ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ "የቱሪዝም እንቅስቃሴው ልክ መብራትን የማጥፋት ያህል በቅጽበት ቆሟል"
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርስኝ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጽዕኖው በከፍተኛ ሁኔታ እየታየ ይገኛል።
ተጽዕኖው ክንዱን ካበረታባቸው ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ዘርፉ አንዱ ነው። በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ባለበት አማራ ክልል ተመራጭ መዳረሻ በሆኑት በላል ይበላ እና በጎንደር እያሳደረ የሚገኘውን ተጽዕኖ ለመመልከት ሞክረናል።
በላል ይበላ ከተማ በቱሪስት አስጎብኚነት የሚያገለግሉት ዲያቆን ፈንታ ታደሰ ለቢቢሲ እንደገለጹት ምንም ቱሪስት በአካባቢው የለም።
"ቤተክርስቲያኖች ተዘግተዋል። ከቤተክርስቲያን ካለው መንፈሳዊ አገልግሎት ውጪ የጉብኝት ሥራ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል" ብለዋል።
"የቅዱስ ላልበላ አብያተክርስቲያናት ከቤተክርስቲያን አገልግሎት ባሻገር በጣም ብዙ ቁጥር ላላቸው ወጣቶችም ሆነ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የገቢ ምንጭ ናቸው። አሁን ግን ጎብኚ ስለሌለ ሥራ ቆሟል" ሲሉ ያስረዳሉ።
በላል ይበላ ከተማ ምንም የቱሪስት እንቅስቀሴ እንደሌለ የገለጹት ዲያቆን ፈንታ "የስጦታ ዕቃዎችን የሚሸጡ ብዙ ሰዎች አሉ። ለቱሪስት የሚቀርቡ ብዙ ነገሮችንም ገዝተው ቢይዙም እነዚህን ለቱሪስቱ እንጂ ሕዝቡ የሚገዛቸው አይደሉም። የነበረው እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል፥ አቁሟል። ምንም የለም" ብለዋል።
ላል ይበላ ከከተማ እና አካባቢው ነዋሪዎች ህይወት የተመረኮዘው በእርሻ ሲሆን በተጨማሪም የቅዱስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናትን ለመጎብኘት በሚመጡ ቱሪስቶች ላይ መሆኑን በላሊበላ ከተማ አስተዳደር የባህል ቱሪዝም ጽህፈት በቤት ኃላፊ የሆኑት መሪ ጌታ መልካሙ አለሙ ገልጸዋል።
የግብርና ምርቶችን ለሆቴሎች የሚያቀርቡ፣ በቅሎ አከራዮች፣ የታክሲ ማኅበራ፣ የስጦታ ዕቃ አምራቾች እና ሻጮች፣ የአካባቢ አስጎብኚዎች፣ሆቴሎች፣ ሪዞርት እና ሎጆች በሙሉ ከሺህዎች ከሚቆጠሩ ሠራተኞቻቸው ጋር ሥራ ማቆማቸውን ገልጸዋል።
ኃላፊው ወረርሽኙ "ላል ይበላ ላይ ያስከተለውረ ጉዳት በመሞት እና በመኖር መካከል ያህል ነው ማለት ይቻላል። ይሄ ምንም የተጋነነ አይደለም" ብለዋል።
እንደ ኃላፊው ከሆነ ችግሩን ለመቀነስ ከመንግሥት ጋር እየተነጋገሩ ነው። በተለይም ከባንኮች ብድር ወስደው መኪና የገዙ እና ሆቴሎችን ለገዙ ሰዎች የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲራዘም ግፊት እያደረጉ መሆኑን እና "መንግሥትም ያሰበበት ይመስለናል። እንደላል ይበላ ጥቅል መረጃ ስጡን ብለው ሰጥተናል። ምላሹን እየጠበቅን ነው" ብለዋል።
ጎንደር
ሌላኛዋ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የቱሪዝም እንቅስቃሴው የተቋረጠባት ታሪካዊቷ ጎንደር ናት።
በከተማዋ የሚገኘው የጎሃ ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አማራ አጥናፉ ከኮሮናቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ ለቱሪስቶች አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ሆቴላቸው ሥራውን ተቋርጦ መዘጋቱን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በተጨማሪም "ጉዳቱ በአሁኑ ወቅት የምንሰራው ሥራ መቋረጡ ብቻ ሳይሆን፤ ለወደፊት በደንበኞች ቀድመው ተይዘው የነበሩ ሥራዎችም በሙሉ ተሰርዘዋል" ሲሉ ያለውን ጫና አስረድተዋል።
ነገር ግን ሆቴሉ ያለ አገልግሎት እንዳይቀመጥ ኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ኃላፊነቱን ወደመወጣት ፊቱን ማዞሩን ሥራ አስኪያጁ አመልክተዋል።
"ቫይረሱ በከተማዋ ቢከሰት የህክምና መስጫ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል። የጎደላቸው ህክምና ለሚሰጡ ባለሙያዎች መኖሪያ በመሆኑ፤ እኛ ክፍሎቻችንን ሰጥተን ያለምንም ክፍያ እንዲገለገሉበት አድርገናል።"
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገቡትን የጎንደር አብያተ መንግስታት ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች እንቅስቃሴ መቆሙን የጎንደር ከተማ ዓለም አቀፍ ቅርስ አስተዳዳር ኃላፊ አቶ ጌታሁን ስዩም ገልጸዋል።
ይንንም "በአጭር ቃል ለመግለጽ የኮሮና ወረርሽን ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የጎንደር ቱሪዝም እንቅስቃሴ ልክ መብራትን የማጥፋት ያህል በቅጽበት የቆመ ጉዳይ ነው። ሙሉ ለሙሉ ነው የቆመው" ሲሉ ያስረዳሉ።
ኃላፊው አክለውም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የአገር ውስጥም ሆነ የውጭም ቱሪስቶች እንቅስቃሴ አንድ ላይ በመቆሙ ሥራውን ሙሉ ለሙሉ እንዲቆም አድርጎታል።
ነገር ግን ይህንን ሁኔታ በመጠቀም ቀደም ሲል በዕቅድ ተይዞ የነበረውን አብያተ መንግሥታቱ ላይ የቅርስ ጥገና እተከናወነ ነው። ጥገናው እና የእንክብካቤ ሥራው ቀደም ሲል ከጎብኚዎች በተገኘ ገንዘብት ቀደም እየተካሄደ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በአገር ደረጃ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ወደነበረው የአማራ ክልል ያለው እንቅስቃሴ መቆሙን የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ለቢበሲ ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ከ154 ሺህ በላይ የውጭ አገር ዜጎች ክልሉን የገበኙ ቢሆንም የኮሮናቫይረስ ክስተትን ተከትሎ በአሁኑ ጊዜ አጠቃላይ ቱሪስቶች እንቅስቃሴው መቆሙን አቶ እነድሪስ በማስረጃነት አንስተዋል።
"በዚህም ምክንያት ዘርፉ የተሰማሩ ብዙ አካላት ከሥራ ውጪ ሆነዋል" ያሉት ኃላፊው የደረሰውን ጉዳት የሚያሳይ ሙሉ መረጃ እየተጠናቀረ መሆኑን ጠቅሰው "ሰሜን ተራራን ብቻ በአጭሩ ብንወስድ በኢኮ-ቱሪዝም የተደራጁ እና ሥራ ላይ የነበሩ 8300 የሚሆኑ ሰዎች አሁን ከሥራ ውጪ ሆነዋል" ብለዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ በአገር አቀፍም ሆነ በክልልለ ደረጃ የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት እና ወደ ነበረበት ለመመለስ የስትራቴጂክ ፕላን ተዘጋጅቷል።
"በዘርፉ ብዙ ተዋናዮች አሉ። ዘርፉ ብዙ የሥራ ዕድል የሚፈጥር እና የሚይዝ በመሆኑ የመጀመሪያው የጉዳት መጠን ልየታ ነው። ምን ያህል ሰው ከሥራ ውጪ ነው በሚል የመለየት ሥራ እየተከናወነ ነው። የጉዳቱን መጠን በማየት ከፌደራሉ ፕላን ላይ በመነሳት የክልሉን ስትራቴጂ በማዘጋጀትእና ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር ተወያይተን ወደ ሥራ እንገባለን" ሲሉ አስረድተዋል።