ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከኮሮናቫይረስ የትኞቹ ድርጅቶች አተረፉ? እነማንስ ከሰሩ?
ኮሮናቫይረስ በርካታ የንግድ ዘርፎችን አሽመድምዷል። በተቃራኒው ቀን የወጣላቸው የቴክኖሎጂ ዘርፎችም አሉ። ለመሆኑ የበሽታውን ሥርጭት ተከትሎ የትኞቹ ድርጅቶች አተረፉ? እነማንስ ከሰሩ?
ትርፋማ ድርጅቶች
1. ዙም
ኮቪድ-19 ብዙዎች ከቤታቸው እንዲሠሩ ምክንያት ሆኗል። እርስ በእርስ በቪድዮ የሚያገናኘው ዙም ታድያ ገበያ ደርቶለታል። በአንድ ቀን ተጠቃሚዎቹ ከ10 ሚሊዮን ወደ 200 ሚሊዮን ከፍ ብለዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ የማይክሮሶፍት ተጠቃሚዎችም ጨምረዋል። ካለፈው ወር ወዲህ 44 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ያገኘ ሲሆን፤ ይህም ቀድሞ ከነበረው 40 በመቶ እድገት አሳይቷል።
‘ቲምቪወር’ የተባለው መተጋበሪያም እንደ ዙም እና ማይክሮሶፍት ትርፋማ ሆኗል።
2. ‘ጌም’
እንቅስቃሴ መገደቡን ተከትሎ የድረ ገፅ ጨዋታ (ኦንላየን ጌሚንግ) የብዙዎች ጊዜ ማሳለፊያ ከሆነ ሰነባብቷል።
ለምሳሌ ከድሮውም ተወዳጅ የነበረውን ‘ኮል ኦፍ ዲውቲ’ ወደ አስር ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ይጫወቱታል።
ተንታኞች እንደሚሉት የ ‘ጌም’ ዓመታዊ ሽያጭ 35 በመቶ አድጓል።
ሆኖም ግን አዳዲስ ጨዋታዎች እየተመረቱ አይደለም። ተቋማቱ ሥራ ማቆማቸው በቀጣዩ ዓመት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራልም ተብሏል።
3. ኔትፍሊክስ
ሲኒማ ቤቶች ዝግ ስለሆኑ፤ ብዙ ፊልሞች በድረ ገፅ እየታዩ ነው። ስለዚህም ፊልም የሚያሰራጩ ድረ ገፆች ካለፉት ዓመታት በላቀ በርካታ ተከታዮች ያፈሩት በዘመነ ኮሮናቫይረስ ነው።
ለምሳሌ ኔትፍሊክስ 16 ሚሊዮን አዳዲስ ተከታዮች አግኝቷል። ኔትፍሊክስን በዋነኛነት የሚፎካከረው 'ዲዝኒ ፕላስም' ትርፉ ጨምሯል።
ሌላው አትራፊ 'ስፖቲፋይ' ተከታዮቹ 130 ሚሊዮን ደርሰዋል።
4. ክላስፓስ
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማከናወኛ (ጂም) መዘጋቱ፤ ሰዎች ፊታቸውን ወደ ድረ ገፅ እንዲያዞሩም አስገድዷል። እንደ 'ክላስፓስ' ያሉ በድረ ገፅ ስፖርት የሚያሠሩ በከፍተኛ ደረጃ ተፈላጊ ሆነዋል።
'ፔሎቶን' የተባለው ገፅ የተለያዩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ከሚያሳዩ አንዱ ነው። ምንም እንኳን ስቱድዮው በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ቢዘጋም፤ ትርፉ ከ60 በመቶ ዘሏል።
በድረ ገፅ በሚተላለፉ ስፓርቶች ተጠቃሚ የሆኑት ትልልቅ ተቋሞች ብቻ አይደሉም። ዩ ቲዩብ ላይ ቤት ውስጥ የሚሠሩ ስፖርቶች የሚያስተምሩ ግለሰቦችም ስኬታማ እየሆኑ ነው።
ከነዚህ አንዱ ጆ ዊክስ ሲሆን፤ በዩ ቲውብ የቀጥታ ሥርጭት ተከታዮች ብዛት የዓለምን ክብረ ወሰን ሰብሯል።
5. አማዞን
የድረ ገፅ መገበያያው አማዞን ከፍተኛ ገቢ እያካበተ ነው። ሆኖም ግን ተቀጣሪዎቹን ከኮቪድ-19 ለመከላከል ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ ባለመሆኑ ይተቻል።
ከሠራተኞች ደህንነት ጋር በተያያዘ የቀረቡ ቅሬታዎች እስኪጣሩ ፈረንሳይ መሠረታዊ ያልሆኑ የአማዞን ግዢዎችን አግዳለች።
የአማዞን መስራች ጄፍ ቤዞስ ገቢውን በ24 ቢሊዮን አሳድጓል።
የከሰሩ ተቋሞች
1. የመጓጓዣ ዘርፍ
የበረራ ዘርፍ እንዲሁም የመኪና ሽያጭም በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሏል። ዩናይትድ ኪንግደምን እንደ ምሳሌ ብንወስድ የመኪና ሽያጭ ከ1946 ወዲህ ሲቀንስ የመጀመሪያው ነው።
በሌላ በኩል 'ኡበር' የተሰኘው የታክሲ አገልግሎት ሰጭ ድርጅት በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞቹን አሰናብቷል።
2. የቴክኖሎጂ ውጤቶች አሻሻጮች
ባያመርቱም ሻጭና ገዢን የሚያገናኙ አካላት በዚህ ወቅት ሥራ ፈተዋል። በተለይም በቴክኖሎጂ ውጤቶች ለሸማቾች አገልግሎት ያቀርቡ የነበሩ ተቋሞች በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ንግዳቸው ተቀዛቅዟል።
ትርፍ የመኝታ ክፍል ያላቸው ሰዎች በድረ ገፅ ለኪራይ የሚያቀርቡበት 'ኤርቢኤንቢ' ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ይጠቀሳል። 1,900 ሠራተኞቹንም አሰናብቷል።
አሁን ላይ ምግብ ቤቶች እንዲሁም መሥሪያ ቤቶችም እንደ ቀድሞው እየሠሩ አይደለም።
ስለ ምግብ ቤቶችና ሌሎችም አገልግሎት ሰጪዎች አስተያየት እየሰበሰቡ ለተጠቃሚዎች ከሚያቀርቡ ድረ ገፆች አንዱ የሆነው 'የልፕ' አንድ ሦስተኛ የሚሆኑ ሠራተኞቹን አጥቷል።
'ዊወርክ' የሚባለው ቢሮ ተከራይና አከራይ አገናኝም ኪሳራ ውስጥ ገብቷል።