ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትግራይ፡ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እና ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ መወያየታቸው ተነገረ
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጋር መወያየታቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ እንዳሉት፤ የውጭ ጉዳይ ኃላፊው በውይይታቸው በትግራይ ክልል ያለው የሰብአዊ እርዳናታና የሰብአዊ መብቶች ቀውስ አሜሪካንን እንደሚያሳስባት አጽንኦት ሰጥተው ከጠቅላይ ሚኒስተሩ ጋር መነጋገራቸው ተገልጿል።
አንቶኒ ብሊንከን እየጨመረ የመጣ ያሉትን ግድያዎችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ታማኝ ያሏቸውን ሪፖርቶች በመጥቀስ የኢትዮጵያ መንግሥት ስደተኞችን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎችን እንዲጠብቅ እንዲሁም ተጨማሪ ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ ጠይቀዋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩና ጠቅላይ ሚኒስትሩ አደረጉት ስለተባለው ንግግር በተመለከተ በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በውይይታቸው በአስቸኳይ ግጭቶች ቆመው የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎችን ጨምሮ የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል እንዲወጡ አጥብቀው መጠየቃቸው የወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በተመሳሳይ ከቀናት በፊት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በትግራይ ይገኛሉ ያላቸው የኤርትራ ሠራዊት እና የአማራ ክልል ኃይሎች ከክልሉ መውጣት አለባቸው ሲል መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መግለጫ በሰጠው ጠንካራ ምላሽ አገሪቱ በግዛቷ ውስጥ የጸጥታ መዋቅሯን በማሰማራት በኩል ካላት ሉአላዊ መብት አንጻር ጣልቃ መግባት ነው በሚል የአሜሪካንን መግለጫ በጽኑ ተቃውሞታል።
ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትም ይሁን የኤርትራ መንግሥት በትግራይ በተካሄደው ግጭት ኤርትራ ተሳትፎ የላትም ቢሉም፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከዚህ ቀደም የኤርትራ ጦር ወደ ትግራይ ክልል መግባቱን የሚገልጽ መረጃ ማውጣቱ ይታወሳል።
ብሊንከን ከጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ ጋር በነበራቸው ወይይት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ገለልተኛ፣ ዓለም አቀፍና ተአማኒ መርመራዎች ተፈጸሙ በተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ እንዲካሄድና ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር እንዲሰራ መጠየቃቸው ተገልጿል።
ባሳለፍነው ዓርብ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአክሱም ከተማ ከ200 በላይ ንጹሃን ዜጎች በኤርትራ ሠራዊት ተገድለዋል የሚል ሪፖርት ማውጣቱ ይታወሳል።
አምነስቲ ይህ የጅምላ ግድያ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ሊሆን ይችላል ብሎ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት "ባልተሟላ መረጃና ውስን በሆነ የጥናት ዘዴ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው" ሲል ተችቷል።
የኤርትራ መንግሥትም በተመሳሳይ የአምነስቲን ሪፖርት እንደማይቀበለው ገልጿል። ኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል ሪፖርቱ በአብዛኛው መሠረት ያደረገው ሱዳን ውስጥ ባለው ሐምዳይት የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ያሉ 31 ግለሰቦችን ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የአምነስቲ ሪፖርት የጥናት ዘዴ ይተች እንጂ መንግሥት ገለልተኛ ቡድን በማቋቋም ተፈጽመዋል የተባሉ በደሎችን የሚመረምር ቡድን ለማዋቀር ዝግጁ መሆኑን አስታውቆ ነበር።
የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንሰትሩ አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር ባደረጉት ውይይት በቅርቡ ኢትዮጵያ ወደ ትግራይ ክልል የሚደረጉ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች ያለምንም ገደብ እንዲካሄዱ መፍቀዷን አድንቀዋል።
በተጨማሪም አሜሪካ ግጭቱ መፍትሔ እንዲያገኝ ለመርዳት ዝግጁ መሆኗንና በመላው ኢትዮጵያ የሚያስፈልግ ህይወት አድን የሰብአዊ እርዳታን በማቅረብ በኩል ያላትን ፈቃደኝነት ገልጸዋል።