በካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ተጨማሪ ጥቃት ሊኖር እንዲሚችል ፕሬዚዳንት ባይደን አስጠነቀቁ

ጣሊያኖች ከካቡል ሲወጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ሌላ ተጨማሪ ጥቃት የመድረሱ አዝማሚያ በጣም ከፍተኛ ነው ሲሉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስጠነቀቁ።

የጦር አዛዦች እስከ ሳምንቱ መጨረሻ እሁድ ሊከሰት እንደሚችል ነግረውኛል ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሁሉም የአሜሪካ ዜጎች ከአውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ያለውን ቦታ ለቀው እንዲወጡ በበማለት "ልዩ ፣ ተዓማኒ ሥጋት" አለ ሲል አሳስቧል።

አሜሪካ አሁንም ቢሆን ከአፍጋኒስታን ሙሉ በሙሉ ያልወጣች ሲሆን ቀስ በቀስም እየወጣች እንደሆነ አስታውቃለች።

ነገር ግን የመጨረሻዎቹ የእንግሊዝ ወታደሮች ፣ ዲፕሎማቶች እና ባለሥልጣናት በአሁኑ ወቅት ካቡልን ለቀው ወጥተዋል።

በያዝነው ሳምንት ሐሙስ ዕለት በአውሮፕላን ማረፊያው አቅራቢያ በአጥፍቶ ጠፊ በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ የ170 ሰዎች ህይወት አልፏል።

የአካባቢው የእስላማዊ መንግሥት ቡድን ቅርንጫፍ እስላማዊ መንግሥት በኮራሳን ግዛት (አይ ኤስ -ኬ) ጥቃቱን ማድረሱን አምኗል።

አሜሪካ በበኩሏ በወሰደችው አፀፋዊ እርምጃ በምዕራብ አፍጋኒስታን ላይ "የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት" የፈፀመች ሲሆን በዚህም ሁለት "ከፍተኛ" የአይ ኤስ ኬ አባላትን እንደገደለች አስታውቃለች።

የተገደሉት ሁለቱ ግለሰቦች ዕቅድ አውጪ እና አሳላጭ ነበሩ ተብለዋል ። ሆኖም የካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ጥቃትን ለማቀድ በቀጥታ ተሳታፊ ስለመሆናቸው ግልፅ አይደለም።

ፕሬዚዳንት ባይደን ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫ "ይህ ጥቃት የመጨረሻ አይደለም። በዚያ አሰቃቂ ጥቃት የተሳተፈ ማንኛውም ሰው እናድናለን ዋጋውንም እንሰጠዋለን" ሲሉ አሳስበዋል።

አይ ኤስ-ኬ በአፍጋኒስታን ከሚገኙት የጂሃዲስት ታጣቂ ቡድኖች ሁሉ እጅግ ጽንፈኛ እና በነውጠኛነቱ የሚታወቅ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ አፍጋኒስታንን ከሚቆጣጠሩት ታሊባን ጋር ከፍተኛ ልዩነት እንዳለውም ይነገራል።

ቡድኑ ታሊባኖች ከአሜሪካኖች ጋር በድርድር የሰላም እልባት በማግኘታቸውና የጦር ሜዳውን በመተው ይከሳቸዋል።

ታሊባኖች በበኩሉ አሜሪካ የፈፀመችውን የአየር ድብደባ አውግዘው አሜሪካውያን በመጀመሪያ እነሱን ማማከር ነበረባቸው ሲሉ አንድ ቃል አቀባይ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።