በምሥራቅ ወለጋ ታጣቂዎች ጥቃት ሰንዝረው እስረኞችን ማስመለጣቸው ተነገረ

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ሳሲጋ ወረዳ ታጣቂዎች በአንድ ፖሊስ ጣቢያ ላይ በፈጸሙት ጥቃት እስረኞችን አስመልጠው በርካታ የፖሊስ አባላትን ማቁሰላቸው ተነገረ።
ቢቢሲ ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ከሆስፒታል ምንጮች ማረጋገጥ እንደቻለው ጥቃቱ የተፈጸመው ማክሰኞ ዕለት ነሐሴ 25/2013 ዓ.ም ነው።
የአካባቢው ባለስልጣናት ጥቃቱን በተመለከተ ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡ ከቢቢሲ ጥያቄያ ቢቀርብላቸውም አስካሁን ያሉት ነገር የለም።
ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር እያለ የሚጠራውና ከወራት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪ ድርጅትነት የተፈረጀው መንግሥት ሸኔ እያለ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጥቃቱን ስለመፈጸሙ አስታውቋል።
በሳሲጋ ወረዳ የጋሎ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አንድ ግለሰብ ጥቃቱን በተመለከተ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ማከሰኞ ረፋድ 3፡30 አካባቢ በከተማዋ የተኩስ ድምጽ መሰማት እንደጀመረ ገልጸዋል።
የተኩስ ልውውጡም በአካባቢው በነበሩ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና ታጣቂዎቹ መካከል መሆኑን እና ይህም እስከ እኩለ ቀን መቀጠሉን ይናገራሉ።
ታጣቂ ቡድኑ ጥቃት የፈጸመው በሳሲጋ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ሲሆን በዚህም ጥቃት እስረኞችን ማስመለጡን ነዋሪው ይናገራሉ።
"ከእስር ቤቱ ያመለጡ ስድስት ሰዎች እኔ ወደ ምሠራበት ቦታ ሸሽተው ገብተው ነበር። ክፍት በር ሲያገኙ ነው ዘልቀው የገቡት። ከዚያ በኋላ ወጥተው ሄዱ። እኔም የሥራ ቦታዬን ዘግቼ ከአካባቢው ሄድኩ" በማለት የገጠማቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ በተረጋገጠው የትዊተር ገጽ ላይ ቡድኑ በሳሲጋ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት ስለመፈጸሙ አስፈሯል።
በዚህም ጥቃት "ከ100 በላይ የፖለቲካ እስረኞች ተለቀዋል" ብሏል።
ቢቢሲ ከእስር ያመለጡ እስረኞችን ትክክለኛ ቁጥር ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።
ጥቃቱን ተከትሎ በቁጥር ከ40 በላይ የሚሆኑ የአካባቢው የፖሊስ አባላት ላይ የተለያየ ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና ወደ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል መምጣታቸውን ከሆስፒታሉ ማረጋገጥ ተችሏል።
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሆስፒታሉ ሠራተኛ "ከሳሲጋ ጉዳት የደረሰባቸው የፖሊስ አባላት ይመጣሉ ተብለን ስንጠባበቅ ነበር" ብለዋል።
በተጨማሪም፤ "በጥይት እንደተመቱ ነው የሚናገሩት (ጉዳት የደረሰባቸው የፖሊስ አባላት)፤ እኛም ጉዳት የደረሰባቸው በጥይት ተመትተው መሆኑን አረጋግጠናል" ይላሉ።
ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ስድስት የፖሊስ አባላት ቀዶ ሕክምና እንደተደረገላቸው እና ሌሎች ስምንት የፖሊስ አባላትም የቀዶ ሕክምና እንደሚደረግላቸው መሆኑን የሆስፒታሉ ሠራተኛ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በተጨማሪም "ስድስት ሰዎች ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ሪፈር ተብለዋል" በማለት ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ሌላ የጤና ተቋም የተላኩ የፖሊስ አባላት መኖራቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።
በዚህ ጥቃት ሕይወቱ ያለፈ የፖሊስ አባል ስለመኖሩ እስካሁን ማወቅ አልተቻለም።
የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ ስለጉዳዩ ተጠይቀው "እኔ አላውቅም። በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ የለኝም" በማለት ዛሬ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።
ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር እያለ የሚጠራው እና መንግሥት "ሸኔ" የሚለው ታጣቂ ቡድን በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥት ባለሥልጣናት እና የጸጥታ አካላት ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲሰነዝር ቆይቷል።
ከጥቂት ወራት በፊት የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በዚህ ታጣቂ ቡድን 112 የፖሊስ አባላት፣ 57 የሚሊሻ አባላት እና በተለያየ ደረጃ የሚገኙ 18 ባለሥልጣናት መገደላቸውን አስታውቆ ነበር።
በተጨማሪም በአካባቢዎቹ በተለያዩ ጊዜያት በንጹሃን ነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ከተፈጸሙ የጅምላ ግድያዎች ጋር በተለያያዘ ክስ ሲቀርብበት ቆይቷል።
ከሳምንት በፊት በምስራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ ከ100 በላይ ንጹሃን ሰዎች የቡድኑ ታጣቂዎች ናቸው በተባሉ ጥቃት ፈጻሚዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣት መግለጫ አስታውቆ ነበር።
እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጣራውና መንግሥት ሸኔ የሚለው ይህ ታጣቂ ቡድን ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በሰሜን ኢትዮጵያ ከባድ ጦርነት ውስጥ ከሚገኘው ከህወሓት ጋር በጋር ጸረ መንግሥት እንቅስቃሴ ለማድረግ መስማማቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።












