በሩዋንዳ መንግሥት ስፖንሰር በሚደረገው የአርሰናል ክለብ ሽንፈት ፕሬዚዳንት ካጋሜ ብስጭታቸውን ገለፁ

የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት እና የአርሰናሉ ደጋፊ ፖል ካጋሜ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን መክፈቻ ቀን በክለቡ አስደንጋጭ ሽንፈት ብስጭታቸውን ገልፀዋል።

ለ74 ዓመታት ያህል በከፍተኛ ሊጎች ውስጥ ያልነበረው ብሬንትፎርድ አርሰናልን 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በሩዋንዳ መንግሥት ስፖንሰር የሚደረገው አርሰናል ክለብን በተመለከተ ፕሬዚዳንት ካጋሜ ስለ መድፈኞቹ በርካታ ጊዜ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

አርብ ዕለት ከተደረገው ጨዋታ በኋላ ፕሬዚዳንት በትዊተር ገፃቸው "ለሁኔታዎች ይቅርታ እያደረግን ወይም የማይረቡ ነገሮችን መቀበል የለብንም። አንድ ቡድን መገንባት ያለበት ለማሸነፍና ለማሸነፍ ዓላማ ብቻ ነው" ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ በሁለት ተጨማሪ የትዊተር መልዕክቶቻቸው ክለቡ ስኬታማ የሚያደርገውን ዕቅድ እንዲያመጣ የጠየቁ ሲሆን "አድናቂዎች እንዲህ አይነት ሁኔታዎችን መልመድ አይገባቸውም" ብለዋል።

ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ የሩዋንዳ መንግሥት ከ 42 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ከክለቡ ጋር አድርጓል። ይህም በአርሴናል የመለዮ ሸሚዝ እጀታ ላይ የሚታየውን "ሩዋንዳን ጎብኙ" አርማ ያካትታል።

ተቺዎች ለሀብታም የእግር ኳስ ክለብ ድጎማ የሚሰጡ የደሃ አፍሪካዊት ሀገር አምባገነናዊ መሪ ምሳሌ ናቸው ቢሉም ነገር ግን የሩዋንዳ መንግሥት በበኩሉ የስፖንሰር ገቢው በቀጥታ ከሚገኘው በቱሪዝም ገቢው ነው በማለት ይከራከራል።

በፕሬዚዳንት ካጋሜ አገዛዝ ዘመን ወደብ አልባዋ አገር በአውሮፓውያኑ 1990 ዎቹ ከተከሰተው የብሔር ግጭትና ዘር ማጥፋት አገግማለች።

በአውሮፓውያኑ 2018 የዓለም ባንክ ሃገሪቱ እያከናወነች ያለውን "አስደናቂ የልማት ስኬቶች" አመስግኗል።

ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ በፖለቲካ እና በሰብአዊ መብቶች አያያዝ በአገር ውስጥ እና በውጭ ትችት ይገጥማቸዋል።