የፀጥታው ምክር ቤት ዛሬ ለ10ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ጉዳይ ይወያያል

የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ለ10ኛ ጊዜ ዛሬ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ውይይት እንደሚያደርግ ተገለጸ።

"ፒስ ኤንድ ሰኪውሪቲ ኢን አፍሪካ" በሚለው የውይይት አጀንዳ ስር በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ውስጥ ስላለው ሁኔታ ውይይት እንደሚደረግ የምክር ቤቱ መግለጫ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካዮች ይገኙበታል ተብሎ በሚጠበቀው ይህ የምክር ቤቱ ውይይት ባለፈው ሳምንት ከተካሄደው በተለየ ክፍት ስብሰባ እንደሚሆን ተነግሯል።

ውይይቱ እንዲካሄድ የጠየቁት አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ኖርዌይ፣ ኢስቶኒያ፣ ፈረንሳይ እና አየርላንድ ሲሆኑ፤ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በዛሬው ውይይት ጉቴሬዝ፤ ሰባቱ የድርጅታቸው ሠራተኞች ከኢትዮጵያ መውጣታቸውን በተመለከተ እንዲሁም በአገሪቱ ስለላለው ሰብአዊ ቀውስ ንግግር ያደርጋሉ ተብሏል።

በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ጦርነት ከተነሳ ወዲህ የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሲወያይ የዛሬውን ጨምሮ ለ10 ጊዜ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ሰባት የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች አገር ለቀው እንዲወጡ ካዘዘች ወዲህ ምክር ቤቱ ውይይት ሲያደርግ የዛሬው ሁለተኛው ይሆናል።

ኢትዮጵያ በሕገ ወጥ ተግባር ተሰማርተው አግኝቻቸዋለሁ ያለቻቸውን ሰባት የድርጅቱን ሠራተኞች በ72 ሰዓታት ከአገር እንዲወጡ ውሳኔ ማሳለፏን ተከትሎ፤ በአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ኖርዌይ፣ ኢስቶኒያ፣ ፈረንሳይ እና አየርላንድ ጥያቄ ምክር ቤቱ ውይይት ማካሄዱ ይታወሳል።

ይህ ባለፈው ሳምንት የተደረገውን የፀጥታው ምክር ቤት በዝግ ያካሄደውን ውይይት ተከትሎ አየርላንድ ያዘጋጀችው መግለጫ በቂ ድጋፍ ስላላገኘ ይፋ ሳይደግ ቀርቷል።

አየርላንድ አዘጋጅታው የነበረው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ የተመድ ሠራተኞችን ከግዛቷ ማስወጣቷን የሚያውግዝ፣ ኢትዮጵያ ከተመድ ጋር እንድትተባበር የሚጠይቅ እና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዳይደናቀፍ የሚያሳስብ እንደነበር ከፀጥታው ምክር ቤት የተገኘ መረጃ ይጠቁማል።

ነገር ግን ኤስሪ ፕላስ ዋን የሚባሉት ኬንያ፣ ኒጀር፣ ቱኒዝያ፣ ሴንት ቪንሰንት እና ዘ ግሪኒናዲስ እንዲሁም ቻይና እና ሩስያ መግለጫው ጠቀሜታ የለውም ሲሉ ተቃውመዋል። የመንግሥታቱ ድርጅት በኢትዮጵያ ጉዳይ መፍትሔ እንዲፈልግም አገራቱ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ሰባቱ የተመድ ሠራተኞች ከአገር እንዲወጡ ያሳለፈችውን ውሳኔ እንድትቀለብስ ድርጅቱ እንደጠየቀ የዋና ጸሐፊው ምክትል ቃል አቀባይ ፋርሀን ሐቅ ተናግረዋል።

አንድ አገር በዲፕሎማሲ ሥራ ውስጥ ያሉና ያለመከሰስ መብት ያላቸውን ሰዎች ሕጋዊ ሽፋን ማንሳት የምትችልበት አሠራር (ፐርሶና ነን ግራታ) ተግባራዊ የሚሆነው በአገራት ለተሾሙ ዲፕሎማቶች እንጂ ለተመድ አመራሮች እንዳልሆነ የመንግሥታቱ ድርጅት ለኢትዮጵያ አስታውቋል።

ድርጅቱ እነዳለው እርምጃውን ተከትሎ ዋና ጸሐፊው ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በስልክ ተነጋግረዋል።

ዋና ጸሐፊው ጉቴሬዝ እንዳሉት፤ ሰባቱ የተመድ ሠራተኞች ከኢትዮጵያ መባረራቸው የእርዳታ መስጠት ሂደቱን ያደናቅፋል።

"የሰዎችን ሕይወት ለመታደግ እና ሰብአዊ መብታቸውን ለማስጠበቅ መረባረብ ባለብን ወቅት ሠራተኞቹ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ መወሰኑ ሌላ መሰናክል ይፈጥራል። ሰብአዊ ድጋፍን የፖለቲካ ጉዳይ ማድረግ ተመድ ኢትዮጵያውያንን ለመርዳት የሚያደርገውን ጥረት ያሰናክላል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ሰባቱ ሠራተኞች ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት የሚሆኑ ተግባራት ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው ከአገር ለማስወጣት እንደተወሰነ ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲሁም በተመድ የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ እንዳሉት፤ ሠራተኞቹ ሰብአዊ እርዳታ ለህወሓት አሳልፈው ከመስጠታቸው በተጨማሪ የተሳሳተ መረጃም አሰራጭተዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ግን እነዚህን ክሶች አስተባብሏል። ሠራተኞቹ ከመድልዎ ነጻ እንደሆኑና የሙያ ሥነ ምግባር እንደሚከተሉም ድርጅቱ አክሏል።

በሰባቱ ሠራተኞች ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ መደረጉን ድርጅቱ ያሳወቀ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም ከአገር በወጡት ምትክ ሌሎች ሠራተኞች እንዲተኩ ጠይቃለች።

የጉቴሬዝ ምክትል ቃል አቀባይ ፋርሀን ሐቅ፤ በሰባቱ ሠራተኞች ምትክ ሌሎች ሠራተኞች ወደ ኢትዮጵያ ይላኩ እንደሆነ ተጠይቀው፤ "ተመድ የላካቸው ሠራተኞች ለሥራው የሚመጥን አቅም ያላቸው ናቸው። ያለ ምንም መሰናክል ሥራቸውን መቀጠል አለባቸው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በተመድ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር የሆኑት ጄኒቫ ሳይመን ማንሊ 40 አገራትን ወክለው፤ ሰባቱ ሠራተኞች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው እንዲሠሩ እንዲፈቀድ ጠይቀዋል።