በጣልያኗ ደሴት ከ500 በላይ ስደተኞችን መታደግ እንደተቻለ ተገለጸ

በጣልያን የሚገኙ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, EPA

የጣልያን የባሕር ጠረፍ ጠባቂ መርከቦች ላምፔዱዛ ደሴት ላይ እየተንሳፈፈ ካለ የዓሣ ማጥመጃ ጀልባ ላይ 539 ስደተኞችን ማዳናቸውን አስታውቀዋል።

ቅዳሜ ዕለት የተደረገው የማዳን እርዳታ በአንድ ቀን ውስጥ እጅግ በጣም ብዙ ስደተኞችን ወደ ጣልያኗ ደሴትም ያስገባ ነው ተብሏል።

በጀልባው ውስጥ ከተሳፈሩት ውስጥ ሴቶችና ሕፃናት እንደነበሩበትም ተገልጿል። ከሊቢያ በሜድትራኒያን ባህር አቋርጠው ከተጓዙት ስደተኞች መካከል አንዳንዶቹ የነውጠኝነት ባህርይ ታይቶባቸዋል ተብሏል።

የጣልያን ዓቃብያነ ሕግ በአጠቃላይ ሁኔታው ላይ እንዴት ተፈጠረ የሚለውን ለማወቅ ምርመራ ከፍተዋል።

ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን ወይም ኤምኤስኤፍ ተብሎ የሚጠራው ድርጅትን ወክለውም ዶክተር አሊዳ ሰርራቺሪ ወደ አውሮፓ ለመሄድ ጀልባ በመጠባበቅ ላይ እያሉ በሊቢያ ውስጥ አካላዊ ጥቃት የደረሰባቸው በርካታ ስደተኞች እንዳሉም ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪ መርማሪዎቹ ስደተኞቹ በሊቢያ በሐሰት የታሰሩ ሊሆኑ የሚችሉበትን ሁኔታ እየተመለከቱ መሆኑን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ስደተኞቹን ወደ ላምፔዱዛ ለማጓጓዝ ሁለት የባህር ዳርቻ ጠባቂ መርከቦች እና የጉምሩክ ጀልባ ከጣሊያን የገንዘብ ወንጀሎች ፖሊስ ጋርዲያ ዲ ፋንዛ ጋር ተጣምረው ተባብረዋል ተብሏል።

የደሴቲቱ ከንቲባ ቶቶ ማርቲሎ የዳኑትን ስደተኞች አስመልክቶ "ከቅርብ ጊዜያት ውስጥ ከተፈፀሙ ትላልቅ ስራዎች አንዱ" ሲሉ አሞካሽተዋል።

ላምፔዱዛ ወደ አውሮፓ ለመድረስ ከሚጓዙ ስደተኞች መካከል በዋናነት የሚረግጧት መዳረሻ ናት።

በግንቦት ወር ከ 1ሺህ በላይ ስደተኞች በጣሊያን ደሴት ላይ በጥቂት ሰዓታት ልዩነት ውስጥ መድረሳቸው ተገልጿል።

ደሴቲቱ ከ300 ያነሱ ሰዎችን ለመቀበል የስደተኞች ካምፕ ቢኖራትም በአሁኑ ውስጥ በደሴቲቱ ያለው የስደተኛ ቁጥር ከአምስት እጥፍ በላይ ነው። በርካቶችም አቧራሟ በሆነው መንገድ አካባቢ የሚገኙ ሲሆን የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ከሌለው አገራትም እንደሚመጡ ተገልጿል።