ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮቪድ-19፡ 'የበሽታ መከላከል አቅም ይጨምራል' የተባለ ሐሰተኛ መድሃኒት በለንደን ሱቆች ሲሸጥ ተገኘ
የኮቪድ-19 በሽታን የመከላካል አቅም ይጨምራል የተባለ ሐሰተኛ መድሃኒት በለንደን ሱቆች ሲሸጥ እንደነበር የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ አመለከተ።
'ኮሮኒል' የተባለው ከዕፅዋት የተቀመመው መድሃኒት ከሕንድ የመጣ ሲሆን፤ ሲሸጥ የተገኘውም በዋና መዲናዋ በርካታ እስያዊያን በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ሱቆች ነው።
መድሃኒቱን ያመረተው ፓታንጃሊ አዩርቭድ፤ ክኒኑ ከመተንፈሻ አካላት ህመም እንደሚከላከል ይናገራል።
ይሁን እንጂ ለቢቢሲ የተደረገው ምርመራ የሚያሳየው ክኒኖቹ ከኮሮናቫይረስ እንደማይጠብቁ ነው።
በበርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ የተሰራው የላብራቶሪ ምርመራ፤ ከዕፅዋት የተቀመመው ይህ መድሃኒት ከኮሮናቫይረስ እንደማይጠብቅ አሳይቷል።
ቫይረስ አጥኝ [ቪሮሎጂስት] ዶክተር ሜትሪይ ሺቭኩማር፤ "የበሽታ መከላከል አቅምን ማሳደግ የሚለው ሃሳብ በራሱ ኮሮናቫይረስን ማከም ከሚለው አንፃር ትርጉም የሚሰጥ አይደለም" ብለዋል።
" የሰውነታችን የበሽታ መከላከል ሥርዓት ለቫይረሱ እንዴት ምላሽ እንደሚሰጥ በርካታ ልዩነቶች አሉ። የበሽታ መከላከል አቅምን ማሳደግም በሽታውን እንዴት ለመከላከል ሊረዳ እንደሚችል አናውቅም" ብለዋል።
ኮሮኒል የተባለው ይህ ክኒንም ለበሽታ መከላከል ሥርዓት የሚያደርገው አስተዋፅኦም ግለፅ አለመሆኑን ተናግረዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የማስታወቂያ ሕጎች፤ በማንኛውም ምግብም ሆነ የመጠጥ ምርቶች ላይ፤ ኮቪድ -19 እና የበሽታ መከላከል ሥርዓትን ማጣቀስ ይከለክላሉ።
የዚህ ክኒን አምራች ብዙ ተከታዮች ባሉበት ሕንድም ይህን ማድረግ የተከለከለ ነው።
ይሁን እንጂ በዌምብሌይ የሚገኝ አንድ ሱቅ ኮሮኒል የኮቪድ-19 በሽታን የመከላከል አቅም ያጎለብታል ሲል በመደብሮቹ እና በድረ ገጹ ያስተዋውቃል።
ቢቢሲ ኮቪድ -19ን እንደሚያክሙ በመግለፅ ክኒኑን የሚሸጡ ቢያንስ አራት ሌሎች መደብሮችንም አግኝቷል።
አንድ ደንበኛም "መድሃኒቱን ወስጃለሁ ፤ ምክንያቱን 78 ዓመቴ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ለግብይት ከወጣሁ ከማንኛውም ሰው ኮሮናቫይረስ ሊይዘኝ ይችላል። ለዚያ ነው የወሰድኩት ፤ ራሴን ለመጠበቅ" ሲሉ አክለዋል- እኝህ የዕድሜ ባለፀጋ።
እንደ ማስታወቂያ ደረጃዎች ባለሥልጣን (ASA) ከሆነ በዩናይትድ ኪንግደም የበሽታ መከላከል ሥርዓት 'ሊያሳድግ ይችላል' በሚል የተፈቀደለት ምንም ዓይነት መድሃኒትም ሆነ ንጥረ ነገር የለም።
ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ፣ ምልክቶቹን ለማስወገድ ወይም ለማከም ያስችላሉ የተባሉ መድሃኒቶች በመድሃኒቶችና በጤና እንክብካቤ ምርቶች ቁጥጥር ኤጀንሲ ፈቃድ ካላገኙም ሊመረቱ አይችሉም።
ኤጀንሲው ኮሮኒል የተባለው ይህ ክኒን ለማንኛውም አገልግሎት እንዲውልም ፈቃድ አልሰጠም። በመሆኑም "በዩኬ ገበያ ማንኛውም ፈቃድ ያልተሰጠው የመድሃኒት ምርት ለሽያጭ ከቀረበ እርምጃ ይወሰዳል" ሲል አስጠንቅቋል።
የኮሮኒል ክኒን አምራች ድርጅት መስራች የሆኑት ባባ ራምዴቭ፤ ሰኔ ወር ላይ ክኒኑ የኮቪድ -19 ሕሙማንን እንደፈወሰ ተናግረው ነበር።
የሕንድ መንግሥትም በበኩሉ ድርጅቱ ኮሮኒልን እንደ መድሃኒት ሳይሆን የበሽታ መከላከል አቅምን ማጎልበቻ ለገበያ ሊቀርብ ይችላል ብሏል።
የዩኬ ገለልተኛ መረጃ አጣሪ ድርጅት 'ፉል ፋክት' ግን እንደዚህ ዓይነት የተሳሳቱ መረጃዎች በሰዎች ጤና ላይና በኢኮኖሚ ላይ ቀውስ ያስከትላሉ ሲል አሳስቧል።