ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኮሮናቫይረስ ፡ ነፍሰጡር እናቶች የኮቪድ-19 ክትባት መውሰድ ይችላሉ?
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የኮሮናቫይረስ ክትባት በተለያዩ አገሮች እየተሰጠ ነው። ነፍሰጡሮች ክትባቱን መውሰድ ይችላሉ? የሚለው ጥያቄም እየተነሳ ነው።
የፋይዘርና ባዮንቴክ ክትባቶች ሙከራ ነፍሰጡርና የሚያጠቡ እናቶችን አላካተተም።
ክትባቱ በእነሱ ላይ ስለሚኖረው ተጽዕኖ በቂ መረጃ ስለሌለ፤ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ነፍሰጡሮችና የሚያጠቡ እናቶች ክትባቱን እንዳይወስዱ ተመክሯል።
በሌላ በኩል አሜሪካ፤ ነፍሰጡሮችና የሚያጠቡ እናቶች ክትባቱን መውሰድ ወይም አለመውሰድን በተመለከተ የግል ምርጫቸው ነው ብላለች።
እስካሁን የተገኙት መረጃዎች ምን ያሳያሉ?
በነፍሰጡር ሴቶች ጤና ዙርያ በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የሚሰሩት ዶ/ር ሩት ፋደን፤ "እስካሁን ይህ ነው የሚባል መረጃ አልተገኘም" ሲሉ ይናገራሉ።
ክትባቱ ለነፍሰጡር ወይም ለሚያጠቡ ሴቶች አስጊ መሆኑን የሚጠቁም በቂ መረጃ የለም።
የመድኃኒት አምራቹ ፋይዘር የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ተቋም ባወጣው መመሪያ መሠረት ነፍሰጡርና የሚያጠቡ እናቶችን በሙከራው እንዳላካተተ ተናግሯል።
ዳርት ወይም ዴቨሎፕመንታል ኤንድ ሪፕሮዳክቲቭ ቶክሲሲቲ የተባለው በእድገትና በሥነ ተዋልዶ ሂደት ላይ ሊኖር የሚችል ውጤትን የሚያሳይ ምርምር በእንስሳት ላይ ተካሂዶ እስኪጠናቀቅ ነፍሰጡርና የሚያጠቡ ሴቶች በሙከራው እንደማይካተቱ ፋይዘር አስረድቷል።
ዶ/ር ሩት እንደሚሉት፤ ከወረርሽኝ ውጪ ያሉ በሽታዎች ሲከሰቱና ክትባት ሲሰራላቸው በመጀመሪያው የምርምር ደረጃ ነፍሰጡር ሴቶች አይካተቱም።
ከእናት በተጨማሪ ልጅም ከግምት ስለሚገባ፤ በዘርፉ ነፍሰጡር ሴቶች በተለየ ሁኔታ ትኩረት ይሰጣቸዋል።
ወረርሽኞች ሲከሰቱ ግን ነፍሰጡሮችን በምርምር አለማካተት ፈታኝ ይሆናል።
"በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነን። በምርምሩ ነፍሰጡር ሴቶችን ማካተት ጥቅምም ጉዳትም አለው" የሚሉት ዶ/ር ኤምሊ ስቲኔት ናቸው።
በሌላ በኩል ነፍሰጡርና የሚያጠቡ እናቶችን በክሊኒካል ውሳኔዎች ለማሳተፍ እስካሁን በቂ መረጃ አልተኘም።
በየአገሩ ያሉ የተለያዩ መርሆች
አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደምን እንደ ምሳሌ እንውሰድ።
ሁለቱም አገሮች በጉዳዩ ላይ በቂ መረጃ የላቸውም። ሆኖም ግን የተለያየ የፖሊሲ አቅጣጫ ይከተላሉ።
ዩናይትድ ኪንግደም ያለውን የመረጃ ክፍተት ከግምት በማስገባት፤ ተጨማሪ መረጃ እስከሚገኝ ነፍሰጡርና የሚያጠቡ እናቶች ክትባቱን እንዳይወስዱ ብላለች።
የሮያል ኮሌጁ ዶ/ር ኤድዋርድ ሞሪስ እንደሚሉት፤ ነፍሰጡርና የሚያጠቡ ሴቶች በክትባት ምርምር ወቅት ስላልተካተቱ ክትባቱን መስጠት አስተማማኝ አይሆንም።
የአሜሪካ ባለሙያዎች ግን ከዚህ የተለየ አቅጣጫ ተከትለዋል። ክትባት የመውሰድ ውሳኔውን ለነፍሰጡርና የሚያጠቡ እናቶች ትተዋል።
ዶ/ር ሩት እንደሚሉት፤ እነዚህ ባለሙያዎች ክትባቱ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ውስን እንደሚሆን ተስማምተዋል።
አስፈላጊውን የምርመራ ሂደት ያለፉት ክትባቶቹ ደኅንነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነው በዩናይትድ ኪንግድም እና በአሜሪካ ፍቃድ የተሰጣቸው።
በሁለቱም አገሮች ነፍሰጡርና የሚያጠቡ እናቶች ክትባቱን የሚመለከት ምክር ከማግኘታቸው በፊት ተጨማሪ መረጃ ሊኖር ይገባል።
ፋይዘር በዚህ ዙርያ የሚያደርገው ምርምር በዚህ ዓመት መጨረሻ ይገባደዳል ተብሎ ይጠበቃል።
ወረርሽኙ ከተከሰተ ወዲህ ያረገዙ ሴቶች በቅርብ ክትትል ይደረግላቸዋል። ክትባቱን ከወሰዱ ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች አስፈላጊው መረጃም ይሰበሰባል።
አሜሪካ ውስጥ ክትባቱን ለመውሰድ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ከተባሉ የጤና ባለሙያዎች 330 ሺህ ያህሉ ነፍሰጡር ወይም የሚያጠቡ እናቶች ናቸው።
አሜሪካ፣ ኦሀዮ ውስጥ የምትኖረው የ35 ዓመቷ ነፍሰጡር ከመውለዷ በፊት ክትባት የመውሰድ እቅድ የላትም።
ክትባቱ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ስለማታውቅና የመጀመሪያ እርግዝናዋ ስለሆነ ክትባቱን ነፍሰጡር ሳለች ለመውሰድ እንዳላሰበች ተናግራለች።
የ34 ዓመቷ የእንግሊዝ ነዋሪ ኤሚ ኮልድነር በበኩሏ የሁለት ዓመት ልጇን እያጠባች ቢሆንም ክትባቱን ለመውሰድ ወስናለች።
ገና ነፍሰጡር ብትሆን ኖሮ ተጨማሪ መረጃ እስክታገኝ ክትባት እንደማትወስድ አያይዛ ተናግራለች።
ነፍሰጡሮች ልጃቸውን ለአደጋ ላለማጋለጥ ሲሉ በክትባት ሙከራው ላይሳተፉ እንደሚችሉ ኤሚ ትገምታለች።
ዶ/ር ሩት እንደሚናገሩት ከሆነ ግን ነፍሰጡርና የሚያጠቡ ሴቶች በሙከራ ሂደቱ ሲሳተፉ የክትባቱን አስተማማኝነት ማረጋገጥ ይቻላል።