የኢዜማ እና የአብን አባላት የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ አባል ሆነው ተሾሙ

ሥራውን የጀመረው በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ምክር ቤት በከንቲባነት የተሾሙት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲዎችን አመራሮችን ጨምሮ 26 የካቢኔ አባሎቻቸውን አቅርበው እንዲሾሙ አደረጉ።

የከተማዋን የተለያዩ ቢሮዎችን እንዲመሩ ከተመረጡት መካከል የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና በሚንስትር ማዕረግ የፌደራል ተቋማትን ሲመሩ የነበሩ ግለሰቦች ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅብራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ አመራር አባላት ሁለት የከተማዋን ቢሮዎች እንዲመሩ ተሹመዋል።

የኢዜማ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሲሾሙ፣ የአብን ምክትል ሊቀመንበር አቶ የሱፍ ኢብራሂም የመንግሥት ንብረት አስተዳደር ባለሥልጣን እንዲሆኑ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በካቢኔያቸው ውስጥ አካተዋቸዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለምክር ቤቱ ያቀረቧቸው የካቢኔ አባላት ላይ በተሰጠ ድምጽ 120 ድጋፍ ያገኙ ሲሆን፣ አንድ ተቃውሞና በአራት ድምጸ ተአቅቦ ተመዝግቦ ሹመቱ ጸድቋል።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በተካሄደው ምርጫ ላይ ኢዜማና አብን ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዕጩዎቻቸውን አቅርበው የተወዳደሩ ቢሆንም ለመመረጥ ሳይችሉ ቀርተዋል።

በምርጫው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ያሉት 138 መቀመጫዎችን በሙሉ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ አሸንፎ በብቸኝነት እንደተቆጣጠረው ይታወቃል።

አሸናፊው ብልጽግና ፓርቲ በዚህ ወር በሚመሰርታቸው የክልልና የፌደራል መስተዳደሮች ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን እንደሚያካተት በገባው ቃል መሠረት የአዲስ አበባ መስተዳደርም ሁለት የካቢኔ ቦታዎችን ለተቃዋሚዎች ሰጥቷል።

ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 15/2014 ዓ.ም የተመሠረተው የኦሮሚያ መስተዳደርም በተመሳሳይ የክልሉ ምክር ቤት (ጨፌ) አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባልን የቢሮ ኃላፊ አድርጎ ሾሟል።

ከፌደራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ወደ አዲስ አበባ ቢሮዎች ከመጡት መካከል ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) እና ያደታ ቀነዓ (ዶ/ር) ይገኙበታል።

የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር የነበሩት ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) የአዲስ አበባ የባህል፣ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሲሾሙ፤ የመከላከያ ሚንስትር የነበሩት ያደታ ቀነዓ (ዶ/ር) ደግሞ የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮን እንዲመሩ ተሹመዋል።

በምክር ቤቱ የተሾሙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አባልነት የሚከተሉት ናቸው።

  • ጃንጥራር አባይ ምክትል ከንቲባና የሥራ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ
  • መለስ ዓለሙ የምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ
  • ጥራቱ በየነ የከተማ ሥራ አስኪያጅ
  • ሂክማ ከይረዲን የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ
  • ነጂባ አክመል የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ
  • ያስሚን ወሃቢ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ
  • አለማየሁ እጅጉ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ
  • ተተካ በቀለ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ
  • ቀንዓ ያደታ (ዶ/ር) የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ
  • ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) የባህል፣ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ
  • ጽዋዬ ሙልነህ የፍትህ ቢሮ ኃላፊ
  • ጀማል አልዩ የመሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ
  • ዳዊት የሺጥላ የትራንስፓርት ቢሮ ኃላፊ
  • አያልነሽ ኃ/ማሪያም ዲዶ (ኢ/ር) የዲዛይንና ግንባታ ቢሮ ኃላፊ
  • ሙሉቀን ሀብቱ (ዶ/ር) የቴክኒክ ሙያና የስልጠና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ
  • አደም ኑሪ ዋበላ የንግድ ቢሮ ኃላፊ
  • ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ የጤና ቢሮ ኃላፊ
  • ዘላለም ሙላቱ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ
  • ሀና የሺንጉስ (ዶ/ር) የሴቶች ህፃናትና እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ
  • ሙሉጌታ ተፈራ የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ
  • አብርሃም ታደሰ የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ
  • ዮናስ ዘውዴ የኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ
  • ጽጌረዳ ወርቁ የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ
  • ዳዲ ወዳጆ (ዶ/ር) የፕላን ልማት ኮሚሽን ኃላፊ
  • ግርማ ሰይፉ የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ
  • የሱፍ ኢብራሂም የመንግሥት ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን

ሆነው እንዲመሩ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ቀርበው ሹመታቸው ማክሰኞ መስከረም 18/2014 ዓ.ም ጸድቋል።