ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሄይቲ በተከሰተ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢያንስ 304 ሰዎች ሞቱ
በካሪቢያኗ ደሴት በሄይቲ በተከሰተው ከፍተኛ ርዕደ መሬት ቢያንስ 304 ሰዎች ሲሞቱ ከ1 ሺህ 800 በላይ መቁሰላቸው ተገልጿል።
የተከሰተው የመሬት ርዕደት በሬክተር መለኪያ 7.2 ሲሆን በምዕራባዊቷ የአገሪቱ ክፍሎችም አብያተ ክርስቲያናትን እና ሆቴሎችን ጨምሮ ህንፃዎችንም በትናንትናው ዕለት አፍርሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል" ሲሉ ለአንድ ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል።
ሄይቲ በአሁኑ ወቅት በአውሮፓውያኑ 2010 ከተከሰተውና ክፉኛ ከተባለው የመሬት መንቀጥቀጥ እያገገመች ነው።
የዩናይትድ ስቴትስ የጂኦሎጂ ጥናት (USGS) እንደገለጸው የቅዳሜው የርዕደ መሬት ማዕከል የሆችው ስፍራ ከሴንት ሉዊስ ዱ ሱድ 12 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ ናት።
ርዕደ መሬቱ በርካታ ህዝብ በሚኖርበትና 125 ኪሎ ሜትር ርቀት የምትገኘውን ፖርት ኦው ፕሪንስን ጨምሮ በአጎራባች ግዛቶች ተሰምቷል ተብሏል።
"ብዙ ቤቶች ወድመዋል ፣ ሰዎች ሞተዋል ፣ አንዳንዶቹም ሆስፒታል አሉ።" በማለት ርዕደ መሬቱ በተከሰተበት አቅራቢያ የሚኖሩት ክሪስቴላ ሴንት ሂላየር ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አሪኤል ሄንሪ የአስቸኳይ ዕርዳታውን ለመሥራት አንድ ቡድን ማሰባሰባቸውን ተናግረዋል።
"መሰረታዊውና አስቸኳዩ ነገር በተቻለ መጠን የተረፉትን ከፍርስራሹ ስር ማዳን ነው" ብለዋል።
አክለውም "የአካባቢው ሆስፒታሎች በተለይም የሌስ ካይስ ቁስሎች በቆሰሉና በደም በተለወሱ ሰዎች እንደተጨናነቁ ለማወቅ ችለናል" ብለዋል።
ሚስተር ሄንሪ በካይስ ከተማ ላይ በአውሮፕላን መብረራቸውን ገልፀዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሄይቲን ለመርዳት ፍቃድ የሰጡ ሲሆን እና የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) "ጉዳቱን ለመገምገም እና የተጎዱትን እና አሁን እንደገና መገንባት ያለባቸውን ለማገገም ጥረቶችን ለማገዝ ይሠራል" ብለዋል።