ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በህክምና ትምህርት ቤት የጓደኛውን አስከሬን ለመማሪያነት ያየው ናይጄሪያዊ
ከአፍሪካ ፀሐፊያን ደብዳቤዎች በሚለው በቢቢሲ አፍሪካ ላይ ከሚቀርቡ ጽሁፎች መካከል ናይጄሪያዊው ጋዜጠኛ እና ደራሲ አዳዎቢ ትሪሲያ ኑዋባኒ ወደ አገሪቱ የሕክምና ትምህርት ቤቶች ከተላኩ አንዳንድ "ጠያቂ የሌላቸው" አስከሬኖች በስተጀርባ ስላለው አስጨናቂ እውነታ ጽፈዋል።
የአናቶሚ ተማሪ እንያ እግቤ አንድ አስከሬን ለመማሪያነት ቀርቦ ተጠግቶ እንዲያይ ሲነገረው ተረብሾ እያለቀሰ ክፉሉን ለቆ ወጣ።
ወጣቱ አስከሬን ማየቱ አልነበረም የረበሸው፤ ለአንድ የህክምና ተማሪም የሰከነ ምላሽ አልነበረም።
የ26 ዓመቱ ወጣት ከሰባት ዓመት በፊት በናይጄሪያ ካላባር ዩኒቨርሲቲ የተፈጠረው ነገር ትናንት የሆነ ይመስል ፍንትው ባለ መልኩ ነው የሚያስታውሰው።
ዕለቱ ሐሙስ ነበር አብረውት ከሚማሩት ተማሪዎች ጋር ከሦስት ጠረጴዛዎች ፊት አንድ አስከሬን ተቀመጠ። ከደቂቃዎችም በኋላ ተማሪው ጮክ እያለቀሰ ከክፍሎ ወጥቶ መሮጥ ጀመረ።
ተማሪዎቹ ሊመራመሩትና ሊቆራርጡት እያዘጋጁት የነበረው አስከሬን ከሰባት ዓመታት በላይ የልብ ወዳጁ የሆነው ዲቫይን ነው።
"የምሽት ክለቦች አብረን እንወጣ ነበር" በማለት ነገረኝ "በደረቱ በቀኝ በኩልም በሁለት ጥይቶች ተመትቷል።"
የጓደኛውን አስከሬን ተመልክቶ በድንጋጤ እያለቀሰና እየሮጠ ሲወጣ ከተከተሉት ተማሪዎች አንዷ ኦይፎ አና ነበረች።
"በትምህርት ቤት ውስጥ ለመማሪያነት የምንጠቀምባቸው አብዛኛዎቹ አስከሬኖች በጥይት የተመቱ ነበሩ። አንዳንድ ሰዎች እውነተኛ ወንጀለኞች ላይሆኑ እንደሚችሉ ስገነዘብ በጣም አዝን ነበር" ብላለች አይፎ አና።
በአንድ ጠዋትም በርካታ በደም የተጨማለቁ አስከሬኖች በፖሊስ መኪና ተጭነው ወደ ህክምና ትምህርት ቤት ሲመጡም አይታለች።
እንያ እግቤ የጓደኛውን ዲቫይን አስከሬን ካየ በኋላ ለጓደኞቹ ቤተሰቦች አሳወቃቸው። የሚያሳዝነው ነገር ዲቫይንና ሁለት ጓደኞቹ በምሽት በደኅንነት ወኪሎች መታሰራቸውን ተከትሎ ደብዛቸው በመጥፋቱ ቤተሰቡ በየፖሊስ ጣቢያው እየፈለጉ ነበር።
ቤተሰቡ በመጨረሻ አስከሬኑን መልሶ ማግኘት ችሏል።
እንያ እግቤ የጓደኛውን አስከሬን በዚህ አስደንጋጭ ሁኔታ ማግኘቱ በአንድ በኩል በናይጄሪያ ውስጥ ለህክምና ተማሪዎች የአስከሬን እጥረት መኖሩን በሌላ በኩል በፖሊስ ጭካኔ ሰለባ የሆኑ ሰዎች መድረሻቸውን ያሳየ ነበር።
በ16ኛው እና በ19ኛው ክፍለ ዘመን መካከል በእንግሊዝ ውስጥ የተገደሉ ወንጀለኞች ለህክምና ትምህርት ቤቶች መማሪያነት እንዲውሉ የተለያዩ ሕጎች ይፈቅዱ ነበር። ይህ ደግሞ የሳንይንስን ምክንያት የደገፈ ቅጣት ነው ተብሎም ነበር።
በናይጄሪያም ያለው ሕግ ባለቤት የሌላቸው አስከሬኖችና በመንግሥት መካነ መቃብር ያሉ አስከሬኖች ለህክምና ትምህርት ቤት እንዲሰጡ ያዛል።
ከዚህም በተጨማሪም መንግሥት በሞት የቀጣቸውን ወንጀለኞች አስከሬንም ለህክምና ትምህርት ቤቶች መስጠት ይችላል። ነገር ግን የሞት ቅጣት ለመጨረሻ ጊዜ የተፈፀመው በአውሮፓውያኑ 2007 ነው።
በናይጄሪያ የሕክምና ትምህርት ቤቶች ለማስተማሪያነት የሚውሉት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት አስከሬኖች "በጥይት የተገደሉ ወንጀለኞች" እንደሆኑ የ2011 ምርምርን ተመርኩዞ ክሊኒካል አናቶሚ የተባለው የሕክምና መጽሔት አስፍሯል።
እውነታው ግን እነዚህ ግለሰቦች በፀጥታ ኃይሎች ተጠርጥረው በጥይት የተገደሉ ናቸው። እነዚህ በጥይት የተገደሉት ግለሰቦች ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 40 ዓመት ሲሆናቸው፣ 95 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች ሲሆኑ ከአራቱ ሦስቱ ደግሞ የታችኛው የማኅበራዊ-ኢኮኖሚ ክፍል አካል ናቸው።
ጥናቱን በጋራ የጻፉት በናይጄሪያ ዩኒቨርስቲ የአናቶሚ ፕሮፌሰር የሆኑት ኢሜካ አኒያኑ "ከ10 ዓመታት በኋላ ምንም የተለወጠ ነገር የለም" ብለዋል።
'የአምቡላንስ ግዴታ'
ባለፈው ዓመት የናይጄሪያ መንግሥት የፖሊስ ጭካኔ የተሞላበትን ክስ ለመመርመር በተለያዩ ግዛቶች የፍትህ ማጣሪያዎችን አቋቁሟል።
ይህም በደቡብ ዴልታ ግዛት ልዩ ፖሊስ የሆነው የፀረ-ዘረፋ ቡድን (ሳርስ) አንድ ወጣት መግደሉን የሚያሳይ ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎ ለተነሳው ተቃውሞ ምላሽ ነበር።
በእነዚህ የፍትህ ማጣሪያዎች ላይ የመሰከሩት በርካታ ግለሰቦችም በደኅንነት ወኪሎች ስለተወሰዱ ዘመዶቻቸውና ደብዛቸውም ስለመጥፋቱ መስክረዋል።
ፖሊስ በበኩሉ ደብዛቸው የጠፉ ግለቦች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ መገደላቸውንና ፖሊስም ራሱን ለመከላከል ያደረገው ነው ብለዋል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ፍራንክ ምባ እንዳሉት ፖሊስ እነዚህን አስከሬኖች ለህክምና ትምህርት ቤት መሰጠታቸውን ወይም በመንግሥት የቀብር ስፍራ መቀበራቸውን እንደማያውቁ ተናግረዋል።
በኤንጉ ግዛት ውስጥ ለፍትህ አጣሪ ፓናሉ ከቀረቡ ምስክርነቶች ውስጥ የ36 ዓመቱ ነጋዴ ቼታ ንናማኒ በአውሮፓውያኑ 2009 በሳርስ ቁጥጥር ስር በዋለባቸው በአራት ወራት ውስጥ የፀጥታ ኃይሎች ያሰቃይዋቸውንና የገደሏቸውን ግለሰቦች አስከሬኖች ለማስወገድ የደኅንነት ወኪሎቹን እንደረዳ ተናግሯል።
ምስክሩ በአንድ ምሽት ሦስት አስከሬኖችን በመኪና ላይ እንዲጭን ተጠይቆ ነበር፣ ይህም በእስር ቤት ቋንቋ "የአምቡላንስ ግዴታ" በመባል ይታወቃል።
ከዚያም ፖሊሱ ነጋዴውን በሰንሰለት አስሮ በመኪና በአቅራቢያው ወደሚገኘው የናይጄሪያ የማስተማሪያ ሆስፒታል (ዩኤንኤቲ) የሄዱ ሲሆን ቼታ ንናማኒ አስከሬኖቹን ከመኪና አውርዷል። ከዚያም በአስከሬን ሠራተኞች ወደ ውስጥ ሲወሰዱ አይቷል።
ነገር ግን ከትንሽ ጊዜ በኋላ ቼታ ንናማኒ ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ይገጥመኛል በሚል ፍራቻ መሞላቱን ነገረኝ።
በደቡብ ምሥራቅ ኦወሪ ከተማ የሚገኝና የግል ንብረት የሆነው የአላዲማ ሆስፒታል ከፖሊስ ወንጀለኞች ተብለው የሚመጡ አስከሬኖችን መቀበሉን ማቆሙን አሳውቋል።
ሆስፒታሉም ለዚህ እንደ ምክንያትነት የጠቀሰው ፖሊስ የሟቾቹን ማንነት ለማሳወቅም ሆነ ለዘመዶቻቸው መንገር ባለመፈለጉ ነው።
ይህም ሁኔታ ባለቤት የሌላቸው አስከሬኖችን ለመቅበር ወጪው መንግሥት ላይ በመውደቁ በጅምላ ይቀብራቸው ነበር።
የቀብር ቦታዎች አስተዳዳሪ ኡጎና አማማሲ "አንዳንድ ጊዜ ፖሊሶች አስከሬኖችን ለመቀበል ያስገድዱናል፤ ነገር ግን እኛ ወደ መንግሥት ሆስፒታል እንዲወስዱ አጥብቀን እንጠይቃለን" ብለዋል።
አክለውም "የግል ቀብር ስፍራዎች ለሕክምና ትምህርት ቤቶች አስከሬን እንዲሰጡ ባይፈቀድላቸውም የመንግሥት ቀብር ስፍራዎች ግን ይሰጣሉ" ብለዋል።
ቤተሰቦች ስለተገደሉ ዘመዶቻቸው የማያዉቁበት ሁኔታ
ከፍተኛ የሕግ ባለሙያው ፍሬድ ኦኑቢያ በሕጋዊ መንገድ የተገደሉ ወንጀለኞችን አስከሬን የመሰብሰብ መብት ቤተሰቦች እንዳላቸው ተናግረዋል።
ጠበቃው "ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ማንም ካልተገኘ አስከሬኖቹ ወደ ማስተማሪያ ሆስፒታሎች ይላካሉ" ብለዋል።
ነገር ግን በፀጥታ ኃይሎች በዘፈቀደ ወይም ከሕግ ውጪ በሆነ ሁኔታ የሚገደሉ ግለሰቦችን ማግኘት ባለመቻላቸው ለቤተሰቦች እጅግ አስከፊ ነው ይላሉ።
የእንያ ጓደኛ ዲቫይን ቤተሰብ የልጃቸውን አስከሬኑን ማግኘታቸውና በሥርዓት መቅበር መቻላቸው የአጋጣሚ ጉዳይ ነበር።
የናይጄሪያ አናቶሚ ማኅበር በአሁኑ ወቅት አስከሬኖች ለህክምና ትምህርት በሚሰጡበት ወቅት የቤተሰብ ፈቃድን እንዲያገኙ እንዲሁም ሙሉ ታሪካቸውም እንዲታወቅ እንዲቻል ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖር እየተሟገተ ነው።
በተጨማሪም ግለሰቦች አካላቸውን ለሕክምና ሳይንስ እንዲለግሱ የሚያበረታቱባቸውን መንገዶች ያስቀምጣል።
እንያን በተመለከተ የጓደኛውን አስከሬኑ መመልከቱን ተከትሎ ለሳምንታት ያህል ትምህርቱን አቋርጦ ነበር። የአናቶሚ ትምህርት ክፍል በሚደርስበት ወቅት የጓደኛው መንፈስ ድቅን እያለም ያስቸግረው ነበር።
ወደ ዩኒቨርሰቲውም የተመለሰው ከአንድ ዓመት በኋላ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በዴልታ ግዛት በሚገኝ ሆስፒታል ላብራቶሪ ውስጥ ይሠራል።
የዲቫይን ቤተሰቦች በልጃቸው ግድያ ላይ የተሳተፉ የተወሰኑ መኮንኖች ከሥራቸው እንዲሰናበቱ አስደርገዋል።
ነገር ግን አሁንም ቢሆን በርካቶች የፖሊስ ጥቃት ሰለባዎች የሆኑና ምናልባትም በመላው አገሪቱ ባሉ የሕክምና ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተሰጡ አስከሬኖች ቤተሰቦች ፍትህን ይሻሉ።