ኮሮናቫይረስ ሰዎችን ከእምነታቸው እየለየ ይሆን?

ኮሮናቫይረስ የዓለም ራስ ምታት መሆኑን ተከትሎ የሰዎች እንቅስቃሴ በእጅ ተገቷል። ጉዞዎች እየተሰረዙ ነው፤ አብሮ መሳቅ መጫት ቀርቶ የሞተን ሰብሰብ ብሎ መቅበር ፈተና ሆኗል።

የእግዜር ሰላምታን ከእጅ ወደ እግር ለማውረድ የተገደዱ ብዙ አገሮች ናቸው። የእንግሊዝ ፓርላማም ሆነ የፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች ከተጨባበጡ ሰነባበቱ።

ኮሮና ቀስ በቀስ በሃይማኖትም እየገባ ነው።

የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር አብያተ ክርስትያናት፣ መስጂዶችና እና ሌሎች ቤተ እምነቶች የፀሎትና የሃይማኖት በዓላት አከባበር ላይ ለውጥ ለማድረግ ተደገደዋል።

አምልኮዎች የሚደረጉበት ሁኔታ እንዲህ እየተቀየረ ባለበት ሁኔታ እምነት እንዴት ይፀናል? የሚል ጥያቄ የሚያነሱ አሉ።

እስልምና

በታላቁ የመካ መስጂድ ለወትሮ የሚታደሙት በሺህዎች የሚቆጠሩ የነበሩ ቢሆንም የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ተከትሎ የምእመኑ ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል። በመስጂዱ ምእመናን በእጃቸው እንዳይነኳቸው የታጠሩ ቦታዎችም አሉ።

ከውጭ መካንም ሆነ መዲናን ለመጎብኘት የሚደረግ ጉዞ ላይ የተጣለው ገደብም እንዳለ ነው።

ከሃጅ ጉዞ በተለየ መልኩ በየዓመቱ የትኛውም ጊዜ ላይ መደረግ ለሚችለው ለኡምራ ጉዞ ቢያንስ በዓመት ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑ ወደ መካ ያቀኑ ነበር።

ናይጂሪያ ውስጥ ወደ መካ የሚደረጉ መንፈሳዊ ጉዞዎችን የሚያመቻቸው አንድ የጉዞ ወኪል ኃላፊ የሆኑት ሃዚዳ ታኒሙ ዳኑ "ሰዎች አዝነዋል፣ የኡምራህ ነበር ጊዜው እና ሁሉም የማምለክ ጉዞውን ይወደዋል" በማለት ነገሩ ተፅእኖ የሚያሳድረው የኡምራህ ጉዞ ላይ ብቻም ላይሆን እንደሚችል ይናገራሉ።

እገዳው እስከ ረመዳን፣ ከዚያም እስከ ሃጅ ጉዞ ቢራዘምስ በሚል ብዙዎች መጨነቃቸውን አልቀረም። የሳዑዲ ባለስልጣናት እገዳው ጊዜያዊ መሆኑን ከመጠቆም ውጭ እገዳው እስከ ሃጅ ድረስ ሊረዝም ስለ መቻል አለመቻሉ የሰጡት ፍንጭ የለም።

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ሊጨምር የሚችል ሃይማኖታዊ ሁነቶች አሁንም የሚስተዋሉበት ሁኔታ አለ።

ምንም እንኳ ቫይረሱ አገራቸውን እየናጠ ቢሆንም በቅርቡ ኢራናዊያን በተለይም የሺአ እምነት ተከታዮች 'ኮሮናቫይረስ የሚባል ነገር የለም' በሚመስል መልኩ መቅደስ ውስጥ ግድግዳዎችን በምላሳቸው ሲልሱ የሚታይበት ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ በሰፊው እየተጋራ ነበር።

እዚህ ተንቀሳቃሽ ምሥል ላይ አንድ ሰው ኮሮናቫይረስ እንደማያስፈራውና የአምልኮ ስፍራው ፈውስ እንዳለው እየተናገረ የመቅደስ በርና ግድግዳዎችን ሲልስ ይታያል። ይህና ሌሎችም ቪዲዮው ላይ የሚታዩ ነገሮች ብዙዎችን ሊረብሹ ይችላሉ።

በቪዲዮው ከሚታዩት ሁለቱ ግለሰቦች ሲታሰሩ ጥቂት የማይባሉ ኢራናዊያን የእምነት ተቋማት በእንዲህ ያለው ጊዜ ሙሉ ለሙሉ መዘጋት ነበረባቸው ብለዋል።

በሌላ በኩል በቫይረሱ የተያዘ አንድ ሰው ብቻ በተገኘባት ደቡብ አፍሪካ ሼኮች የአርብን ጁምአ ስለኮሮናቫይረስ እንዲጠነቀቁ ለማስተማር እንደተጠቀሙበት የቢቢሲ አፍሪካው ሞሃመድ አሊዬ ታዝቧል። በዚህም አማኞችን እንዳይጨባበጡ መክረዋል።

ምእመናን ምክሩን ቢቀበሉም በቀላሉ መተው የሚችሉት ልማድ ባለመሆኑ መጨባበጥ መቀጠላቸውንም ዘጋቢው ተመልክቷል።

ሂንዱዎች

ይህ ወቅት ለሂንዱ እምነት ተከታዮች የቀለም በዓላቸው ሆሊን የሚያከብሩበት ሲሆን በዓሉ ጥሩ መንፈስ መጥፎውን ማሸነፉ የሚዘከርበት ነው።

ብዙዎች አደባባይ ወጥተው ራሳቸውን እንዲሁም ሌሎችን የሚያቀልሙበት ነው። የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ህዝብ የሚታደምበትን ይህን በዓል እንደማይታደሙ ተናግረዋል።

ዜጎች እንዲህ ባለው ብዙ ሰዎች በሚገኙበት ስርዓት እንዳይገኙም አሳስበዋል። ምንም እንኳ እንደ አፍ መሸፈኛ ያሉን በማድረግ አንዳንዶች ጥንቃቄ ለማድረግ ቢሞክሩም ቅዳሜና እሁድ የነበረውን በዓል ብዙዎች ተሰባስበው አክብረዋል።

ይህ እጅግ አደገኛ ነው ብለው ራሳቸውን ከበዓሉ ያቀቡም ጥቂት አልነበሩም። በህንዷ አርሚስታር የሚኖረው ኒኪ ሲንግ በስልክ መልካም ምኞትን መለዋወጥን እንደመረጠ ይናገራል።

የአይሁድ እምነት

በምእራብ ለንደን የአይሁድ እምነት ራቢ የሆኑት ጃኪ ታቢክ ነገሩ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን ለማስረዳት ሲሞክሩ " ባለቤቷን በሞት የተነጠቀችን ሚስት ቀብር ላይ እንዴት አቅፈህ አታፅናናም? በጣም ከባድ ነገር ነው" ይላሉ።

ቢሆንም ግን ሰዎች መነካካትን ትተው እንዲህ ዓይነት ሃዘን ላይ ያሉ ሰዎችን በጥንቃቄ ቀረብ ብሎ በማናገር ማፅናናት እንደሚችሉ ይናገራሉ።

በእስራኤል ቀዳሚ የአይሁዶች ራቢ ዳቪድ ላው ሰዎች እንዳይነካኩና እንዳይሳሳሙ መልክታቸውን አስተላልፈዋል። ብዙዎቹ ራቢዎችም እንደ እርሳቸው እየመከሩ ነው።

ክርስትና

በመቶዎች የሚቆጠሩ በሚታደሙበት በዋሽንግተን ዲሲው ጆርጅታውን ክራይስት ቤተክርስትያን አገልጋይ የሆኑት ግለሰብ ኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው መታወቁን ተከትሎ በዚያ ቤተ እምነት የሚታደሙ ራሳቸውን አግልለው እንዲቆዩ ተነግሯቸዋል።

ቄስ ቲሞቲ ኮሌ ቫይረሱ የተገኘባቸው ቅዳሜ ዕለት ሲሆን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ተለይተው እንዲቆዩ ተደርጓል።

ቄስ ቲሞቲ በመሩት የአምልኮ ስነስርዓት ላይ 550 ምዕመናን ታድመው ነበር ተብሏል።

በጣሊያንም ቦሆን ፖፕ ፍራንሲስ እንደተለመደው በመስኮት ብቅ ብለው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይን እየተመለከቱ ቡራኬ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። ለዚህም ምክንያታቸው በቫቲካን ሊፈጠር የሚችለውን መጨናነቅ ለማስቀረት በማሰብ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን የዕለቱን ቡራኬም በኢንተርኔት የቀጥታ ስርጭት ሰጥተዋል።

ከጋና እስከ አሜሪካ እንዲሁም አውሮጳ የሚገኙ የካቶሊክ የእምነት አባቶች የቫይረሱን ወረርሽኝ ለማስቀረት በሚል በሕብረት የማምለክ ስርዓታቸውን ቀይረዋል።

የቅዱስ ቁርባን አሰጣጥም ሆነ የእምነት አባቶችን እጅ ጨብጦ መሳም ከቀሩት ስርዓቶች መካከል ይገኙበታል።

ይህ ተግባር ግን ሁሉንም ምዕመን አላስደሰተም።