ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኮቪድ-19 ክትባቶች ላይ የቀለደው ግለሰብ በቫይረሱ ህይወቱ አለፈ
በማህበራዊ ድር አምባዎች በኮቪድ -19 ክትባቶች ላይ ያሾፈ አንድ የካሊፎርኒያ ነዋሪ ለአንድ ወር ያህል ከቫይረሱ ጋር ሲታገል ቆይቶ ህይወቱ አልፏል።
የሂልሶንግ ሜጋች ቤተክርስቲያን አባል የሆነው ስቴፈን ሃርመን ክትባቱን ከመቃወም ባለፈ በክትባቱ ዙሪያ በተከታታይ ይቀልድ ነበር።
የ34 ዓመቱ ግለሰብ በሰኔ ወር ለ 7000 ተከታዮቹ በትዊተር ገፁ ላይ "99 ችግሮች ሲኖሩብኝ ክትባቱ ግን ከዚህ ውስጥ አይካተትም" ብሏል፡፡
በሳንባ ምች እና በኮቪድ-19 ምክንያት ከሎስ አንጀለስ ወጣ ባለ ሆስፒታል ህክምናውን ሲከታተል ቆይቶ ረቡዕ ዕለት ህይወቱ አልፏል።
ከመሞቱ በፊት በነበሩት ቀናት ውስጥ ሃርመን በሕይወት ለመኖር ያደረገውን ትግል በሆስፒታሉ አልጋው ላይ የተነሳቸውን ፎቶግራፎች በመለጠፍ አሳይቷል፡፡
"እባካችሁ ሁላችሁም ጸልዩ ፣ እኔን ለመተንፈስ ባለመቻሌ በመተንፈሻ ማገዣ መሣሪያ ሊደግፉኝ ነው" ብሏል፡፡
ሃርመን በረቡዕ ዕለት የመጨረሻ የትዊተር መልዕክቱ በመተንፈሻ መሣሪያ ድጋፍ ለመተንፈስ መወሰኑን አስታውቋል።
"መቼ እንደሆነ ባላውቅም እነቃለሁ፣ እባካችሁ ጸልዩ" ሲል ጽፏል፡፡
ሃርመን ከቫይረሱ ጋር እየታገለም ቢሆንም እምነቴ ይጠብቀኛል በማለት ክትባቱን እንደማይቀበል ተናግሯል፡፡
ከመሞቱ በፊት ስለወረርሽኙ እና ስለ ክትባቶቹ በመቀለድ ከአሜሪካን ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ ከሆኑት ከዶክተር አንቶንዮ ፋውቺ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት አለኝ በማለት አስቂኝ ምስሎችን አካፍሏል፡፡
የሂልሰንግ ቤተክርስቲያን መስራች ብሪያን ሂዩስተን ሐሙስ ዕለት በትዊተር ገጻቸው ህይወቱ ማለፉን አረጋግጠዋል፡፡
ሂዩስተን "ቤን የምንወደው ጓደኛችን ስቴፈን ሃርመን በኮቪድ ህይወቱ ስለማለፉ አሳዛኝ ዜና አስተላልፎልናል" ብለዋል፡፡
በኢንስታግራም ላይ ደግሞ "እኔ ከማውቃቸው በጣም ለጋስ ሰዎች አንዱ ሲሆን ብዙ ነገርም ከፊቱ አለ" ሲሉ ጽፈዋል፡፡
"ሁል ጊዜም ወደ ታዳጊዎች እግር ኳስ ጨዋታዎች ይመጣ ነበር። እናም በብዙዎች ይናፍቃል፡፡ ነፍሱ በሰላም ትረፍ፡፡"
አክለውም የቤተክርስቲያኗ ምዕመናን "የዶክተሮቻቸውን መመሪያ እንዲከተሉ" አበረታተዋል፡፡
ካሊፎርኒያ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የኮቪድ -19 ቁጥር እየጨመረ የመጣ ሲሆን ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱት አብዛኛዎቹ ክትባት ያልወሰዱ ናቸው፡፡