ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኦፕያን ቴክ፡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ የጤና አገልግሎት ተስፋ የሆነ ቴክኖሎጂ
ዘላለም ግዛቸው እኤአ በ2014 የተቋቋመው የኦፕያን ቴክ መስራች እና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ነው።
ዘላለም በድርጅቱ ውስጥ በአጠቃላይ 21 ሠራተኞችን የሚያስተዳዳር ሲሆን ከመካከላቸው ስምንቱ ሴቶች መሆናቸውንም ይገልፃል።
ኦፕያን ቴክ የተመሰረተበት ዓላማ የጤና ማዕከላት በቀላሉ በማይገኙባቸው አካባቢዎች የጤና አገልግሎትን በቴክኖሎጂ ድጋፍ ለማዳረስ ነው።
ዘላለም ግዛቸው ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ወደ ሕክምናው ዘርፍ ፊቱን በማዞር የሜዲካል ላቦራቶሪ ቴክኖሎጂ በማጥናት ከተመረቀ በኋላ በጤና ኢንዱስትሪ ውስጥ የላቦራቶሪ ቴክኒሻን በመሆን በአዲስ አበባና በሌሎች ቦታዎች ሰርቷል።
በዚህ ወቅት ለመረጃ ትንተና [ዳታ አናሊሲስ] ፣ ለቴክኖሎጂ እና ለሶፍትዌር አናሊሲስ ልቡ በጣም ቅርብ እንደነበር ይናገራል።
ቀስ ብሎም ፊቱን ወደዚያ በማዞር የተማረበትንና የተመረቀበትን ዘርፍ ሳይለቅ፣ በማታው ክፍለ ጊዜ ኮምፒውተር ሳይንስ በመማር፣ ሁለቱን እውቀቶቹን በማጣመር ለጤና ኢንዱስትሪ የሚሆነውን እገዛ በቴክኖሎጂ መልክ ለማቅረብ ወስኖ 'ኦፕያን ቴክን' መሰረተ።
"በዚያን ጊዜ ሁለት የማይገናኙ ትምህርቶችን አቀናጅቶ መሥራት አልተለመደም ነበርና አጋጣሚው ሲታየኝ ማለፍ አልፈለግኩም ነበር። ትምህርቴን ከጨርስኩም በኋላ ሁለቱን ትምህርቶች የሚያቀናጁ ሥራዎች ሆን ብዬ በመፈለግ መሥራት ጀመርኩ" ይላል ዘላለም።
ኦፕያን ቴክ ምንድን ነው?
ኦፕያን ቴክ በጤና አገልግሎት ውስጥ አንድ ማዕከል የሚያስፈልገውን መሣሪያ፣ ባለሙያና በጀት ቀድሞ በመገምገም ጉድለት ያለበትን አስቀድሞ በመለየት የሚያሟላ ሲስተም ነው።
'የኦፕያን ቴክ' ሶፍትዌር እስከ ሦስት ዓመት ድረስ አንድ የጤና ማዕከል የሚሰጠውን አገልግሎትና የታካሚ ቁጥር ጨምሮ መተንበይ የሚያስችል 'አርተፊሻል ኢንተለጄንስ' እንዳለው ዘላለም ይናገራል።
ይህም ማዕከሉን የሚያስተዳድረው አካል መረጃውን በመጠቀም በአቅምና በአቅርቦት ለመደራጀት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ይረዳዋል።
ኦፕያን ቴክ ስለሚኖረው ጠቀሜታ የሚያስረዳው ዘላለም "ከዕቃ፣ መድኃኒት፣ ከመሣሪያ ግዢና አቅርቦት ጋር የተያያዙ በቅድሚያ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ችግሮችን ሊቀርፍ እንደሚችል አልጠራጠርም" ይላል።
በተጨማሪም "እስከዛሬ ለጤና ማዕከላት የሚያስፈልጉ ግዢዎች ሲፈጸሙ. . . መድኃኒቶች ከሚያስፈልገው በላይ ቀርቦ አገልግሎት ላይ ሳይውሉ ለብልሽት ተዳርገው ለብክነት ይዳረጋሉ። ወይም በተቃራኒው በበቂ ሁኔታ ሳይታዘዝ ይቀርና እጥረት ተከስቶ ታካሚዎች ይቸገራሉ" በማለት ኦፕያን ይህን ክፍተት የመሸፈን አቅም እንዳለው ያብራራል።
ኦፕያን በጤና ሚኒስቴር የሚሠራውን የእቅድ ሥራ የማቃለል ዓላማ አለው። በዚህም ከየክልሉና ከየአካባቢው ከሚገኙ የጤና ተቋማት መረጃ የሚሰበሰብበትን መንገድ በማቀላጠፍ ሥራው ያለስህተት እንዲከናወንና አስተማማኝ እንደሚሆን ዘላለም ያስረዳል።
ይህም ሶፍትዌር ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ የሚሰበሰበው መረጃ እርስ በእርሱ የሚናበብ በመሆኑ ከዋና መሥሪያ ቤት የሚጎድሉ ነገሮችን በማየት ማሟላት ስለሚቻል ብዙ ሥራ እንደሚያቃልል ይናገራል።
በማስከተልም እንደ ኦፕያን ቴክ ያሉ ቴክኖሎጂዎች ቢያንስ ፊት ለፊት ላሉ ችግሮች ኪስ በማይጎዳ መልኩና በቀላሉ መፍትሔ ሊያመጡ እንደሚችል ያስረዳል።
ዘላለም ኦፕያን ቴክን ሲጀምር የጤና ማዕከላት የሚገጥሟቸውን ችግሮች በቴክኖሎጂ እገዛ ለመቅረፍ ቢያስብም "ቴክኖሎጂ ሁሉንም የጤና አገልግሎቶች ችግሮችን ይቀርፋል ማለት ግን ዘበት ነው" ይላል።
ምክንያቱንም ሲያስረዳ የኢንተርኔት ወይም የኤሌክትሪክ መቋረጥ ሥራቸውን እንደሚያስተጓጉለው በመግለጽ ነው።
እንደ ኦፕያን ያሉ ዘመናዊ መፍትሔዎች በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውሉ የኢንተርኔት ግንኙነት እና እርስ በእርሱ እንዲናበብ የሚረዳ ኔትወርክ የሚያስፈልገው በመሆኑ የኤሌክትሪክ ችግር ባለበት ወይም መብራት በሚጠፋበት ወቅት ሥራው እንዲቋረጥ ሊያደርግ መቻሉ ትልቅ መሰናክል ሆኖባቸው እንደነበር ያስረዳል።
ይህን ደግሞ በተለዋጭ መፍትሔ ሊፈቱት እንደቻሉ የተናገረው ዘላለም "መረጃው ከተሰጠው በኋላ ሲስተሙ መብራት ቢጠፋ እንኳን መብራትና ኢንተርኔት በሚመለስበት ወቅት ወዲያውኑ ኮኔክት በማድረግ ጊዜ ሳይፈጅ እንዲናበብ አድርገነዋል። ከዚያም በተጨማሪ ደግሞ ድንገት እንኳን ባይመጣ በሞባይል ኔትወርክ በመጠቀም በሳምንት እንዴ እንዲናበብ አድርገነዋል " በማለት የመብራት መጥፋትና የኢንተርኔት ችግር የጎላ ችግር እንዳልሆነ ገልጿል።
የኦፕያን ቴክኖሎጂ መረጃ ከማሰባሰብና ከማናበብ በተጨማሪ ያሉት መሣሪዎች ሲስተሙ ላይ ተመዝግበው ቢበላሹ ወይም ችግር ቢገጥማቸው ወዲያው የሚያስፈልገው እርምጃ እንዲወሰድ መረጃ ያስተላልፋል።
በኦፕያን ቴክኖሎጂ በጤና አገልግሎት ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ማንኛቸውንም የሶፍትዌርም ሆነ የሃርድዌር ችግሮችን የመፍታት አቅም አለው።
ዘላለም ይህን የኦፕያን ቴክኖሎጂን ከኢትዮጵያ ባሻገር ከአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ) ጋር በመተባበር ወደ 23 አገራት እንዲስፋፋ መደረጉን ተናግሯል።
ኦፕያን ሥራ ከጀመረባቸው አገራት መካከል ኢስዋቲኒ፣ ሩዋንዳ፣ ካሜሩን፣ ኮትዲቯር፣ ስዋዚላንድ፣ ቦትስዋናና ሌሶቶ የተወሰኑት ናቸው። ለሁሉም አገራት እኩል የሚያስፈልገውን ሥልጠና ከሰጡ በኋላ ወደ ሥራ እንዲገቡ የረዷቸውም ብዙ ናቸው።
ከጊዜ በኋላ ደግሞ ዘላለም ይህን ቴክኖሎጂ ወደ ሌሎችም ተጨማሪ አገራት የመውሰድ ሃሳብ እንዳለው ይናገራል።
ዘላለም ቢያንስ በመንገድ እጥረት የሚዘገዩ የሕክምና ውጤቶችን በተገቢ ጊዜ ለማድረስ ሲም ካርድ የሚወስድ ፕሪንተር ዲዛይን ማድረጋቸውን ይናገራል።
ይህ የደምና የመሳሰሉ ምርመራዎች የሚፈጁትን ጊዜ መቀነስ ባይችልም እንኳን ቢያንስ ውጤቱን ለማድረስ የሚፈጀውን ጊዜ በግማሽ የመቀነስ አቅም ያለው ቴክኖሎጂ መሆኑን ይገልጻል።
በተመሳስይ መልኩ በአፍሪካ ውስጥ በጤናው ኢንዱስትሪ የሚገጥሙ ችግሮችን ቀስ በቀስ በቴክኖሎጂ እገዛ መቅረፍ እንደሚቻል እምነት እንዳለው ዘላለም ይጠቅሳል።
በዚህም በተለይ ለብዙ ሰዎች ጥራት ያለውን የጤና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻልም ያምናል።
የኦፕያን ቴክ ቢያንስ በመንገድ ችግር ምክንያት የሚዘገዩ የሕክምና ውጤቶችን በተገቢ ጊዜ ለማድረስ ሲም ካርድ የሚወስድ ፕሪንተር ዲዛይን እንዳስደረገም ይናገራል።
በተመሳሳይ መልኩ በአፍሪካ በጤናው ዘርፍ የሚገጥሙ ችግሮችን ቀስ በቀስ በቴክኖሎጂ እገዛ መቅረፍ እንደሚቻል እምነት እንዳለው ያስረዳል።
"በአሁን ጊዜ የመንገድ፣ የኢንተርኔት ትስስር የመሳሰሉ ችግሮችን ቀርፈን እየሠራን እንገኛለን፤ ግን ከሁሉም በላይ የሚቸግረን እውቀት፣ አቅምና ችሎታ ያላቸውን ወጣት ሠራተኞችን ማግኘት ነው" ይላል ዘላለም።
ለዚህ ደግሞ ትምህርት ቤት ያሉ ወጣቶችን በማሰልጠንና በሥራው ውስጥ በማሳተፍ እየተከታተሉ ከተመረቁ በኋላ የቀጠሯቸው እንዳሉ ይገልጻል።
"የወደፊቱን ወጣት የማብቃት ሥራም እንሠራለን" የሚለው ዘላለም የወደፊት ህልሙ ሰፊና ብሩህ መሆኑን ተናግሯል።