ኮሮናቫይረስ፡ በስልጤ ዞን ኮቪድ-19 ያለባቸው ሴት እንዴት ሊገኙ ቻሉ?

የጤና ጥበቃ ሚንስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በየዕለቱ በሚያወጡት የ24 ሰዓታት የኮሮናቫይረስ ሪፖርት እሁድ፣ ሚያዚያ 25 2012 ዓ.ም ለ1560 ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው ሁለት ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተገልጿል።

የመጀመሪያው ታማሚ የ49 ዓመት ኢትዮጵያዊ በአዲስ አበባ ህክምና በመከታተል ላይ ያሉ ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ የ45 ዓመት ኢትዮጵያዊት እና በደቡብ ክልል የስልጤ ዞን የስልጢ ወረዳ ነዋሪ ናቸው።

አብዱልዋሪስ ጀማል የስልጤ ዞን የጤና መምሪያ ኃላፊ ሲሆኑ በዞኑ ኮቪድ-19ን ለመከላከል የተደራጀው ቡድን የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን ነበር ብለዋል።

"የቤት ለቤት አሰሳ እና ጉብኝት እንሠራ ነበር። በተዘጋጀው ማኑዋል መሠረት የጤና ባለሙያዎች፣ በጎ ፈቃደኞች እና ሌሎችን በማስልጠን ባለፉት 2 ሳምንታት ከ93 ሺህ ቤተሰቦች ወይም ከ324 ሺህ በላይ ግለሰቦችን በቤታቸው በማስተማር ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተሰርቷል። ጎን ለጎንም ቫይረሱ ያለባቸውን የመለየት ሥራ ተከናውኗል።"

በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው የ45 ዓመት ሴት በስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። ግለሰቧ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው በተመሳሳይ ቤት ለቤት በተደረገ አሰሳ ነው።

አቶ ካሚል ጃቢር በስልጤ ዞን የስልጢ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሲሆኑ በወረዳው ኮሚቴ በማዋቀር፣ ግብዓት በማሟላት እና በጀት በማጽደቅ በርካታ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውቀዋል።

"500 ሺህ ብር ወጪ ተደርጎ የመከላከል ሥራ ተሠርቷል። . . . በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የወጡ ክልከላዎችን በማስተግበር እና ግንዛቤ በመፍጠር ዙሪያ ተሰርቷል" ይላሉ።

"አካሄድ ቀየረን" የሚሉት አቶ ካሚል "እስከ ሚያዝያ 24 ድረስ 7800 አባወራዎችን ተደራሽ አድርገናል። ይህም 32 ሺህ 590 አካባቢ ሰዎችን ደርሰናል ማለት ነው። ምልክቶች መለየትና ለወረዳ ሪፖርት ማድረግ በተጨማሪነት ይሠራል። ከዚያም ለዞን ሪፖርት ይደረጋል" ሲሉ ያስረዳሉ።

የ45 ዓመቷ በስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ ነዋሪ ሆኑት ግለሰብም በዚሁ መሠረት ነው ሊለዩ የቻሉት።

አንዲት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ በቀበሌ ውስጥ በምታስተምርበት ወቅት ሳል ያለባቸው 4 ሰዎችን በመለየት ለወረዳው መረጃ ትሰጣለች። "የወረዳው ፈጣን ምላሽ ሰጪ ኮሚቴ ሄዶ ካጣራ በኋላ በዞን ደረጃ ላለው ኮሚቴ ሐሙስ ሪፖርት አድርጓል። አርብ ለአራቱ ሰዎች እና በሌሎች ሆስፒታሎች ያሉ ተጠርጣሪዎችን ናሙና ሰብበስበን ወደ ሃዋሳ ልከናል። እሁድ ውጤቱን ሰምተናል" ሲሉ አቶ አብዱላዋሪስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚህ በኋላ ከግለሰቧ ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች የመለየት ሥራ ማከናወን ተሰርቷል።

"ከእሷ ጋር ንክኪ ያላቸውን ቤተሰቦች እና ቅርብ ንክኪ ያላቸውን ሌሎች 16 ሰዎች ወደ ማቆያ አስገብተናል። እሷ ወደ ወራቤ ሆስፒታል አምርታለች" ብለዋል አቶ ካሚል።

እንደ አቶ ካሚል ገለጻ ከሆነ ባለቤቷ ቀደም ሲል ናሙና ከተወሰደላቸው አራት ሰዎች አንዱ ሆኖ ነጻ መሆኑ ቢረጋገጠም ናሙናው ከተወሰደ በኋላ ከባለቤቱ ጋር በድጋሚ ንክኪ ስለነበረው ወደማቆያ እንዲገባ ተደርጓል።

የወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ሆስፒታል ትኩረቱን ቫይረሱን በመከላከል ላይ አድረጎ እየሰራ ይገኛል። ኮሮናቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መከሰቱ ከተገለጸ ጀምሮ ማህበራዊ ርቀትን፣ የግል ንጽህናን ስለመጠበቅ እና ሰለቫይረሱ የሚረዱ ሌሎች መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ሲያደርስ ቆይቷል።

ጎን ለጎን ደግሞ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቢመጡ በሚል ዞኑ ያለውን ሃብት በጠቀም ለይቶ ማቆያ እና ህክምና መስጫ ሲያዘጋጁ መቆየታቸውን የሆስፒታሉ ባልደረባ እና የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ፈድሉ ጀንፋ ገልጸውልናል።

"ግለሰቧ የ45 ዓመት እናት ናቸው። ከገጠር ወረዳ ቀበሌ የመጡ ናቸው። ከውጭ ጉዞም ሆነ ከሚጠረጠር ሰው ወይም ከሚታወቅ ሰው ጋር ግንኙነት ስላላቸው ሳይሆን የምትጠረጥሯቸውን እና ሳልና ትኩሳት ያለባቸውን ሰዎች ናሙና መላክ ትችላላችሁ በመባሉ ነው የተገኙት። እኚህ እናት ለሁለት ሳምንት ገደማ ሳል ስለነበራቸው ናሙናቸው ተላከ። አሁን 'ስቴብል' ናቸው። ለሳምንታት የነበራቸው ደረቅ ሳል አሁን ትንሽ ሲሆን እሱም እየጠፋ ነው። ህክምና እየተደረገላቸው ነው። ምንም ምልክት ወደሌለው እየተቀየሩ ነው" ሲሉ ስለጤንነታቸው ሁኔታ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሁኔታ መልሰዋል።

የጉዞ ታሪክ የሌላቸው እና ከተተረጠረም ሆነ ቫይረሱ እንዳለበት ከታወቀ ግለሰብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሳይኖራቸው በቫይረሱ መያዛቸው ስጋት አይፈጥርም ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ "ስጋት ይፈጥራል። በጣም ይፈጥራል። ቫይረሱ እንዴት እሳቸው ጋር እንደደረሰ ለማወቅ እየተሠራ ነው። እሳቸው ባያምኑበትም ከውጭ ከመጣ ሰው ጋር ንክኪ ነበራቸው የሚል መረጃ እየደረሰን ነው። በህብረተሰቡ ውስጥ የቫይረሱ ስርጭት እንደሌለ ስለሚታወቅ ስጋት ይፈጥራል" ብለዋል።

ሁሉም እስካሁን ያሉት [በቫይረሱ የተያዙት] ከውጭ የመጡ ወይም ንኪኪ ያላቸው እንጂ ወደ በህብረተሰብ ውስጥ ስርጭት ስለመኖሩ አልታወቀም የሚል እሳቤ ነው ያለው።

ሴትየዋ የቤት እመቤት ናቸው። ገበያ ይሄዳሉ። ሳሉ ከጀመራቸውም በኋላ ገበያ ሄደዋል። ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ተብሎ 35 ሰዎች ተለይተው ለ14 ቀን ወደ ለይቶ ማቆያ ገብተዋል።

"ስጋት አለ" ይላሉ ዶ/ር ፈድሉ። በህብረተብ ደረጃ ስርጭት ወደምንለው ደረጃ መሸጋገሩን የሚያሳይም ሊሆን ይችላል ብለዋል ለቢቢሲ ጉዳዩን ሲያስረዱ። "አሁን ባለው መረጃ ማለት ንክኪ የላትም ብለን መናገር የምንችልበት ደረጃ ላይ አልደረስንም " ብለዋል።

ናሙና ሲወሰድ የሚሞላ ፎርም አለው። የጉዞ ታሪክ፣ ከበሽታው ከተጠረጠረ ወይም ከታየበት ጋር ንክኪ ስለመኖሩ ጥያቄ ይቀርባል። "በዚህ በኩል በደንብ ለማጣራት ሞክረናል። በአካባቢው ወደሚገኙ ገበያዎች ይንቀሳቀሳሉ። ከውጭ ከመጡ፣ ከአዲስ አበበባ ከመጡ ሰዎች ጋር ንክኪ ካለ ለማጣራት በጣም ጥረት አድርገናል። እስካሁን ግን ያላገኘንበት ሁኔታ ነው ያለው። በአካካቢው የተጠናከረ ስራ እየሰራን ነው። ግንኙነት ያላቸውን ናሙና ወስደን ዛሬ ልከናል። ሁኔታው በጣም አስደንጋጭ ነው። ግለሰቧ የገጠር ነዋሪ ናቸው። አሁን የተጠናከረ ስራ እየሠራን ነው።" ያሉት ደግሞ አቶ አብዱላዋሪስ ናቸው።

በዞኑ የቫይረሱን ስርጨት ለመቆጣጠር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የወጡ ደንቦች ተግባራዊ እንዲሆን በመስራት ላይ መሆናቸው ኃላፊዎቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እንደወረዳቸው ስጋቶች መኖራቸውን ያጫወቱን አቶ ካሚል በተሽከርካሪዎች ትርፍ መጫን፣ በገበያ ቦታዎች ርቀትን አለመጠበቅ ይታያል ብለዋል። ባለፉት ቀናት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን መዘናጋት መፍጠሩን አስረድተዋል።

በቤተ እምነቶች አካባቢ ደንቦች እየተከበሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን ግን በወረዳው "ባለ ሶስት እግር ተስከርካሪዎች አንድ ሰው ብቻ እንዲጭኑ፣ ጋሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ፣ ሞተር ሳይክሎች እንዳይንቀሳቀሱ (የመንግስት ሞተር ሳይክሎች ሰው እንዳይጭኑ)፣ በከተሞች እና ሰዎች በሚበዛባቸው ከጉልት ያለፈ ትልቅ ገበያ ተከልክሏል" ብለዋል።

እንደ አቶ ካሚልም ከሆነ ከተማው ላይ ጫት መሸጥም ተከለከለ ሲሆን፣ የሚሸጡ ሲገኙም እየታሸገባቸው ነው። የጀበና ቡና ሽያጭ የተከለከለ ሲሆን "ሁኔታዎችን እያየን ተጨማሪ እርምጃዎችን እንወስዳለን" ብለዋል።

እንደ አቶ አብዱላዋሪስ ጀማል ከሆነ ስልጤ ዞን ለቫይረሱ "ተጋላጭ ዞን" ነው። "በርካታ የአካባቢው ሰዎች በሥራ ምክንያት ወደተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ተሰራጭተዋል። ከእነዚህ መካከል የተወሰኑት በኮሮና ምክንያት እየተመለሱ ነው" ሲሉ ምክንያታቸውን ያስቀምጣሉ።

"ቀደም ሲል 305 ሰዎችን በወራቤ ዩኒኒቨርሲቲ ማቆያ ለ14 ቀናት አቆይተናል። እነዚህ ከአዲስ አበባ እና አዳማ የመጡ ሲሆን ምንም ምልክት ስላላሳዩ ክትትል በማድረግ ወደ ቤተሰብ መልሰናቸዋል። ዞኑ ተጋላጭ በመሆኑ እና ከህብረተሰቡ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ እስካሁን ትንሽ ነው የተመመረረው" ብለዋል።

ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ማሽን ለማስገባት በሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጸውልናል።