ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት አገልግሎቶችን ላልተወሰነ ጊዜ አገደ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲታገዱ ውሳኔ ማስተላለፉን የአስተዳደሩ ከንቲባ ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመሬት አስተዳደር ተቋማት ለመሠረተ ልማት ቅንጅት እና ግንባታ ፈቃድ ባለስልጣን እንዲሁም ለ11ዱም ክፍለ ከተሞች ባስተላለፈው ትዕዛዝ መሰረት ከነሐሴ 7፣ 2013 ጀምሮ የመሬት እና መሬት ነክ አገልግሎቶች ላልተወሰነ ጊዜ መታገዱን አስተዳደሩ በማህበራዊ ገፁ በትናንትናው ዕለት ካወጣው መረጃ መረዳት ተችሏል።
አስተዳደሩ ዕግዱን ያስተላለፈው በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ አመራሮች በአሁኑ ወቅት ትኩረታቸው ወቅታዊ በሆነው ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ በማድረጋቸውና ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም አንዳንድ ብልሹ ስራዎቹን በመመልከቱ ነው።
"አንዳንድ ስግብግብ ግለሰቦች ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታውን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአቋራጭ ለመክበር በመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት በማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ በመገንዘቡ ነው።" በማለት መግለጫው አስፍሯል።
ከዚህም ጋር ተያያዞ ማንኛውም የመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶች ማለትም መሸጥ ፣ መለወጥ፣ ካርታ ማውጣት፣ ስም ዝውውርና ሌሎች አገልግለቶች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲታገድ ውሳኔ ላይ ተደርሷል።
በስድስቱም የመሬት ነክ ተቋማት ፣በ11ዱም ክፍለ ከተሞች እና የመሠረተ ልማት ቅንጅት እና ግንባታ ፈቃድ ባለስልጣን የመሬት አገልግሎቶችን እንዳይሰጡ ወሳኔም መተላለፉ ተገልጿል።