ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካዊው ራፐር ካንዬ ዌስት ስሙን ዬ ወደሚል ሊቀይር ነው
ታዋቂው ራፐር ካንዬ ዌስት ስሙን ዬ ወደሚል ፊደል በይፋ ለመቀየር ህጋዊ ሂደቱን መጀመሩ ተዘግቧል።
በሎስ አንጀለስ በቀረቡት የፍርድ ቤት ሰነዶች ውስጥ እንደተጠቀሰው ራፐሩ ስሙን ለመቀየር "የግል ምክንያቶች" በሚል አስቀምጧል።
ይህ የሙዚቃ ኮከብ ፣ የፋሽን ዲዛይነር እና በአንድ ወቅት ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ያወጀው ካንዬ ዌስት ስሙን ለመቀየር ያሰበው 'ዬ' የሚል የሙዚቃ አልበም ማውጣቱን ተከትሎ ከሶስት አመታት በፊት ነው።
በአሁኑ ወቅት 'ዬ' የሚለውን መጠሪያ ከመውሰዱ በፊት "ዘ ቢንግ" የሚል መጠሪያም እንደሚወስድ አስታውቆ ነበር።
የ 44 ዓመቱ ራፐር የአሁኑን ስሙን አሕጽሮተ ቃል ለመጠሪያው ከማድረጉ በፊት ስሙ ለእርሱ ሃይማኖታዊ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
ካንዬ ዌስት በ አውሮፓውያኑ 2018 ከሬዲዮ አስተናጋጅ ቢግ ቦይ ጋር የአልበሙን ርዕስ አስመልክቶ ሲወያዩ ‹እኔ› (ዬ) የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዛት ጥቅም ላይ የዋለው ቃል ነው።
እናም መፅሃፍ ቅዱስ እና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ "ዩ" እናንተ የሚለውን የሚገልፅ ነው ብሎ ነበር።
"ስለዚህ እኔ አንተን ነኝ ፣ እኔ እኛ ነን፤ እኛ ነን እኮ። ካንዬ ከሚለው ትርጉሙም ብቸኛ ወደ ዬ ብቻ መሄዱ የጥሩነታችን ፣ የመጥፎነታችን ፣ ግራ የተጋባ ስብዕናችን ፣ የሁሉ ነገር ነፀብራቅ መሆኑን ነው" ይላል
ራፐሩ በእናቱ ዶንዳ ስም የተሰየመውንና ቀጣይ አልበሙን ይለቀቃል ከተባለበት ጊዜ ቢዘገይም ከሰሞኑ ሊወጣ መሆኑ ተነግሯል።
በአሁኑ ወቅት ከኪም ካርዳሺያን ጋር በፍቺ ሂደት ያለው ራፐሩ በአውሮፓውያኑ 2020 ውስጥ 60 ሺህ ድምጾችን ማግኘቱን ተከትሎ በ2024 ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለመወዳደር ያለውን ፍላጎት ገልጿል።