የማላዊ የቀድሞ የምክር ቤት አባል ምክር ቤት ውስጥ ራሳቸውን ገደሉ

የፎቶው ባለመብት, TedX
የማላዊ የቀድሞ የምክር ቤት አባል ክለመንት ቺዋያ ምክር ቤት ውስጥ በሚገኝ ቢሮ በጥይት እራሳቸውን መትተው ሕይወታቸውን አጠፉ።
የሁለት ዓመት ሕጻን ሳሉ በፖሊዮ በሽታ ምክንያት በደረሰባቸው የአካል ጉዳት የዊልቸር ተጠቃሚ የነበሩት ቺዋያ፤ እአአ ከ2014 እስከ 2019 ባሉት ጊዜያት የማላዊ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሆነው አገልግለዋል።
የቀድሞ የምክር ቤት አባሉ ራሳቸውን ከመግደላቸው በፊት ባስቀመጡት ማስታወሻ ከምክር ቤቱ ባለሥልጣናት ጋር በልዩ ሁኔታ በተዘጋጀ ተሽከርካሪ ባለቤትነት ምክንያት ውዝግብ ውስጥ ገብተው እንደነበር አስፍረዋል።
ቺያዋ ከምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔነት ከመነሳታቸው በፊት በምክርቤቱ የቀረበና አካል ጉዳተኛ ቢሆኑም ሊያሽከረክሩት የሚችሉት መኪና ግዥ እንዲፈቀድላቸው የሚያስችላቸውን ሂደት ጀምረው ነበር።
የቀድሞ የምክር ቤት አባሉ ለተሽከርካሪው ክፍያ መፈፀማቸውን፤ ነገረ ግን ፓርላማው ባለቤትነቱን ለእርሳቸው ለማስተላለፍ አልፈቀደም ሲሉ ምክር ቤቱን ከሰዋል።
ምክር ቤቱ ከቀድሞ የምክር ቤት አባሉ ሞት በኋላ ባወጣው መግለጫም ጉዳዩ እስካሁን በፍርድ ቤት የተያዘ መሆኑን ገልጿል።
የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ቺዋያ ሐሙስ ዕለት ወደ ምክር ቤቱ ጸሐፊ ቢሮ ከገቡ በኋላ ጸሐፊው እየተመለከቷቸው ነበር ራሳቸው ላይ የተኮሱት።
ቺዋያ ባስቀመጡት ማስታወሻ ላይ የራሳቸው የሆነን ነገር ለማግኘት መለማመጥ እንደሰለቻቸው በመግለፅ 'ሌሎችን ላለመጉዳት' በመፍራት የራሳቸውን ሕይወት እንዳጠፉ ገልጸዋል።
የ50 ዓመቱ ቺዋያ የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋች የነበሩ ሲሆን ለአገሪቷ ምክር ቤት አባልነት ሦስት ጊዜ ተወዳድረው ተመርጠዋል።
ፖሊስ የቀድሞ የምክር ቤት አባሉ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለት ምክር ቤት ጥይት የጎረሰ ሽጉጥ ይዘው እንዴት ሊገቡ እንደቻሉ እየመረመረ ነው።
ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ የደህንነት ባለሥልጣናቱ ቺዋያ ሲገቡ የፍተሻ መሣሪያዎቹ ድምጽ ያሰሙት በዊልቸራቸው ምክንያት ነው ብለው አስበው ነበር ብሏል።












