የብራዚሉ ፕሬዝደንት' እገደላለሁ፣ እታሠራለሁ አሊያም ድጋሚ እመረጣለሁ' ሲሉ ተነበዩ

ቦልሶናሮ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የብራዚሉ ፕሬዝደንት ጃይር ቦልሶናሮ የወደፊቱ እጣ ፈንታዬ ከመገደል፣ አሊያም ከመታሠር ካልሆነ ደግሞ ድጋሚ ከመመረጥ የሚዘል አይደለም ሲሉ ተደምጠዋል።

ሕዝባዊው ቀኝ ዘመም የብራዚል መሪ ቦልሶናሮ በሚቀጥለው ዓመት ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ይጠብቃቸዋል።

ፕሬዝደንቱ ከግራ ዘመሙ ተቀናቃኛቸው የቀድሞው ፕሬዝደንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ከባድ ግጥሚያ ይጠብቃቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ነገር ግን እስካሁን በተደረጉ የቅድመ ምርጫ ድምፅ ስብሰባዎች ቦልሶናሮ ዳ ሲልቫን እየመሩ እንደሆነ እያሳዩ ነው።

"የኔ ዕጣ ፈንታዎች ሶስት ናቸው። መታሠር፣ መገደል አሊያም ድል" ሲሉ ለኢቫንጀሊካል ኃይማኖት መሪዎች ተናግረዋል።

ነገር ግን የቀድሞው ወታደር እሥር የሚባል ነገር አይነካኝም፤ ምክንያቱም "እኔን ሊያስፈራራኝ የሚችል ማንም የለምና" ብለዋል።

ቦልሶናሮ ከሶስት ዓመታት በፊት በተደረገው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ወቅት ቅስቀሳ ላይ ሳሉ በጩቤ መወጋታቸው ይታወሳል።

ከስለት ተርፈው መንበረ ፕሬዝደንትቱን የተቆጣጠሩት ቦልሶናሮ ከሃገሪቱ የሕግ ሰዎችና ከምርጫ ቦርድ ሰዎች ጋር ስምምነት ላይ ሊደርሱ አልቻሉም።

በሚቀጥለው ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ ለመመረጥ እያማተሩ ያሉት የ66 ዓመቱ ፕሬዝደንት የብራዚል ኤሌክትሮኒክ መምረጫን ሥርዓትን ሲነቅፉ ነበር።

ቦልሶናሮ የሚቀጥለውን ዓመት ምርጫ ውጤት ላይቀበሉ እንደሚችሉ ሲዝቱ ነበር።

ባለፈው ረቡዕ የብራዚል ምርጫ ቦርድ ኃላፊ የመመረጫ ሥርዓቱ ምንም ችግር የለበትም ሲሉ ተደምጠው ነበር።

ነገር ግን ትላንት ቅዳሜ ከኢቫንጀሊካል መሪዎች ጋር ስብሰባ የነበራቸው ቦልሶናሮ አሁንም የመምረጫ ሥርዓቱን ከመንቀፍ ወደኋላ አላሉም።

አነጋጋሪው የብራዚል ፕሬዝደንት የኮሮኖቫይረስ በሽታን አስመልክቶ በሚሰጧቸው አወዛጋቢ አስተያየቶችም ይታወቃሉ።

ወረርሽኙ ብራዚል ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ቀጥፏል።