ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮቪድ-19፡ በኢትዮጵያ የኮቪድ ክትባት ለማግኘት በነበረው የዕድሜ ገደብ ላይ ለውጥ ተደረገ
በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባት የሚሰጣቸው ዜጎች የዕድሜ ገደብ ዝቅ ከመደረጉ በተጨማሪ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲካተቱ መደረጉ ተገለጸ።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ስላለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝና የክትባት አቅርቦትን በተመለከተ እንደተናገሩት በሽታው እየተስፋፋ መሆኑንና ለዚህም የክትባቱ ተደራሽነት ላይ ለውጥ መደረጉን አመልክተዋል።
በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ የኮሮናቫይረስ ክትባት በኢትዮጵያ መሰጠት ሲጀምር የጤና ሚኒስቴር ክትባቱ በቀዳሚነት ለጤና ባለሙያዎች፣ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ለሆኑ እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ50 እስከ 60 ሆኖ ተጓዳኝ ህመም ላለባቸው እንዲሰጥ መመሪያ አውጥቶ ነበር።
በአገሪቱ የወረርሽኙ መከላከያ ክትባት መሰጠት ከጀመረ ከስድስት ወራት በኋላ ግን ክትባቱን በቅድሚያ ማግኘት ያላባቸው ሰዎች የዕድሜና የጤና ሁኔታ ላይ ለውጥ መደረጉ ተገልጿል።
በዚህም መሠረት ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በተለየ በሽታው በከፍተኛ ሁኔታ በተስፋፋባት በመዲናዋ በአዲስ አበባ ውስጥ ያሉ እድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ ለሆኑ ነዋሪዎች እንዲሁም በሌሎች የአገሪቱ ክልሎችና የከተማ አስተዳደር እድሜያቸዉ ከ55 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎች እንደሚሰጥ የጤና ሚኒስተሯ ተናግረዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ የኮቪድ-19 ወረሽኝ ምጣኔ በአንጻራዊ ሁኔታ ቀደም ሲል ከነበረበት የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቶ እንደነበር ሚኒስትሯ አስታውሰው፤ ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ግን የበሽታው መስፋፋትና የጉዳት መጠን መጨመሩን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ካለፉት ሦስት ሳምንታት ወዲህ ጀምሮ የሚወጣው ሳምንታዊ የወረርሽኙ ሪፖርት በበሽታው የመያዝ መጠን በአራት እጥፍ፣ በጽኑ የሚታመሙ ሰዎች በ2.5 እጥፍ እንዲሁም በበሽታው ሕይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ደግሞ በ2.8 እጥፍ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቅሰው አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎች እየቀነሱ በመምጣታቸው በበርካታ የአፍሪካ አገራት እየተከሰተ ያለው ሦስተኛ ዙር የወረርሽኙ የስርጭት ማዕበል በኢትዮጵያ ላይ እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንዲደረግ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመከላከል የተለያዩ የክትባት አይነቶች እንዳሉና በሽታውን ለመከላከልና በበሽታው ሊደርስ የሚችለውን የከፋ ህመምና ሞት ለመቀነስ እንደሚረዱ ገልጸው የክትባቱ ተደራሽነት መመሪያ ላይ ለውጥ መደረጉን አሳውቀዋል።
በመሆኑም በአገሪቱ ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የበሽታው ተጠቂዎች የተመዘገቡባት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የኮቪድ-19 ክትባት ላልወሰዱና ዕድሜያቸዉ ከ35 ዓመት በላይ ለሆኑ ይሰጣል ብለዋል።
በሌሎች ክልሎችና ከተማ አስተዳደር ውስጥ ደግሞ ዕድሜያቸዉ ከ55 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች የኮቪድ ክትባት ይሰጣል ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባም ሆነ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑና ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች በሙሉ የወረርሽኙን ክትባት ማግኘት እንደሚችሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በተመሳሳይም በሥራቸው ባህርይ ከብዙ ሰዎች ጋር ቀጥተኛ የሥራ ግንኙነት ያላቸው ሠራተኞችና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችና የጎዳና ተዳዳሪዎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ የመንግሥት ጤና ተቋማት ውስጥ ክትባቱን ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ክትባት ሲሰጥ በቆየባቸው ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከ2.3 ሚሊየን በላይ ሰዎች ክትባቱን ማግኘታቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ወረርሽኙ በአገሪቱ መኖሩ በተረጋገጠበት ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ከ287 ሺህ በላይ ሰዎች ላይ በሽታው የተገኘ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 265 ሺህ የሚደርሱት ከበሽታው ሲያገግሙ 4,452 ሰዎች ደግሞ በወረርሽኙ ሰበብ ለሞት ተዳርገዋል።