ቻይና ለ6 ዓመት ልጆች የጽሁፍ ፈተና እና የቤት ሥራ እንዳይሰጥ አገደች

ተማሪዎች በክፍል ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና ለስድስት እና ለሰባት ዓመት ህጻናት ተማሪዎች የጽሁፍ ፈተና እንዳይሰጥ ማገዷን አስታወቀች።

ይህ ውድድር በበዛበት ትምህርት ሥርዓት ውስጥ በተማሪዎችና በወላጆች ላይ የሚፈጥረውን ጫና ለማቃለል የተወሰደ እርምጃ ነው ተብሏል።

ውሳኔው በቻይና የትምህርት ዘርፍ እየተወሰደ ያለው ሰፊ የማሻሻያ አካል ነው።

ከዚህ ቀደም ተማሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከገቡ ከመጀመሪያው ዓመት አንስቶ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና እስከሚወስዱበት 18 ዓመታቸው ድረስ ፈተና መውሰድ ይጠበቅባቸው ነበር።

ነገር ግን ይህ ጫና የተማሪዎቹን "አካላዊና አዕምሯዊ ጤና" እየጎዳ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ሚኒስቴሩ በመግለጫው "ፈተናዎች የትምህርት ቤት ሥርዓት አካል ሲሆኑ አስፈላጊም ናቸው፤ ነገር ግን አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በርካታ ፈተና ይሰጣሉ። ይህም በልጆቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና ይፈጥራል። በመሆኑም መስተካከል አለበት" ብሏል።

መመሪያው አንድ ትምህርት ቤት በአንድ ወሰነ ትምህርት ሊያዘጋጃቸው የሚችለውን የፈተናዎች ብዛትም ይገድባል።

"የአንደኛ እና የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች ጽሁፍ ላይ የተመሰረተ ፈተና መውሰድ አይጠበቅባቸውም። በሌሎች ክፍሎች ግን ትምህርት ቤቶች በየወሰነ ትምህርቱ ማጠቃለያ ላይ ፈተና መስጠት ይችላሉ። ለመካከለኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በየወሰነ ትምህርቱ ማጠቃለያ እና አጋማሽ ፈተናዎችን መስጠት ይፈቀዳል" ብሏል ሚኒስቴሩ።

ከዚህም በተጨማሪ ትምህርት ቤቶች ለሁሉም የአንደኛ ደረጃ ክፍል ተማሪዎች ክልላዊ አሊያም የመግቢያ ፈተና መስጠት እንደማይፈቀድ ገልጿል።

ሚኒስቴሩ አክሎም ያልተመረቁ የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሳምንታዊ፣ የትምህርት ማጠቃለያ እና ወርሃዊ ፈተናዎች መውሰድ አይጠበቅባቸውም ብሏል።

ይህ ብቻም ሳይሆን 'ትምህርታዊ ምርምር' በሚል ሌላ ስያሜ የሚሰጡ ፈተናዎችም አይፈቀዱም።

በዚህ መመሪያ ላይ የቻይና ማኅበራዊ ሚዲያ 'ዌቦ' ተጠቃሚዎች የተለያዩ ሃሳቦችን እያንፀባረቁ ነው።

አንዳንዶች ውሳኔው በህጻናት ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ለመጓዝ የሚያስችል አንድ እርምጃ ነው ብለዋል።

ሌሎች ደግሞ ትምህርት ቤቶች ያለ ፈተና የተማሪዎችን ችሎታ እና እውቀት እንዴት መመዘን ይችላሉ ሲሉ ጠይቀዋል።

የቻይና የትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ዓመት ለአንደኛ ክፍል ተማሪዎች የቤት ሥራ እንዳይሰጥም አግዷል። እንዲሁም ለመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ደግሞ የሚሰጠው የቤት ሥራ መጠን ይኑረው ሲል 1 ሰዓት ከ50 ደቂቃ ያህል ለምሽቱ ሥራቸው በቂ ነው ማለቱን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

ሐምሌ ወር ላይ ቤይጂንግ በአገሪቷ መሠረታዊ የትምህርት ዓይነቶችን በኦንላይን በማስተማር ትርፍ ለማግኘት የሚሰሩ የኦንላይን ቲቶሪያል [አጋዥ ትምህርት] የሚሰጡ ድርጅቶችን ዘግታ ነበር።

በወቅቱ እርምጃው ቻይና ዝቅተኛ የውልደት ምጣኔ ካስመዘገበች በኋላ ወላጆች ልጆችን ለማሳደግ የሚያጋጥማቸውን የገንዘብ ጫና ለማቃለል ባለሥልጣናት የወሰዱት ተደርጎ ነበር የተወሰደው።

አዲሱ መመሪያም በትምህርት ዘርፉ ላይ የውጭ ኢንቨስትመንት እና ከማሻሻያው በፊት 120 ቢሊየን ዶላር የሚገመቱ የግል አጋዥ ትምህርት ሰጭ ተቋማትንም ሥራ ገድቧል።