ሂውማን ራይትስ ዋች፡ "ጀርመን ዶ/ር ዳንኤል በቀለን መሸለሟ አግባብ አይደለም"

የፎቶው ባለመብት, German Africa Foundation
የሂውማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር የጀርመን አፍሪካ ፋውንዴሽን (ዲኤኤስ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለን (ዶ/ር) ለመሸለም መወሰኑ "ወቅቱን ያልጠበቀ እንዲሁም የተሳሳተ መልዕክት የሚያስተላልፍ" ነው ሲሉ ወቀሱ።
ላቴሺያ ይህንን ያሉት በሚቀጥለው ሳምንት የሚመሰረተው አዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ብሎም በዕለቱ የሚታደሙት የአፍሪካ መሪዎች ላይ በትግራይ ክልል ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተመለከተ ጫና ለማሳደር በተጠራው የፕሬስ መግለጫ ላይ ነው።
"አሁን ባለንበት ሰዓት፤ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ክብደትን ከግምት ውስጥ ከከተትን፤ ምንም እንኳን አንድ ሰው ለሰብአዊ መብቶች ያለው የቁርጠኝነት የኋላ ታሪክ የተመሰከረለት ቢሆንም እንዲህ ያለ ሽልማት መስጠት የተሳሳተ ዲፕሎማሲያዊ መልዕክት ያስተላልፋል" ሲሉ ላቴሺያ ተናግረዋል።
ሃላፊዋ አክለውም "የእነዚህ ጥሰቶች ሰለባዎች ብሎም ከጥቃቶቹ የተረፉት ሰዎች እነዚህን የፌደራል ተቋማት አያምኗቸውም። ይህ ባለፈው አመት በኦሮሚያ የሰራነውን ጥናት ጨምሮ በዚህ ዓመት በሰራናቸው ጥናቶች እንዲሁም በትግራይ ክልል ካሉ የጥቃቶቹ ሰላባዎች የተረዳነው በፌደራል ተቋማት ላይ ዕምነት እንደሌላቸው ነው" ብለዋል።
"ጀርመን በዚህ ሰአት ለአንድ የፌደራል ተቋም መሪ እንዲህ ያለ ሽልማት ለመስጠት መወሰኗ የተሳሳተ መልክት የሚያስተላልፍ ይሆናል" ሲሉ የቀድሞ የተቋማቸው ከፍተኛ አመራር የነበሩትን የዶ/ር ዳንኤልን መሸለም ተቃውመዋል።
ፋውንዴሽኑ ዶ/ር ዳንኤል ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ላበረከቱት የህይወት ዘመን አስተዋፅኦ ከፍተኛውን ሽልማት ለመስጠት መወሰኑን ከሁለት ሳምንታት በፊት ይፋ አድርጎ ነበር።
ዶ/ር ዳንኤል ከ30 ዕጩዎች መካከል በሙሉ ድምፅ የተመረጡ ሲሆን ሽልማታቸውንም በኅዳር ወር እንደሚቀበሉም ይጠበቃል።
ሂውማን ራይትስ ዋች "ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እስከ አሁን ድረስ የቀጠሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አይተው እንዳለዩ ማለፍ የለባቸውም፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ መሪዎች በትግራይ ላይ የተጫነው የተዘዋዋሪ ከበባ እንዲያነሱ ሊያሳስቡ ይገባል" ሲል ጠይቋል። እንዲሁም የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ ሊያሳስቡ ይገባል ብሏል።
የአፍሪካ ህብረት ጦርነቱን ተከትሎ እየደረሱ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለማስቆም ጫና ማድረግ ይጠበቅበታል ያሉት ላቲሺያ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዘዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የሚመሩት የአፍሪካ ቀንድ ወኪል ጽህፈት ቤትም ተጠያቂነት ላይ ያተኮረ ስራ እንዲሰራ ጠይቀዋል።
"የአፍሪካ ሕብረት በሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ የሚካሄደውን የበዓለ ሲመት አይነት የዲፕሎማሲያዊ አጋጣሚዎችን በመጠቀም የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል መሰረታዊ ግልጋሎቶችን እንዲያስጀምር ጫና መፍጠር ይገባዋል። ከሁሉም በፊት ግን ስለፍትሕ፣ ሰብአዊ መብቶች ብሎም ተጠያቂነትን በተመለከተ ፊት ለፊት በመውጣት በይፋ እንዲያወግዝ እንጠይቃለን" ሲሉ የሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ የአድቮኬሲ ሃላፊ ካሪን ካኔዛ ናንቱሊያ ጠይቀዋል።












