ኮሮናቫይረስ፡ አቅመ ደካሞችን እያማለለ የሚገኘው የማፊያዎች ገንዘብ

የኮሮናቫይረስ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ በሚገኝበት በዚህ ሰዓት የጣልያን ማፍያዎች በሚሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለማትረፍ ደፋ ቀና እያሉ ነው።

የአገሪቱ ባለስልጣናት እንደገለጹት ዜጎች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ፊታቸውን ማፊያዎች ወደሚሰጡት የተለያየ አይነት ብድርና እርዳታ እያዞሩ ይገኛሉ።

በጣልያን የሚታወቀው የኮሳ ኖስትራ ማፊያ ቡድን ዋና አለቃ ወንድም በሲሲሊ ደሴት ፓሌርሞ መንደር ለሚገኙ ችግረኛ ነዋሪዎች ምግብ እያከፋፈለ ይገኛል።

‘’ ብዙ ሰዎች ስልክ እየደወሉ ችግራቸውን እየነገሩኝ ያለቅሳሉ። ልጆቻቸውን መመገብ እንኳን እንዳልቻሉ ይነግሩኛል’’ ብሏል።

‘’ አንዲት ወጣት ሴት በየቀኑ ነበር የምትደውልልኝ፤ አምስት ልጆች ያሏት ሲሆን ምን እንደምታበላቸው ጨንቋታል።‘’

የማፊያ ቡድኑ ወንድም አክሎም ‘’ሰዎችን መርዳት ማፊያ የሚያስብል ከሆነ፤ ኩሩ የማፊያ አባል ነኝ’’ ብሏል።

በርካታ በማፊያዎች የተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ምስክርነቱን የሰጠውና ከዚህ በፊት የማፊያ አባል የነበረው ጋስፔሬ ሙቶሎ ግን በዚህ በጎ በሚመስል ተግባር ሰዎች ሊሸወዱ አይገባም ይላል።

‘’ እኔም ልክ እንደዚህ ነበር የማደርገው። ሰዎች በጣም ይወዱኛል፤ ችግራቸውን አሰማለሁ። ማፊያዎች ሁሌም በሰዎች ችግር በኩል ነው የሚገቡት። የሆነ ነገር እስከሚፈጠር ድረስ ትክክለኛ ማንነታቸውንና ፍላጎታቸውን ማወቅ አይቻልም።‘’

‘’ እኔም ወንጀለኛ ነበርኩ። በዘመኔ ከ20 በላይ ሰዎችን ገድያለሁ።‘’

ጋስፔሬ ፖሊሶች ብቻ በሚያውቁትና ጥበቃ በሚያደርጉለት አድራሻው በማይታወቅ ቦታ ሆኖ ነው ይህንን መረጃ ለቢቢሲ ለመስጠት የቻለው።

‘’ ልጆች ሲራቡና የምትሰራበት የንግድ ቤት ኪሳራ ውስጥ ሲወድቅ ምንም አማራጭ ስለማይኖር እርዳታ ለማግኘት ሰዎች የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። ማፊያዎች የጠቀሙ መስለው የሚገቡት በዚህ መንገድ ነው’’ ይላል።

ጋስፔሬ እንደሚለው ምግብ በነጻ ማከፋፈል በራሱ ድብቅ አጀንዳ አለው።

‘’ ይህን የሚያደርጉት ታማኝነትን ለማትረፍ ነው። እነሱ ዋነኛ ግባቸው በአካባቢዎቹ በነጻነት መንቀሳቀስና የሚፈልጉትን ማንኛውንም ነገር ያለማንም ጠያቂ ማከናወን ነው። ማህበረሰቡ ተቀብሏቸው ዝም ካለ ደግሞ ለእነሱ የተመቸ ይሆናል’’ የሚለው የተደራጀ ወንጀል መከላከል ላይ የሚሰራው ኒኮላ ግራቴሪ ነው።

‘’በዚህ የኮሮናቫይረስ ወቅት ደግሞ እንዲህ አይነት ነገሮች መበራከታቸው ግልጽ ነው። በጣም ትንሽ የሚባለውን ስጦታ እንኳን መቀበል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሊከት ይችላል።‘’

ማርሴሎ በፓሌርሞ መሀል ውስጥ አነስተኛ ምግብ ቤት አለው። ከባለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ ደግሞ ምግብ ቤቱ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ተዘግቷል።

‘’ አሁን ምንም አማራጭ የለኝም፤ ሌላው ማፊያዎቹ መጥተው ምግብ ቤቱን እስከሚገዙኝ እየጠበቅኩኝ ነው። ከዚህ በኋላ ደግሞ መክፈት የምችል አይመስለኝም።‘’

ማርሴሎ እንደሚለው የሆነ ሰው ይመጣና ሬስቶራንቱን ለመግዛት ዋጋ ያቀርባል ከትንሽ ድርድር በኋላ የእነሱ ያደርጉታል።

ከዚህ በተጨማሪ እንደዚህ አይነት አስቸጋሪ ጊዜያት ለማፈያዎች ዋነኛ ምቹ አጋጣሚዎች ናቸው። ምክንያቱም ሰዎች አማራጭ ስለማይኖራቸው ትንሽም ይሁን ትልቅ ብድር ውስጥ ይገባሉ።

ማፍያዎቹም ወጣም ወረደ ያንን ገንዘብ ከነወለዱ ከመቀበል ወደኋላ አይሉም።

ከዚህ ባለፈም ምርጫ በደረሰ ጊዜ እነዚሁ ማፍያዎች ወደረዷቸው ሰዎች በመሄድ የሰራንላችሁን ውለታ የምትከፍሉበት ሰአት ደርሷል። እኛ የምንላችሁን ተወዳዳሪ ምረጡ ይሏቸዋል።

ከማፊያ ብድር ወስደው ለተቸገሩ ሰዎች የተቋቋመው የጥሪ ማዕከል በጣልያን እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ከተጣለ በኋላ የሚቀርቡለት ቅሬታዎች 100% ጨምረዋል።

‘’ዜጎች ከመንግስታቸው አፋጣኝ እርዳታ ማግኘት የማይችሉ ከሆነ በማፊያዎች ወጥመድ ውስጥ መውደቃቸው አይቀሬ ነው’’ ትላለች የፀረ ማፍያ ቡድን ውስጥ የምትሰራው ኤንዛ ራንዶ።

ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ የጣልያን ኢኮኖሚ 9.1 በመቶ እንደሚቀንስ ይጠበቃል። በዚህም ምክንያት በርካታ ጣልያናውያን በተለይም አነስተኛ ንግድ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሰዎች ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል።

‘’ ይህ ደግሞ ለማፊያዎቹ በጣም ምቹ አጋጣሚ ነው’’ ትላለች ኤንዛ።

ምክሯም መንግስት ከማፊያዎቹ ቀድሞ ለዜጎቹ የብድር አቅርቦት ማመቻቸት እንዳለበት ነው።

የጣልያን መንግስት እንዳስታወቀው ደግሞ ዜጎች እስከ 25 ሺ ዩሮ የሚደርስ ብድር መየጠቅ ይችላሉ። ነገር ግን እንደ ማርሴሎ ያሉ ዜጎች ይህን ያክል ገንዘብ ከመንግስት መበደር አይፈልጉም።

ምክንያቱም ሱቆቻቸውን ቢከፍቱ እንኳን በአሁኑ ሰአት ምንም አይነት ደንበኛ ማግኘት ስለማይችሉ ብድራቸውን መክፈል አይችሉም። ስለዚህ ያላቸው አማራጭ የንግድ ሱቆቻቸውን ለማፊያዎች መሸጥ ነው።

ማፊያዎቹ ደግሞ እንደዚህ አይነት አነስተኛ ሱቆችን ገንዘብ በሕገወጥ መንገድ ለማዘዋወር በእጅጉ ይፈልጓቸዋል።