ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጸጥታው ምክር ቤት በትግራይ ጉዳይ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ
የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በትግራይ ጉዳይ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ጥሪ ቀረበለት።
የጸጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ የጠየቁት አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አየርላንድ መሆናቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ለዜና ወኪሉ ቃላቸውን የሰጡ ዲፕሎማቶች እንዳሉት ከሆነ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በትግራይ ጉዳይ የፊታችን አርብ ሊወያይ ይችላል።
አገራቱ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲካሄድ የጠየቁት የፌደራሉ መንግሥት ጦር መቀለን ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ የትግራይ ኃይሎች የክልሉን መዲና መቆጣጠራቸው ከተሰማ በኋላ ነው።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፌደራል መንግሥቱ በክልሉ ውስጥ የተኩስ አቁም እንዲያደረግ መጠየቁን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁ ይታወሳል።
የትግራይ ኃይሎች መቀለን ሲቆጣጠሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ መንገዶች በመውጣት ባንዲራ በማውለብለብ እና ርችት በመተኮስ ደስታቸውን ሲገልጹ እንደነበረ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማይቱ ነዋሪዎች የትግራይ ኃይሎች የከተማዋን ዋና መንዶችን ጨምሮ አየር ማረፊያውን ተቆጣጥረዋል ብለዋል።
የፌደራሉ መንግሥት ጦር ቀደም ብሎ ከተማዋን ለቅቆ ስለመውጣቱ የተከማዋ ነዋሪዎች ጨምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የፈረንሳይ ዜና ወኪል ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ሰዎች ሰማሁ በማለት እንደዘገበው ከሆነ የትግራይ ኃይሎች መቀለን መቆጣጠራቸው ከመነገሩ በፊት ሁሉም የጊዜያዊው አስተዳደሩ ኃላፊዎች ከተማዋን ለቅቀው ወጥተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ የተናጠል የተኩስ አቁም ማድረጉን ይፋ ባደረገበት መግለጫ ላይ የትግራይ ኃይሎች መቀለን ስለመቆጣጠራቸው ያለው ነገር የለም።
የትግራይ ኃይሎች መቀለን የመቆጣጠራቸው ዜና መሰማቱን ተከትሎ ትናንት አመሻሽ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ ማውራታቸውን ገልጸው፤ "ግጭት ይቆማል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል።
በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት በርካታ የክልሉ ነዋሪዎችን ለከፋ የሰብዓዊ ቀውስ የዳረገ ሆኗል።
የተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎች ምዕራባውያን በጎ አድራጊ ድርጅቶች በትግራይ አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ አሳሳቢ የረሃብ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል በተደጋጋሚ ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
ከዚህ ቀደም በጸጥታው ምክር ቤት ምን ተብሎ ነበር?
የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ትግራይን በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ ባወጣው መግለጫ በትግራይ በቂ የሰብዓዊ እርዳታ ባይቀርብም የኢትዮጵያ መንግሥት ጥረት ግን የሚበረታታ ነው ማለቱ ይታወሳል።
ምክር ቤቱ ሚያዚያ 15/2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ በክልሉ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አሳስቦኛል ያለ ሲሆን፣ የምክር ቤቱ አባል አገራት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የፖለቲካ ነጻነትን ያከብራሉ ብሏል።
የመግለጫውን መውጣት ተከትሎ የተመድ የኢትዮጵያ ተወካይ፤ የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ለሰጡት 'ገንቢ ምልከታ እና ድጋፍ' አድናቆቱን ገልጾ ነበር።
የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ከሚያዚያ 15 በፊት ኢትዮጵያን በተመለከተ መግለጫ ለማውጣት በርካታ ጊዜ ቢሰበሰብም ከስምምነት ሳይደርስ መቅረቱ ይታወሳል።
በትግራይ አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ እና ግጭት እንዲቆም የሚጠይቅ መግለጫ ለማውጣት ያደረገው ስብሰባ በሩሲያ እና በቻይና ተቃውሞ ሳይወጣ ቀርቷል።
ሩሲያ እና ቻይና መሰል መግለጫ በኢትዮጵያ "ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው" በማለት ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው ይታወሳል።
የጸጥታው ምክር ቤት አባል አገራት የትኞቹ ናቸው?
የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት 15 አባል አገራት አሉት።
ከ15ቱ አባል አገራት አምስቱ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ቋሚ አባል አገራት ሲሆኑ፤ አስሩ ደግሞ በየዓመቱ የሚቀያየሩ እና ድምጽን በድምጽ የመሻር አቅም የሌላቸው አባል አገራት ናቸው።
ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው የምክር ቤቱ አባላት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ዩናይትድ ኪንግድ፣ ፈረንሳይ እና ቻይና ናቸው።
ኢስቶኒያ፣ ሕንድ፣ አየርላንድ፣ ኬንያ፣ ሜክሲኮ፣ ኒጂር፣ ኖርዌይ፣ ሴንት ቪንሰንት ኤንድ ዘ ግሬናዲንስ፣ ቱኒዚያ እና ቬትናም ደግሞ አስሩ ተለዋዋጭ የምክር ቤቱ አባላት ናቸው።