የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ የጀርመን አፍሪካ ፋውንዴሽን ተሸላሚ ሆኑ

ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)

የፎቶው ባለመብት, German Africa Foundation

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የዘንድሮው የጀርመን አፍሪካ ፋውንዴሽን (ዲኤኤስ) ተሸላሚ ሆኑ።

ፋውንዴሽኑ በዛሬው ዕለት እንዳስታወቀው ዶ/ር ዳንኤል ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ላበረከቱት የህይወት ዘመን አስተዋፅኦ ከፍተኛውን ሽልማት ለመስጠት መወሰኑን አስታውቋል።

ዶ/ር ዳንኤል ከ30 ዕጩዎች መካከል በሙሉ ድምፅ የተመረጡ ሲሆን ሽልማታቸውንም በኅዳር ወር እንደሚቀበሉም ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ዳንኤል ኮሚሽኑ ነፃ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውንም ፋውንዴሽኑ ካሰፈረው መረጃ መረዳት ተችሏል።

ሽልማቱ "የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በከፍተኛ ደረጃ እንዲለወጥና ገለልተኝነቱ እንዲረጋገጥ፣ እንዲሁም ሥልጣንና ኃላፊነቱ እንዲሰፋ ለተጫወቱት ቁልፍ ሚና እውቅና የሚሰጥ" መሆኑም ተገልጿል።

ከ25 ዓመታት በላይ በየዓመቱ ሲካሄድ የቆየው ይህ ሽልማት፣ በሙያቸው የላቀ አመራር ላሳዩና ለእድገትና ለመሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አፍሪካውያን እውቅና የሚሰጥ ሲሆን በባለፈው ዓመትም ሶማሊያ ካናዳዊት የሰላም ተሟጋች ኢልዋድ ኤልማንን ሸልሟል።

ከዚህ ቀደም ሽልማቱ ከተበረከተላቸው አፍሪካውያን መካከል የቀድሞው የማሊ ፕሬዝዳንት አልፋ ኦማር ኮናሬ፣ የጋናው የሕግ ባለሙያና ከፍተኛ ዲፕሎማት ሞሐመድ ኢብን ቻምባስ እንዲሁም የኬንያው የፀረ-ሙስና ተሟጋች ጆን ጊቶንጎ ይገኙበታል።

የዋና ኮሚሽነሩን ሽልማት በማስመልከት የድርጅታቸው ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ "ዶ/ር ዳንኤል 'ማየት የምትሹትን ለውጥ ሁናችሁ ተገኙ የሚለውን የእንግሊዘኛ ብሂል ማሳያ ስለመሆናቸው ሁላችንም የኢሰመኮ ሠራተኞች የምንመሰክረው ነው" ብለዋል።

አክለውም "የዳንኤል በር ለማንኛው እሱን ለሚፈልግ ሰው ዝግ ሆኖ አያውቅም፣ ከባልደረቦቹ ሁለት እጥፍ የሚተጋና የሰዎችን እምቅ አቅም ጭምር የመለየት አቻ የሌለው ችሎታ ያለው ሰው ነው። ዋና ኮሚሽነራችን ላገኙት እውቅና ሙሉ ድጋፋችንን ስንለግስ በከፍተኛ ኩራት ነው" ብለዋል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ጠበቃ የሆነት ዳንኤል በሂውማን ራይትስ ዋች ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2011 እስከ 2016 የተቋሙ የአፍሪካ ክንፍ ዋና ዳይሬክተርነት እንዲሁም በተጨማሪም በኦክስፋም፣ አርቲክል 19፣ የዓለም ባንክ እና ዩኤስኤድን በአማካሪነት አገልግለዋል።

በበርካታ የሲቪል ማኅበራት ውስጥ የሠሩት ዶ/ር ዳንኤል፤ የ97ቱ ምርጫ ነጻ እንዲሆን እንዲሁም ሰብአዊ መብት እንዳይጣስ ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል።

ከምርጫው በኋላ የተፈጠረውን ቀውስ ለማርገብም የሞከሩ ሲሆን በዚህም ለእሥር ተዳርገው ነበር።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2009 ላይ ላይ 'አሊሰን ደስ ፎርጅስ አዋርድ ፎር ኤክስትራኦርዲነሪ አክቲቪዝም' የተሰኘ ሽልማትንም አግኝተዋል።

ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በሪጅናል ዴቨሎፕመንት ስተዲስ እንዲሁም ከኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ በሌጋል ስተዲስ ሁለተኛ ዲግሪ፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ ሕግ አግኝተዋል።