አቶ አሕመድ ሐሰን ሱካሬ፡ የ64 ዓመቱ አዛውንት የፈጠራ ባለሙያ

አቶ አሕመድ ሐሰን ሱካሬ ይባላሉ። የ64 ዓመት አዛውንት ናቸው። እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ነው የተማሩት። እኚህ አዛውንት ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አራት የፈጠራ ባለቤትነት መብት ያገኙባቸው ፈጠራዎች አሏቸው።

"እኔ ብዙ የተማርኩ ሰው አይደለሁም። የፈጠራ ሥራን ከጀመርኩ ግን አርባ ዓመት ሆኖኛል። ፈጠራን ችግር ነው ያስተማረኝ። አሁን ዩኒቨርስቲ ሄጄ ልምዴን እያካፈልኩ ነው" በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ትምህርታቸውን ካቋረጡ በኋላ ጋራዥ ውስጥ ሲሰሩ እንደቆዩ የተናገሩት አቶ አሕመድ፣ አሁን የጋራዡን ቦታ ወደ የፈጠራ ስራዎቻቸው ማምረቻ መለወጣቸውን ያስረዳሉ።

ከፈጠራ ስራቸው መካከል አንዱ ቡና ማጠቢያ ማሽን ሲሆን በብዛት እያመረቱ ይሸጣሉ።

አቶ አሕመድ በ2004 ዓ.ም. በአገር አቀፍ ደረጃ የፈጠራ ስራዎቻቸውን ካቀረቡ 5098 ሰዎች ጋር ተወዳድረው አንደኛ በመውጣት 150 ሺህ ብር፣ ወርቅ እንዲሁም የእውቅና ምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ያስታውሳሉ።

የፈጠራ ባለቤትነት መብት ካገኙባቸው አራት ማሽኖች መካከል ሁለቱን ከልጃቸው ጋር በመሆን መስራታቸውንም ጨምረው አስረድተዋል።

ከልጆቻቸው መካከል አንዱ የእርሳቸውን ፈለግ መከተሉን የሚናገሩት አቶ አሕመድ፣ ሁለት ማሽኖችን በጋራ በመሆን ሰርተው የፈጠራ ባለቤትነት መብት ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ማግኘታቸውን ይናገራሉ።

"በእኔ ጊዜ ብረት የሚቀጠቅጥ ሰው ይናቃል። የእኛ ጎሳ ብረት የሚቀጠቅጥ ሰው የለውም። አሁን ግን ልጄ ስራዬን ወድዶ በመግባት ከእኔ ጋር እየተወዳደረ ነው" ይላሉ አቶ አሕመድ።

አቶ አህመድ ሐሰን ማን ናቸው?

የቡሌ ሆራ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሐሰን ሱካሬ፣ የአካባቢያቸው ነዋሪዎች ሲጠሯች በአያታቸው ስም ሱካሬ በማለት ነው።

አቶ ሐሰን የፈጠራ ስራውን ከጀመሩ አርባ ዓመት ቢሆናቸውም እውቅና ያገኙት ግን ከ12 ዓመታት ወዲህ ነው።

የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ ደግሞ ሽልማት እንዳገኙበት ይናገራሉ።

የፈጠራ ስራ እንዴት እንደጀመሩ ሲናገሩ ፊደል በቅጡ ባይቆጥሩም የማህበረሰቡን ችግር የሚፈታ ፈጠራን ራሳቸውን በራሳቸው ማስተማራቸውን ያስታውሳሉ።

"እኛ አካባቢ ትምህርት ቤት አልነበረም፤ ትምህርቴን ስምንተኛ ክፍል አቋርጩ የመኪና ረዳት በመሆን ስራ ጀመርኩ። ከዚያም በኋላ ወደ ሹፍርና ገባሁ" በኋላም ከሹፍርና ወደ ጋራዥ ስራ መግባታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በጋራዥ ውስጥ ረዳት ሆነው መሰራት የጀመሩት አቶ አህመድ ራሳቸውን ሙያ በማስተማር ወደ ሙሉ መካኒክነት ከዚያም ወደ ጋራዥ ባለቤትነት ተሸጋግረዋል።

"የከፈትኩትን ጋራዥ ወደ ኋላ ላይ ወደ ማሽን ማምረቻ ነው ያሳደግኩት። አሁን ከውጪ የሚመጣውን እሸት ቡና መፈልፈያ በማሻሻል የፈጠራ ባለቤትነት መብት አግኝቻለሁ" የሚሉት አቶ አሕመድ በብዛት በማምረት ለገበያ እያቀረቡ እንደሚጠቀሙ ገልፀዋል።

የአቶ አሕመድ የፈጠራ ስራዎች

አቶ አህመድ እውቅና ካገኙበት የፈጠራ ስራዎቻቸው መካከል አንዱ የቡና ማጠቢያ ማሽን ነው። ሁለተኛው ደግሞ ለባህላዊ የወርቅ ፈላጊዎች የሚያገለግል፣ የወርቅ ድንጋይ መፍጫ ማሽንን በማሻሻል ሰርተዋል። የታጠበ ቡናን ከቦታው በማንሳት ወደ ማድረቂያ አልጋ የሚወስድ ማሽን ደግሞ ከፈጠራ ስራዎቻቸው መካከል ሶስተኛው ነው።

ይህንን የወርቅ ድንጋይን የሚፈጭ ማሺን በጉጂ ዞን የሚገኙ በወርቅ ፍለጋ ላይ የተሰማሩ 16 የወጣት ማህበራት በመግዛት እየተጠቀሙበት መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

አራተኛው የፈጠራ ባለቤትነት መብት ያገኙበት ደግሞ በአነስተኛ የኤሌትሪክ ጉልበት (5.5hp) የሚሰራ የእህል ወፍጮን በማሻሻል የሰሩት ነው።

ከልጃቸው ካሚል አሕመድ ጋር ደግሞ ገብስ በመሸክሸክ ከገለባው የሚያፀዳ ማሽን በመስራት የፈጠራ ባለቤትነት መብት አስመዝግበዋል።

አቶ አሕመድ በ2004 ዓ.ም 150 ሺህ ብር፣ መሬት፣ ወርቅ እና ቴሌቪዥን በሽልማት ማግኘታቸውን ይናገራሉ።

ካገኙት የብር ሽልማት በላይ እውቅና እንደሚበልጥ የሚናገሩት አቶ አሕመድ በፈጠራ ስራዎቻቸው በገንዘብም ተጠቃሚ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ስለ ስራዎቻቸው ሲያብራሩም "ከውጪ የሚገባው ማሽን በ1 ሰዓት 300 ኪሎ ግራም ይፈለፍላል፤ እርሱን አሻሽዬ 800 ኪሎ ግራም የሚፈለፍል ሰራሁ"

የቡና ማጠቢያው ማሽን ደግሞ በአንድ ሰዓት ውስጥ 40 000 ኪሎ ግራም ማጠብ እንደሚችል አብራርተዋል።

የአቶ አህመድን የፈጠራ ስራ የተመለከቱት ቡሌ ሆራ እና አዳማ ዩኒቨርስቲዎች አብረዋቸው ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

አቶ አሕመድ በእነዚህ ዩኒቨርስቲዎች ለሚማሩ የምህንድስና ተማሪዎች ልምዳቸውን በማካፈል እና በማሳየት አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።

"እነዚህ ኢንጂነሮች የምሰራቸውን ስራዎች ያደንቃሉ፤ ከዚያም ይማራሉ፤ ያግዙኛል"

አቶ አህመድ በአሁኑ ጊዜ እምቦጭ አረምን የሚያፀዳ ማሽን የመኪና መለዋወጫዎችን በመጠቀም መስራታቸውን ገልፀዋል።

ወደፊትም ወደ አዲስ አበባም በመቅረብ የራሳቸውን ኢንደስትሪ ለመክፈት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።