ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትውልደ ኤርትራዊቷ በጀርመን ምክር ቤት የመጀመሪያዋ ጥቁር እንደራሴ ሆኑ
ትውልደ ኤርትራዊቷ አወት ተስፋየሱስ በጀርመን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረጡ ጥቁር ሴት የፓርላማ አባል ሆኑ።
በጀርመን የግሪን ፓርቲ አባል የሆኑት አወት ተስፋየሱስ ቡንደስታግ ተብሎ የሚታወቀው የጀርመን የፌደራል ፓርላማ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት እንደራሴ ለመሆን ችለዋል።
የ47 ዓመቷ የሕግ ባለሙያ ፍራንክፈርት እና ካሰል ተብለው በሚጠሩ ከተሞች ውስጥ ነው ተወዳድረው በአገሪቱ የፌደራል ፓርላማ ወንበር አሸናፊ መሆን የቻሉት።
አወት ተስፋየሱስ እአአ 2006 ላይ ከፍራንክፈርት ዩኒቨርስቲ ከተመረቁ በኋላ፤ ስደተኞችን፣ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እየወከሉ በሕግ ሥራ ላይ ተሰማርተው ስለመቆየታቸው የጀርመን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ኤርትራ ውስጥ የተወለዱት አወት ተስፋየሱስ ገና የስድስት ዓመት ልጅ ሳሉ ነበር ከወላጆቻቸው ጋር ወደ ጀርመን ተሰደው በጀርመኗ ሃይደልበርግ ከተማ መኖር የጀመሩት።
ከእአአ 2009 የጀርመን ግሪን ፓርቲ አባል የሆኑት አወት፤ እአአ 2020 ላይ ከፍራንክፈርት ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ አፍቃሪ ናዚ የሆነ አንድ ግለሰብ 11 ሰዎችን ከገደለ በኋላ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን አጠናክረዋል።
ከአንድ ዓመት በፊት በተመሳሳይ ሌላ ትውልደ ኤርትራዊው የኒው ዚላንድ የሕዝብ እንደራሴ አባል ሆኖ መመረጡ በስፋት ተዘግቦ የነበረ ሲሆን፤ ሌላ ትውልደ ኤርትራዊ ኢብራሂም ኦመር በኒው ዚላንድ ታሪክ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ የፓርላማ አባል ሆኖ ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርን ሌበር ፓርቲ በ50 ዓመት ታሪኩ ከፍተኛውን ድል ማግኘቱን ተከትሎ ነው ኢብራሂም ኦመር የኒው ዚላንድ የፓርላማ አባል መሆን የቻለው።
ከዚህ በተጨማሪም በቅርብ ዓመታት በአሜሪካ እና በስዊትዘርላንድ ጠንካራ የፖለቲካ ተሳትፎ ያደረጉ ትውልደ ኤርትራውያን ፖለቲከኞች አሉ።