ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያና ቻይና በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን በተመለከተ የቀረበውን ሃሳብ ተቃወሙ
ትናንት የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን በተመለከተ ያደረገው ውይይት ከስምምነት ላይ ሳይደርስ መቅረቱን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ ዘገበ።
ኤኤፍፒ እንዳለው የጸጥታው ምክር ቤት ያካሄደውን ውይይት ተከትሎ ከስምምነት ቢደርስ ኖሮ ኢትዮጵያ በተመለከተ የቀረበው ረቂቅ መግለጫን ያጸድቅ ነበር።
የዜና ወኪሉ የጸጥታው ምክር ቤትን ረቂቅ መግለጫ ተመልክቻለሁ ብሎ በሰራው ዘገባ፤ የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ባረጋገጠ መልኩ በትግራይ አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ እና ግጭት እንዲቆም የሚጠይቅ ነበር።
ይሁን እንጂ ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣን ካላቸው አምስት ቋሚ የምክር ቤቱ አባላት መካከል የሚገኙት ሩሲያ እና ቻይና መግለጫው በኢትዮጵያ "ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው" በማለት መቃወማቸውን ዘግቧል።
ይህንን ተከትሎ በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ አሜሪካ በሉአላዊ አገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንድትቆጠብ ጠይቋል።
ኤምባሲው በትዊተር ገጹ ላይ፤ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት ማሪያ ዛካሮቫ አሜሪካ በአገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የምታደርገውን ጥረት መቃወማቸውን ገልጿል።
ምንም እንኳ ሕንድ በረቂቅ መግለጫው በተጠቀሱ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ በትስማምም መግለጫውን ሙሉ በሙሉ ሳትደግፍ ቀርታለች ተብሏል።
የዲፕሎማቲክ ምንጮች ነግረውኛል ብሎ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው ከሆነ፤ በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት አባል አገራት ከሆኑት መካከል ሦስት የአፍሪካ አገራት ረቂቅ መግለጫውን ደግፈውታል።
እነዚህም ጎረቤት ኬንያ፣ ኒጄር እና ቱኒዚያ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ጉዳይ የአፍሪካ ሕብረት መሪነቱን ይውሰድ በማለት ድጋፍ ሳይሰጡ ቆይተው ነበር።
የጸጥታው ምክር ቤት በአንድ ድምጽ መናገር አለበት
ይህ ኢትዮጵያ የተመለከተ ጉዳይ በጸጥታው ምክር ቤት በአጀንዳነት እንዲቀርብ ያደረገችው አየርላንድ ነች።
አየርላንድ የተባበሩት መንግሥታት በትግራይ ክልል ስላለው የሰብዓዊ እርዳታ በአንድ ድምጽ መናገር አለበት ብትልም ምክር ቤቱ በውይይቱ ላይ ከስምምነት ሳይደርስ ተለያይቷል።
አየርላንድ በትግራይ ክልል ያለውን አሳሳቢ የሰብዓዊ ሁኔታ ወደ ተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ማቅረቧን እና የአሜሪካ፣ የዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ኖርዌይ እና ኢስቶኒያ ድጋፍ ማግኘቷን ገልጻ ነበር።
የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አባል አገራት የትኞቹ ናቸው?
የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት 15 አባል አገራት አሉ።
ከ15ቱ አባል አገራት አምስቱ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ቋሚ አባል አገራት ሲሆኑ፤ አስሩ ደግሞ በየዓመቱ የሚቀያየሩ እና ድምጽን በድምጽ የመሻር አቅም የሌላቸው አባል አገራት ናቸው።
ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት አባላት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ዩናይትድ ኪንግድ፣ ፈረንሳይ እና ቻይና ናቸው።
ኢስቶኒያ፣ ሕንድ፣ አየርላንድ፣ ኬንያ፣ ሜክሲኮ፣ ኒጂር፣ ኖርዌይ፣ ሴንት ቪንሰንት ኤንድ ዘ ግሬናዲንስ፣ ቱኒዚያ እና ቬትናም ደግሞ አስሩ ተለዋዋጭ የምክር ቤቱ አባላት ናቸው።
ትናንት በጸጥታው ምክር ቤት ምን ተባለ?
የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ፤ የተመድ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርክ ሎውኮክ ለጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን በተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸውን ተናግረዋል።
ስቴፈን ዱጃሪክ የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመነጋገር በተቀመጠበት ወቅት ማርክ ሉውኮክ በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት
ማርክ ሎውኮክ በትግራይ 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ እርዳታ እንደሚያሻው እና በገጠራማ አከባቢ የሚገኘው አብዛኛው ሕዝብ ጋር አሁንም መድረስ አለመቻሉን እንዲሁም የምግብ እጥረት ዋና ጉዳይ መሆኑን ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ተናግረዋል።
ማርክ ሎውኮክ በትግራይ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና የጤና አጠባበቅ አገልግሎቶች ስለተቋረጡ ወረርሽኝ ሊከስት እንደሚችል ተናግረዋል ሲሉ ስቴፈን ዱጃሪክ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
በክልሉ ከሚገኙት 205 የጤና ተቋማት 22 በመቶ ብቻ የሚሆኑት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቅሰው፤ የውሃ ወለድ፣ የኩፍኝ እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋቶች መኖራቸውን ማርክ ሎውኮክ ተናግረዋል።
ማርክ ሎውኮክ በክልሉ ተጨማሪ የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅት ሰራተኞችን በማሰማራት፣ የቴሌኮም እና የባንክ አገልግሎቶችን በማስጀመር እና ለሰብዓዊ እርዳታ ተጨማሪ ድጋፎችን በማሰባሰብ በከፍተኛ ደረጃ የሰብዓዊ ድጋፉን መጨምር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች
ማርክ ሎውኮክ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሸል ባሽሌት በትግራይ ግጭት የተሳተፉ አካላት የጦር እና በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ፈጽመው ሊሆን ይችላል ማለታቸውን ጠቅሰው ለጸጥታው ምከር ቤት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኮሚሽነሯ ተፈጽመዋል የተባሉ ወንጀሎችን የሚመረምር ገለልተኛ አካል መቋቋም አለበት ማለታቸውንም ማርክ ሎውኮክ ጨምረው ተናግረዋል።
ሚሸል ባሽሌት የሚረብሹ የመደፈር፣ የዘፈቀደ ግድያ፣ መጠነ ሰፊ የንብረት ውድመትና ዘረፋ መፈጸሙን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች እንዲሁም በማዕከላዊ ትግራይ ግጭት መቀጠሉን የሚያመላክቱ ሪፖርቶች እያደረሰን ሲሉ ተናግረዋል ሲሌ ማርክ ሎውኮክ ለጸጥታው ምከር ቤት ተናግረዋል።
ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የህወሓት ኃይሎች በትግራይ ክልል በሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ ወታደራዊ ግጭቱ መጀመሩ ይታወሳል።
ጦርነቱን ተከትሎ አገራት፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች በትግራይ ክልል የተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ እንዳሳሰባቸው በተደጋጋሚ ሲገልጹ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በትግራይ ያከናወነው የሕግ ማስከበር እርምጃ መሆኑን በመጥቀስ የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነትን እንደማይቀበል በመግለጽ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መርምሮ እርምጃ እንደሚወስድ አሳውቋል።
ከዚህ ቀደም በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ውይይት እንዲያደርግ ሐሳብ ቀርቦ የነበረ ሲሆን፤ የአፍሪካ አገራት በኢትዮጵያ ጉዳይ የአፍሪካ ሕብረት መሪነቱን ይውሰድ የሚል አቋም መያዛቸው ይታወሳል።