ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ በጀርመን አንዲት ነርስ በኮቪድ ክትባት ፈንታ የጨው ውህድ ሰጥታለች ተባለ
አንዲት ነርስ በኮቪድ ክትባት ፈንታ 'ሳላይን' የተሰኘ ንጥረ ነገር መስጠቷን ተከትሎ በሰሜን ጀርመን ያሉ ባለሥልጣናት ከ8,000 በላይ ሰዎች የኮቪድ ክትባት በድጋሚ እንዲወስዱ እየጠየቁ ይገኛሉ።
ፖሊስ በሰሜን ጀርመን ድንበር አቅራቢያ በፍሪስላንድ በሚገኝ የክትባት ማዕከል ውስጥ የነርሷን ድርጊት በመመርመር ላይ ይገኛል።
በቅድሚያ ስድስት ሰዎች በመጋቢት እና በሚያዝያ ወራት የተለየ ጉዳት የማያስከትል የጨው ውህድ መወጋታቸው ታውቆ ነበር።
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ከ70 ዓመት በላይ የነበሩ እና ለወረርሽኙ ከፍተኛ ተጋላጭ ከሆኑ ቡድን ውስጥ የነበሩ ናቸው።
መርማሪው ፒተር ቢራ ለአንድ የጀርምን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት የ40 ዓመቷ ነርስ የኮሮናቫይረስን የተመለከቱ ትችቶችን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ትሰነዝር ነበር።
መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ያለሙ የእንቅስቃሴ ገደቦችን በመተቸትም ማጋራቷን መርማሪው ገልጸዋል።
ኤንዲአር የተሰኘው ሚዲያ እንደዘገበው 8,557 ሰዎች ክትባቱን በድጋሚ እንዲወስዱ የተጠየቁ ሲሆን እስካሁን 3,600 የሚሆኑት አዲስ ቀጠሮ መያዛቸው ተረጋግጧል።
በሚያዝያ ወር ነርሷ ወለል ላይ የክትባት ብልቃጦችን ጥላ መስበሯን ለመሸፈን ለስድስት ሰዎች ጨዋማውን ውህድ መስጠቷን አምና ነበር።
ነገር ግን የፖሊስ ምርመራን ተከትሎ በርካታ ሰዎች በክትባት ፈንታ ጨዋማውን ውህድ ተወግተው ቤታቸው መሄዳቸው ተደርሶበታል።
ፖሊስ ነርሷ በፖለቲካዊ አላማ ድርጊቱን ፈጽማው ሊሆን ይችላል ብሎ የጠረጠረ ሲሆን ጠበቆቿ ግን ይህንን ውድቅ አድርገውታል። እንዲሁም የተጠቀሰው የጨዋማ ውህድ ቁጥር መጠን ላይም ተከራክረዋል።
በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምስክሮች ቃላቸውን በመስጠት ላይ ሲሆኑ እስካሁን በጉዳዩ ላይ ክስ አልተመሠረተም።
ከኮቪድ መከሰት በኋላ ጀርመን ብዙ የፀረ-ክትባት ተቃውሞዎችን አስተናግዳለች።
የቀኝ አክራሪ ቡድኖች ስለኮቪድ-19 መስፋፋት ይፋዊ መረጃን እና መደምደሚያዎችን ከማይቀበሉት መካከል ናቸው።