በግብፅ በትዳር ውስጥ የሚፈፀም መደፈርን እየታገሉ ያሉ ሴቶች

የግብፅ ሴቶች በፆታዊ ጥቃት ዙሪያ ያሉ ዝምታዎችን እየሰበሩ ነው።

በቅርብ ጊዜያት የተነሳው ትግል ለዘመናት በአገሪቷ የማይጠቀስ የነበረው በትዳር ውስጥ የሚፈጸም መደፈር ነው።

ማስጠንቀቂያ፦ ይህ ፅሁፍ ወሲባዊ ጥቃትን በተመለከተ አንባቢያንን ሊረብሹ የሚችሉ መረጃዎችን ይዟል።

በሠርጓ ምሽት የ34 ዓመቷ ሳፋ በባለቤቷ ተደፈረች። በደረሰባትም ጥቃት በብልቷ አካባቢ፣ በእጅ አንጓዋ ላይና በአፏ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰባት።

"የወር አበባዬ ላይ ነበርኩ እና በዚያች ምሽት ወሲብ ለመፈፀም ዝግጁ አልነበርኩም" የምትለው ሳፋ እምቢተኝነቷ በባለቤቷ ተቀባይነት አላገኘም።

"ባለቤቴ ከእሱ ጋር ወሲብ ላለመፈፀም የምፈጥረው ምክንያት መሰለው። ደበደበኝ፣ እጄን በካቴና አሰረኝ፣ አፍኖኝ ደፈረኝ" በማለት ታሪኳን አጋርታለች።

ሆኖም ሳፋ በማኅበረሰቡ ሊደርስባት የሚችለውን መገለል በመፍራት ባሏ እንደደፈራት ለፖሊስ ሪፖርት ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነችም።

የጥቃት ሰለባዎችን ጥፋተኛ ማድረግ በግብፅ በሰፈነው አባታዊ (ፓትርያርካል) ሥርዓት የተለመደ ነው በተለይም ተጎጂዋ ሴት ከሆነች።

ነገር ግን በሚያዝያ ወር 'ኒውተን ክራውል' ተብሎ በሚጠራው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ውስጥ በረመዳን የሙስሊሞች የጾም ወቅት የተላለፈ ድራማ ባል ሚስቱን ሲያስገድድ የሚያሳይ ትዕይንት ብዙ ነገሮችን ቀየረ።

ለበርካታ ሴቶች ይህ ትዕይንት መጥፎ ትዝታዎችን ቢቀሰቅስም ከዚህ በተጨማሪ ለበርካቶችም ታሪካቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ለማጋራት ብርታት ሆናቸው።

በጥቂት ሳምንታት 'ስፒክ' በተባለ የፌስ ቡክ ገጽ ከ700 የሚበልጡ የገጹ አባላትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምስክሮች ታሪካቸውን ማጋራት ጀመሩ።

ከእነዚህም ውስጥ አንደኛዋ የ27 ዓመቷ ሳና ናት።

"ከተጋባን በአንድ ዓመት ውስጥ መልዓክ ነበር። ቀኔ የደረሰ ነፍሰ ጡር ነበርኩኝ። በማይረባ ነገር ተጣላንና ሊቀጣኝ ፈለገ። ደፈረኝ፤ ጽንሱም ጨነገፈ" ብላለች 'ስፒክ አፕ' ለተሰኘው ፌስ ቡክ ገጽ በላከችው መልዕከት።

ሳና ብቻዋንም እየተሰቃየች፣ ለፋች እንዲሁም በትግሏ ቀጠለች። በአሁኑ ወቅት ከባሏ ጋር የተፋታች ሲሆን የልጇም ሐዘን ልቧን እንደሰበረው ነው።

በግብፅ የተለያዩ ግዛቶች መደፈርና ኃይል የተቀላቀለበት ወሲብ መፈፀም የተለመደ ነው በተለይም በሠርግ ምሽት።

በተለይም የአንድ ታዋቂ ዘፋኝ የቀድሞ ሚስት ባሏ እንዴት እንደደፈራት ታሪኳን ማጋራቷን ተከትሎ ጉዳዩ በከፍተኛ ሁኔታ መነጋገሪያም ሆነ።

በኢንስታግራም ገጿ ላይ በእንባ ተሞልታ ያጋራችው ቪዲዮን በርካቶች ተመልክተውታል፤ ብዙ ሚዲያዎችም ዘገቡት።

የግለሰቧ የቀድሞ ባለቤት የቀረበበትን ክስ "መስረት የሌለው ነው" በማለት ምላሽ ሰጥቷል። እሷ ግን በበኩሏ የፍትህ ሥርዓቱ እንዲቀየርና በወንጀል ሕጉ ዝርዝር ውስጥ እንዲካተተት ጠይቃለች።

በአውሮፓውያኑ 2015 በመንግሥት ስር ባለው ብሔራዊ የሴቶች ምክር ቤት (ኤንሲደብልዩ) በታተመ ጥናት መሰረት በየዓመቱ በትዳር ውስጥ 6500 ያህል ሴቶች ይደፈራሉ፣ ወሲባዊ ትንኮሳ እንዲሁም ሌሎች አስገዳጅ ነገሮችን እንዲፈጽሙ ይገደዳሉ ይላል።

"በትዳር ውስጥ ያለ መደፈር በባህሉ ሴቶችን ጥፋተኛ የማድረግ ነገር አለ። የጋብቻ ውል ማለት ሴቶች በማንኛውም ጊዜ ለወሲብ ዝግጁ መሆን አለባቸው የሚል አንድምታ አለው። ፈቃደኛ ባይሆኑም ሴቶች በትዳር ውስጥ እምቢ ማለት አይችሉም፤ ቢሉም ይገደዳሉ" በማለት የሴቶች መመሪያና የሕግ ግንዛቤ ማዕከል ዋና ሥራ አስፈፃሚና የሕግ ባለሙያ ረዳ ዳንቡኪ ይናገራሉ።

እዚህ ላይ አንዳንድ ሐይማኖታዊ ትርጓሜዎችን መሰረት በማድረግ ያለው የጋራ እምነት አንዲት ሴት ከባለቤቷ ጋር የወሲብ ግንኙነት ለመፈፀም ፈቃደኛ ካልሆነች "ሃጥያተኛ" ትሆናለች እንዲሁም "መላዕክት ሌሊቱን ሙሉ ይረግሟታል" የሚሉ ናቸው ይላሉ።

ይህንን ክርክር ለማስተካከል የሐይማኖታዊ መመሪያዎችን የሚያወጣው የግብጽ እስላማዊ አማካሪ አካል ዳር አር ኢፍታ በበኩሉ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል።

"ባለቤቱ ኃይልን በመጠቀም ሚስቱን አብሯት እንድትተኛ ካስገደደ እሱ ሃጥያተኛ ነው። ይህ ብቻ ይደለም ባለቤቱ ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ መክሰሰስ ትችላለች፤ ሊቀጣም ይገባል" በማለት አትቷል።

ያም ሆኖ የሴቶች የመመሪያና የሕግ ግንዛቤ ማዕከል ባለፉት ሁለት ዓመታት 200 በትዳር ውስጥ የመደፈር ሪፖርቶችን መዝግቧል።

በአብዛኛውም የመጀመሪያው ምሸት የሚፈጠሩ መደፈሮችም እንደሆነ ዳንቡኪ ያስረዳሉ።

የግብፅ ሕግ በትዳር ውስጥ ያለ መድፈርን በወንጀል አይቀጣም። ፍርድ ቤቶች በትዳር ላይ ያለ መደፈርን ማስረጃ ማግኘት ይከብዳል ቢሉም በዓለም ጤና ድርጅት መሰረት በትዳር ውስጥ ኃይልን በመጠቀም ወሲብ መፈፀም መደፈር ነው ወንጀልም ነው ይላል።

ወደ ፍርድ ቤት የሚሄዱ አብዛኛዎቹ በትዳር የመደፈር ጉዳዮች በግብፅ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 60 ምክንያት በጥፋተኝነት አይጠናቀቁም።

"የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ድንጋጌዎች በሸሪዓ (በእስልምና ሕግ) በተደነገገው መብት መሠረት በቅን ልቦና ለተፈፀሙ ማናቸውም ተግባራት ተፈፃሚነት አይኖራቸውም "ይላል አንቀጹ።

ዳንቡኪ በበኩላቸው በትዳር ውስጥ ያለ መደፈርን ማስረጃ ማግኘት ይቻላል ይላሉ።

"ለምሳሌ ሙሉ ሰውነት ላይ ምርመራ በማድረግ ውጫዊ የአካል ጉዳቶችና መበለዝን ማየት ይቻላል። በአፍ ዙሪያ ቁስለቶች ካሉ እንዲሁም በእጅ አንጓዎችም ላይ እንዲሁ መበለዝና ሌሎች ቁስለቶች ማስረጃ ይሆናሉ" በማለት ያስረዳሉ።

ወግ አጥባቂ እሴቶች አሁንም በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ስፍራ በሚሰጣቸው ግብፅ ለውጥ ለመምጣት ዘገምተኛ ነው።

ነገር ግን በትዳር ውስጥ መደፈርን በተመለከተ በርካታ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ድምፅ መሰማት ተጀምሯል።

*ማንነታቸውን ለመጠበቅ ሲባል የሳፋ እና የሳና ትክክለኛ ስሞች ተቀይረዋል