በናዚ የ11ሺህ ሰዎች ግድያ ተባባሪ ነበሩ የተባሉ የ96 ዓመት ሴት ተሰወሩ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ስቱተፎ ተብሎ የሚጠራው የናዚ ማጎሪያ ካምፕ ሠራተኛ የነበረች እና በሰዎች ግድያ ተባባሪ ናቸው የተባሉ የ96 ዓመት ሴት ከሚኖሩበት የአዛውንቶች ማቆያ መሰወራቸው ተነገረ።
አዛውንቷ በ11ሺህ ሰዎች ግድያ ውስጥ በተባባሪነት ተጠርጥረው ክስ ተመስርቶባቸው ሰሜን ጀርመን ባለ ፍርድ ቤት ዛሬ ሐሙስ መቅረብ ነበረባቸው።
ኢራመጋርድ ፉርቸነር የተባሉት አዛውን ከሚኖሩበት የአዛውንቶች ማቆያ ታክሲ ይዘው ከወጡ በኋላ በባቡር ተሳፍረው ወደ ጀርመኗ ሃምቡርግ ሳይጓዙ አይቀርም ተብሏል።
የፍርድ ቤቱ ዳኛ ዶሚኒክ ግሮስ በአዛውንቷ ላይ የእስር ማዘዥ መውጣቱን ተናግረዋል።
በናዚ ጉዳት የደረሰባቸው የቤተሰብ አባላትን የሚወክሉ ቡድኖች የአዛውንቷ የማምለጥ ዜና አበሳጭቶናል እያሉ ነው።
ከእነዚህ ቡድኖች መካከል አንዱ ዓለም አቀፉ የኦሽዊትስ ኮሚቴ የአዛውንቷ መጥፋት የሚያመለክተው ሕግን እና ከናዚ ጥቃት የተረፉ ሰዎች መዳፈርን ነው ብሏል።
ኢራመጋርድ ፉርቸነር የናዚ ማጎሪያ ካምፕ ኃላፊ የነበረው ፖል-ዎርነር ሆፕ ፀሐፊ ሆነው ሰርተዋል።
ኢራመጋርድ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እአአ 1945 ከመጠናቀቁ በፊት ፖላንድ ውስጥ በነበረው የናዚ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ምን እንደተከናወነ ዝርዝር መረጃ አላቸው።
ተከሳሿ እአአ 1954 ላይ የማጎሪያ ካምፑ ኃላፊ ሆፕ በቃሉ የሚነግረኝን ከመጻፍ ውጪ በካምፑ ውስጥ ስለተፈጸመው ግድያ የማውቀው ነገር የለም ብለው ነበር።
የአዛውንቷ ፍርድ በናዚ ጀርመን ከተፈጸሙት ግድያዎች ጋር በተያያዘ ከመጨረሻዎቹ የፍርድ ሂደቶች መካከል አንዱ ነው ተብሏል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በዚህ ወንጀል ተሳታፊ ናቸው የሚባሉት በሞት በመለየታቸው ነው።
በአሁኗ ፖላንድ ውስጥ ተቋቁሞ በነበረው ስቱትሆፍ ካምፕ ውስጥ ከ100ሺህ ያማያንሱ ሰዎች ታጎረው ነበር። ከእነዚህ መካከል ወደ 65ሺህ የሚጠጉት ተገድለዋል።
በስቱትሆፍ የናዚ ማጎሪያ ካምፕ ሰዎች በመርዛማ ጋዝ፣ በጥይት ተመትተው አልያም መርፌ ተወግተው ይገደሉ ነበር።
በካምፑ ከተገደሉት አብዛኛዎቹ አይሁዳውያን፣ የፖላንድ ዜጎች እና በጦርነት ወቅት የተማረኩ የሶቪዬት ወታደሮች ይገኙበታል።












