

በአገሪቱ እየተከሰተ ያለው ቀውስ ከፍተኛ ቢሆንም የሚገባው እርዳታ በቂ አይደለም። ለዚህም የመንገዶች መዘጋትና የእንቅስቃሴ ገደቦች ያሉ መሰናክሎች ይጠቀሳሉ።

በተጨማሪም ኤሌክትሪክ፣ የመገናኛ ዘዴዎችና የጤና አገልግሎትና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ሚሊዮኖች አለማግኘታቸው ችግሩን አሳሳቢ እንዳደረገው ምክር ቤቱ ሰምቷል።

የድጋፍ ተማፅኖ

በሴቶች እና ታዳጊዎች ላይ ወሲባዊ ጥቃትን ጨምሮ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በጦርነቱ ተሳታፊዎች ዘንድ ተፈፅመዋል።

በርካታ የረድዔት ሠራተኞችም በረሃብ እየተከሰቱ ያሉ ሞቶችን ጨምሮ መሬት ላይ እየደረሱ ስላሉ ስቃዮች አስከፊነት የተመለከቱትን ማጋራታቸውን አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተናግረው ለኢትዮጵያ መንግሥት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

"አስፈላጊ የሆኑትን የነዳጅ፣ የገንዘብ፣ የመገናኛ መሣሪያዎች እና የሰብአዊ አቅርቦቶች ባልተገደበ መልኩ ወደሚያስፈልጋቸው ክልሎች ሁሉ እንዲገባ መንግሥትን እማፀናለሁ" ብለዋል ዋና ጸሐፊው።

ጦርነት መፍትሄ ሊሆን አይችልም በማለት በተደጋጋሚ የሚናገሩት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ በዚህም ወቅት ሁሉም ወገኖች ግጭቶቹን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲያቆሙና ይህንን ዕድል ተጠቅመው ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቅም ድርድር ማድረግ እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በአገሪቷ ያሉ የውጭ ኃይሎች እንዲወጡ፣ የረድዔት ሠራተኞች እንዲከበሩና የሕዝብ አገልግሎቶች እንደገና እንዲመሠረቱ አሳስበዋል።

"ለሁሉም የፀጥታው ምክር ቤት አባላት እነዚህን ጥሪዎች ለመደገፍ እና የተባበሩት መንግሥታት እና በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አጋሮቹ ከሚያደርጉት ጥረት በስተጀርባ በሕብረት እንዲተባበሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ" ብለዋል።

በዚህ ሳምንት ኢትዮጵያ አዲስ መንግሥት መመስረቷን አስታውሰውም አስተዳደሩ "ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መንግሥት ለመሆን በታደሰ ቁርጠኝነት እንዲሠራ" አሳስበዋል።

የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ እንዲቀመጥ ጥሪ ካደረጉት አንዷ የሆነችው የአሜሪካ የተመድ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት የመንግሥታቱ ድርጅት ባለስልጣናትን ለማባረር የወሰደውን እርምጃ "ጥንቃቄ የጎደለው" በማለት ገልፀው "የኢትዮጵያ መንግሥት ለወሰደው እርምጃ ምንም ምክንያታዊነት የለም" ብለዋል።

ለ15 ምክር ቤቱ አባላትም "የተባበሩት መንግሥታት ገለልተኛ ነው" ብለዋል።

በተጨማሪም እነዚህ ሠራተኞች ህይወት አድን እርዳታን የሚያቀርቡ ከመሆናቸው አንፃር ይህንን አስከፊ መዘዝ ሊያመጣ የሚችለውንም ረሃብ ለማስቆም ከኢትዮጵያ የታገዱት የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች በአስቸኳይ እንዲመለሱ ሊፈቀድላቸው ይገባል ብለዋል።

ጦርነቱ በራስ ላይ የተፈጠረ ቁስል ነው ያሉት አምባሳደሯ "በዚህ ጦርነት ኢትዮጵያውያን፣ ኢትዮጵያውያንን እየገደሉ ነው፤ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያውያንን እየደፈሩ ነው። የኢትዮጵያ መሪዎችም የሕዝቡን ፍላጎት አላሟሉም" ብለዋል።

ሆኖም አሁንም ረሃቡን፣ ጥሰቶችን ለማስቆም፣ ህይወትን ለማዳንም ሆነ አገሪቷም ወደተሻለ ደረጃ ላይ እንድትደርስ ጊዜው አልረፈደም ካሉ በኋላ ነገር ግን ለዚህ ተኩስ አቁምና ድርድር በማድረግ "ሕዝባቸውን መታደግ አለባቸው" በማለት አስረድተዋል።