ዶ/ር እሌኒ በተመድ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ ያሰበውን አዲስ ዘርፍ በኃላፊነት እንዲመሩ ተመረጡ

ኢትዮጵያዊቷ ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድህን በተባባሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ውስጥ አዲስ የተቋቋመውን አዲስ ዘርፍ በኃላፊነት እንዲመሩ ተመረጡ።

ይህ ዘርፍ ቲምቡክቶ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የግል እና የመንግሥት ሴክተሮችን በማጣመር ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ የተቋቋመ የድርጀቱ አንድ አካል ነው።

ከዚህ ቀደም በተይም የኢትዮጵያ የምርት ገበያን በማቋቋም የሚታወቁት ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድህን በአዲሱ ሹመታቸው "የዲጂታል አብዮትን በማሳለጥ ወጣቶች የአፍሪካን የልማት ተስፋን እንዲመሩ ማስቻል" ቀዳሚ ግባቸው እንደሆነ ተቋሙ በድረረ ገጹ ላይ ይፋ አድርጓል።

ዶ/ር እሌኒም በትዊተር ገጻቸው ላይ በአዲሱ ኃላፊነታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ መጪው የአፍሪካ መልካም ዕጣ ፈንታም በወጣቶች እጅ ነው ሲሉ አክለዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም እንዳለው የዶ/ር እሌኒ ወደ ኃላፊነቱ መምጣት የባለብዙ ተሰጥኦ ባለቤት የሆኑትን አፍሪካዊያን ወጣቶችን የሥራ ፈጠራ አቅም ለመምራት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ሲል በመግለጫው ላይ አስፍሯል።

"ከኮቪድ-19 ቀውስ ለማገገም ጥረት በሚደረግበት በዚህ ወሳኝ ወቅት የግሉ ዘርፍ ብሎም ኢኖቬሽን ትልቅ ሚና ይኖረዋል። የዶ/ር እሌኒ የሞያ ልምድ ይህንን ለመምራት አስተዋጽኦው ትልቅ ነው" ያሉት የተባበሩት መንግሥታት ረዳት ዋና ፀሐፊና የዩኤንዲፒ የአፍሪካ ዳይሬክተር አሁና ኢዚአኮንዋ "ይህንን እድል በማግኘታችንም ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል" ብለዋል።

የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ የሆኑት ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድህን የዓለም ባንክን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በኃላፊነት ሰርተዋል።

እንዲሁም በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ዋጋ ያላቸውን የግብርና ምርቶች የሚያገበያየውን የኢትዮጵያ የምርት ገበያ መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ለዓመታት አገልግለዋል።

ቀጥሎም በስማቸው የሚጠራ ተቋም በመመስረት በምርት ገበያ ዙሪያ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የማማከር ሥራዎች ሰርተዋል። ቀጥለውም ብሉ ሙን የተሰኘ እና ወጣት የሥራ ፈጣሪዎችን የሚደግፍ ተቋም በመመስረት በአዲስ አበባ መቀመጫቸውን አድርገው ሲንቀሳቀሱም ነበር።