ትግራይ፡ የተባበሩት መንግሥታት አክሱም ውስጥ የተፈጸመውን ግድያ እንዲመረምር ሂዩማን ራይትስ ዋች ጠየቀ

በትግራይ ክልል የተፈጽሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመመርመር ተጠያቂነትን የሚያሰፍን የተባበሩት መንግሥታት ገለልተኛ ምርመራ በአስቸኳይ እንዲደረግ ሂዩማን ራይትስ ዋች ጥሪ አቀረበ።

የመብት ድርጅቱ ይህንን ያለው የኤርትራ ጦር ሠራዊት በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የ13 ዓመት እድሜ ያላቸውን ታዳጊዎች ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን በተመለከተ ዛሬ ባወጣው ሪፖርት ላይ ነው።

ሂዩማን ራይትስ ዋች በዛሬው ሪፖርቱ በክልሉ የጦር ወንጀሎችና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ሳይፈጸሙ እንዳልቀሩ ጠቅሶ ይህም በአስቸኳይ ተጣርቶ ፈጻሚዎቹ ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቋል።

ባለፈው ሳምንት ሌላኛው ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት በአክሱም ከተማ ከ200 መቶ በላይ ሰዎች በኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውን መግለጹ ይታወሳል።

የአምነስቲን ሪፖርት ተከትሎ መንግሥታዊው የኢትየጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአክሱም ከተማ ተፈጸመ ስለተባለው ግድያ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ኅዳር 10/2013 ዓ.ም የኢትዮጵያና የኤርትራ ኃይሎች በአክሱም ከተማ ላይ በፈጸሙት ቦታ ያልለያ የከባድ መሳሪያ ድብደባ ሰላማዊ ሰዎች ለሞትና ለጉዳት መዳረጋቸውን አመልክቶ፤ ከተማዋ ከተያዘች በኋላ ለሳምንት ያህል ሰላማዊ ሰዎችን በጥይት ተመተዋል፣ ንብረት ተዘርፏል ወድሟል ብሏል።

ኅዳር 19/2013 ዓ.ም የትግራይ ሚሊሻና የአክሱም ነዋሪዎች በኤርትራ ሠራዊት ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ በወሰዱት የበቀል እርምጃ በ24 ሰዓት ውስጥ በአብዛኛው ወንድ ልጆችና አዋቂ ወንዶች የሆኑ በርካታ ነዋሪዎችን እንደገደሉ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ክስተቱን በሚመለከት እያደረገ ባለው ምርመራ የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቱ "ጥቂት ነዋሪዎችና የህወሓት ታጣቂዎች ለፈጸሙባቸው ጥቃት የኤርትራ ወታደሮች በወሰዱት የበቀል እርምጃ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰላማዊ ሰዎች በከተማዋ ውስጥ ተገድለዋል" ሲል አመልክቷል።

"የኤርትራ ወታደሮች ለሰላማዊ ሰዎች ህይወት ግድ ሳይሰጣቸው በአክሱም ከተማ ጭካኔ የተሞላበት ግድያ ፈጽመዋል" ያሉት የሂማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ቀንድ ኃላፊ ላቲታ ባደር፤ የኢትዮጵያና የኤርትራ ባለስልጣናት ፍትህ እንዲሰፍን ፈቃደኛ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

ወታደራዊው ግጭት የተቀሰቀሰው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የትግራይ ክልልን ያስተዳድር የነበረው የህወሓት ኃይሎች በአገሪቱ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትከሎ መሆኑ ይታወሳል።

ምንም እንኳን ኢትዮጵያና ኤርትራ መንግሥታት በተደጋጋሚ ቢያስተባብሉም የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል ውስጥ ተሰማርተው በወታደራዊ ዘመቻው ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸውን የተለያዩ ሪፖርቶች አመልክተዋል።

በሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት መሠረት ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች የኤርትራ ወታደሮችን በተሽከርካሪዎቻቸው የሠሌዳ ቁጥር፣ በሚለብሱት የተለየ የደንብ ልብስ፣ በትግርኛ ቋንቋ ዘዬቸውና በሚጫሙት ኮንጎ ጫማ እንደለይዋቸው ገልጿል።

በከተማዋ የሚገኙ 28 ሰዎችን በስልክ በማናገርና ቪዲዮዎችን በመመርመር ሪፖርቱን ያዘጋጀው የሰብአዊ መብቶች ድርጅቱ፤ በከተማዋ በሁለት ቀናት በተፈጸመው ጭፍጨፋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ200 በላይ ሊሆን እንደሚችል አመልክቷል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ባደረገው ማጣራት ያገኘውን ውጤት ከሁለት ሳምንት በፊት ለኢትዮጵያና ለኤርትራ መንግሥት ባለስልጣናት ያቀረበ ቢሆንም ምላሽ እንዳላገኘ ገልጿል።

አስካሁን የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ መንግሥታት በሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ላይ በይፋ የሰጡት ምላሽ የለም።

በኤርትራ በኩል የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አቶ የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገጻቸው ላይ የድርጅቱን ሪፖርት በበርካታ መልኩ የተሳሳተ ነው ያሉትን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል መልሶ ያስተጋባ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

ጨምረውም ሁለቱ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች አንድ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በኤርትራ ውስጥ ለአስር ዓመታት ያህል "የሥርዓት ለውጥ" ለማካሄድ ሲጥሩ ነበር ሲሉ ከሰዋቸዋል።

ኤርትራ ቀደም ያለውን የአምነስቲ ኢንተርናሽናልን ሪፖርት ውድቅ በማድረግ ወታደሮቿ አክሱም ውስጥ ፈጸሙት የተባለውን ግድያ እንደማትቀበለው መግለጿ ይታወሳል።

የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ የአገራቸው ወታደሮች አክሱም ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ስለመግደላቸው ያወጣውን ሪፖርት አጣጥለውታል።

የሂማን ራይተስ ዋች ኃላፊ ላቲታ ባድር እንዳሉት "በኢትዮጵያና በኤርትራ ኃይሎች ለተፈጸሙ ከባድ በደሎች ፍትህን ለማስገኘት ውግዘት ብቻ በቂ አይደለም" በማለት የድርጊቱ ፈጻሚዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ከተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት ትኩረትና ተግባር ያስፈልጋል ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሸል ባሽሌት ከትግራይ የሚወጡ ሪፖርቶችን ጠቅሰው በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ በሆኑ የተለያዩ ወገኖች የተፈፀሙ ከባድ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊ እርዳታ ሕጎች ጥሰትን የሚያመለክቱ መሆናቸውን ሐሙስ ዕለት ገልጸዋል።

በትግራይ ግጭት የተሳተፉ አካላት "የጦር እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ፈጽመው ሊሆን እንደሚችል" የጠቀሱት ባሽሌት እነዚህን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ወሲባዊ ጥቃቶችን ኮሚሽናቸው ለመመርመር እንዲችል ፈቃድ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

የኢትዯጵያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ሰሞኑን እንደተናገሩት ትግራይ ውስጥ ተከሰቱ ስለተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ግድያዎች ዙሪያ መንግሥት ከፌደራል ፖሊስ፣ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመሆን ምርመራ ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል።

የምርመራውን ውጤት መሰረት በማድረግም መንግሥታቸው በድርጊቱ ውስጥ እጃቸው ያለበትን ወገኖች ተጠያቂ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ በምርመራው ላይ ተጨማሪ እርዳታ ካስፈለገ መንግሥት የውጭ አካል ሊጋብዝ እንደሚችል አመልክተዋል።