ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሴቶች ስም መጠራት እንደ ውርደት የሚታይባት አፍጋኒስታን
አንዲት ሴት ለጊዜው ራቢያ ብለን እንጥራት። ራቢያ በምዕራባዊ አፍጋኒስታን ነዋሪ ናት። በአንድ እለትም ሰውነቷ የተቃጠለ እስኪመስላት ድረስ ከፍተኛ ሙቀት ተሰማት፤ ሰውነቷም ተንቀጠቀጠ። እናም ወደ ጤና ተቋም አመራች።
ዶክተሩ መረመራት እናም ህመሟ ኮሮናቫይረስ እንደሆነም ገለፀላት።
ራቢያ ህክምናዋን ጨርሳ ወደቤቷ ተመለሰች። ቤትም ደርሳ ዶክተሩ ያዘዘላትን መድኃኒት እንዲገዛላት የማዘዣ ወረቀቱን ሰጠችው።
የመድኃኒት ማዘዣ ወረቀቱን ተቀብሎ ስሟን ሲያየው በጣም ተናደደ። በከፍተኛ ሁኔታ ያስቆጣውም "ለእንግዳና ለማታውቀው ወንድ" ስሟን መንገሯ ነበር።
ይህ ምናልባት ለሌሎች እንግዳ ሊሆን ይችላል። በአፍጋኒስታን ግን ባል ብቻ ሳይሆን ሌሎች የቤተሰቧ ወንድ አባላት ሴቶች ለውጪ ሰዎች ስማቸውን እንዳይናገሩ ያስገድዷቸዋል። ስማቸውንም ተናግረው ከተገኙ ክፉኛ ድብደባ ይደርስባቸዋል።
ለአንዳንዶች ግን ይህ ያረጀ፣ ያፈጀና ኋላ ቀር ባህል አልተዋጠላቸውም፤ ለመቀየርም እየታገሉ ነው።
'ስሜ የት አለ' ዘመቻ?
የችግሩ ምንጭ ሴት መሆንን በወጉ ካልተቀበለው ማኅበረሰብ ጋር በፅኑ የተቆራኘ ነው። ስትወለድ ይጀምራል።
እንደ ጨቅላ ወንዶች ዳቦ ተቆርሶ፣ ድግስ ተደግሶ ቀድሞ ስም አይወጣላትም። ዓመታትም ይወስዳል ስሟ እስኪወጣላት ድረስ።
ስታገባም ስሟ በምንም መልኩ አይጠራም። የሠርግ መጥሪያ ካርዱም ላይ ስሟ አይጠቀስም።
እንዲሁ ስትታመመም ስሟ ለሐኪም መነገር የለበትም። በመድኃኒት ማዘዣ ወረቀቱም መስፈሩ የሐጥያት ያህል ይቆጠራል።
በዚህ አያበቃም ህይወቷ ቢያልፍም በሞት ሰርቲፊኬት ላይ ጭራሽ ስሟ አይሰፍርም። ሐውልት ቢሰራም ስሟ አይጠቀስም፤ ባዶ ሐውልት።
ለብዙዎች ስም ቀላል የሚመስለው ለአፍጋኒስታውያን ግን ደግሞ የነፃነት ጥያቄ ነው። ለዚያም ነው በነፃነት ስማቸው እንዲጠቀስና እንዲጠሩበት "ስሜ የት አለ?" የሚለው ዘመቻ የተጀመረው።
ይህም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ዘንድ ከፍተኛ ንቅናቄንም እየፈጠረ ነው።
"የወንድሜ፣ የአባቴና የእጮኛዬ ክብርስ?"
ከራቢያ የትውልድ ቀዬ ሄራት የመጣች ሌላ ሴት ስሟን መንገር አትፈልግም፤ ስሟ አለመጠራቱም ለእሷ ምክንያታዊ ነው።
"አንድ ሰው ስሜን ሲጠይቀኝ የወንድሜን፣ የአባቴንና የእጮኛዬን ክብር ላለማስደፈርና ለማስከበር ስል አልናገርም" የምትለው ይህች ግለሰብ "ለምን ቤተሰቦቼን አበሳጫቸዋለሁ? ስሜን መንገሩ ትርጉሙ ምንድን ነው?"
"የእከሌ ልጅ፣ የእከሌ እህትና ለወደፊቱም የእከሌ ባለቤትና የልጄንም ስም ጠርተው የእከሌ እናት በሚል እንዲጠሩኝ ነው የምፈልገው" ብላለች።
ይሄ ለሰሚው ግራ የሆነ ነገር ለሌላው ማኅበረሰብ አስደንጋጭ ቢሆንም በአፍጋኒስታን ግን የተለመደ ነው። እንዲያውም አንዲት ሴት በስሟ ብትጠራ ነው እንደ ነውር የሚታየው እንዲሁም ቤተሰቦቿን እንደሰደበችና እንዳዋረደች የሚቆጠረው።
አብዛኞቹ አፍጋኒስታናዊያን ወንዶች ይህንን ተቀብለው የእህቶቻቸውን፣ የባለቤቶቻቸውን እንዲያውም የእናቶቻቸውን ስም በይፋ መጥራት እንደ አሳፋሪና መዋረድም ስለሚያዩት አክብረውትና አስከብረውትም ይኖራሉ።
በባህሉም አንዲት ሴት የእከሌ እናት፣ እህት ተብላ የምትጠራ ሲሆን በቤትም ውስጥ ትልቅ ወንድም ካለም እሰዬው፤ ከእሱ ጋር በተያያዘ ይሆናል የሚጠሩት።
በባህሉ ብቻ አይደለም በአፍጋኒስታን ሕግ መሰረት በልደት የምስክር ወረቀት ላይ መስፈር ያለበት የአባት ስም ብቻ ነው።
ከባለቤታቸው ጋር የተለያዩትስ?
ከባለቤቶቻቸው ጋር የተለያዩት በማን ይጠሩ ይሆን? ያለእድሜ ጋብቻ ተቀባይነት ባለበት አፍጋኒስታን ፋሪዳ ሳዳት ገና ነፍስ ሳታውቅ በጨቅላነቷ ተዳረች። የመጀመሪያ ልጇንም ሳትጠና በአስራ አምስት ዓመቷ ወለደች። አራት ልጆችም ከባለቤቷ ወለደች።
ከባለቤቷ ጋር በይፋ ባትፋታም፣ ተለያይታ አራት ልጆቿን ይዛ ወደ ጀርመን ተሰደደች።
የቀድሞ ባለቤቷ ልጆቹን በአካልም ሆነ በስልክም ጠይቋቸው አያውቅም። የህይወታቸው አካልም አይደለም።
"ይህ ሰው እንዴት አባት ተብሎ ስሙ የልጆቹ መጠሪያ ይሆናል?" ስትልም ትጠይቃለች። ያላሳደጋቸውና አይቷቸው የማያውቅ አባት በልጆቿ መታወቂያ ካርድም ስሙ የመስፈር መብት እንደሌለውም ታምናለች።
"ልጆቼን በራሴ ጥሬ ግሬ ነው ያሳደግኳቸው። ባለቤቴ አልፈታም ብሎኝ እንደገና ማግባትም አልቻልኩም" የምትለው ፋሪዳ "በልጆቼ መታወቂያም ስሙ እንዳይሰፍር አድርጌያለሁ።"
"ልከ እንደ ቀድሞ ባለቤቴ በርካታ ሚስቶች ያሏቸው ልጆቻቸውንም ዘወር ብለው የማያዩ አፍጋኒስታናዊያን ወንዶች ብዙ ናቸው" ትላለች።
"የእናቶች ስም በልጆቻቸው የልደት የምስክር ወረቀት ላይ መስፈር አለበት። የአፍጋኒስታን ፕሬዚዳንትም ሕጉን እንዲቀይሩ እማፀናለሁ" ብላለች።
የዘመቻው መጧጧፍ
"ይህ ሁኔታ በዚህ መቀጠል የለበትም" የ28 ዓመቷ አፍጋኒስታናዊት ከሦስት ዓመት በፊት ለእራሷ የገባችው ቃል ነበር።
ከሄራት ግዛት የመጣችው ላሌህ ኦስማኒ ከመሰላቸቷና ጭቆናውን ለመቋቋምም ባለመምረጧ 'ስሜ የት አለ?' የሚል ዘመቻን ጀመረች። ዘመቻው መሰረታዊ የሚባለውን በስም የመጠራት መብታቸውን ለሴቶች ለመመለስ ያለመ ነው።
ሳሌህና ጓደኞቿም አፍጋኒስታናዊያን ሴቶች ማንነታቸው ሲነጠቅ ዝም ብለው ለምን ይመለከታሉ በሚልም ዘመቻውን እንደጀመሩም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ዘመቻው በአሁኑ ወቅት የአፍጋኒስታን መንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳደረ ሲሆን፤ መንግሥት ሕጉን በመቀየር የልደት ሰርቲፊኬት ላይ ከአባቶች በተጨማሪ የእናቶች ስምም እንዲሰፍር በቅርቡ ያደርጋል የሚል እምነት አለን" ብላለች።
የተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ማርያም ሳማ በቅርቡ የእናቶች ስም በልደት ሰርቲፊኬት እንዲካተት በፓርላማ የተናገሩ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ድጋፍም ለማሰባሰብም በሚል በትዊተር ገፃቸው ላይ መልዕክቱን አስፍረዋል።
ተቃውሞ
ሳሌህ በዘመቻው ጉዳይ ከቢቢሲ ጋር ያደረገችው ቆይታ በቢቢሰ ፌስቡክ መውጣቱን ተከትሎ ድጋፍ እንዲሁም ውግዘትን አስተናግዷል።
አንዳንዶችም በፌዝና በስላቅ መልኩ የልደት የምስክር ወረቀት ላይ የዘመድ አዝማድ ስም እንዲካተት ዘመቻ ትጀመር ይሆናል ብለዋል።
በቤተሰብ ውስጥ ሰላም መስፈን አለበት "የሚቀድመውን እወቂ" ያሏትም አልታጡም።
በርካታ ወንዶች የልጇ ልደት ምስክር ወረቀት ላይ ስም እንዲሰፍር የምትጠይቀው አባቱን ስለማታውቀው ነው በማለት ለመዝለፍ ሞክረዋል።
ሳሌህ በበኩሏ ነቃ ያሉና ነገሮችን ቀለል ባለና ሰፋ ባለ መልኩ ይመለከታሉ ብላ የምታስባቸው የወጣቱ ትውልድ አባላት እንዲህ አይነት አፀያፊ አስተያየቶች መስጠታቸው አሳዝኗታል።
የታዋቂ ሰዎች ድጋፍ
በአፍጋኒስታን ውስጥ ስመ ጥር የሆኑት ሙዚቀኛና የሙዚቃ አዘጋጅ ፋራሃድ ዳርያና ሙዚቀኛና የሙዚቃ ፀሐፊ የሆነችው አርያና ሳይድ ለዘመቻው ያላቸውን ድጋፍ አሰምተዋል።
ፋርሃድ እንደሚለው ሴት እናት፣ እህት፣ ልጅ፣ ሚስት መሆኗ ሚና እንጂ የሴት ማንነት አይደለም።
"ሴቶችን ባላቸው ሚና ብቻ ስንጠራቸው ዋናው ማንነታቸውን ማጥፋትና መደምሰስ ነው" በማለት ያስረዳል።
አክሎም "ወንዶች የሴቶችን ማንነት ሲነጥቋቸውና ሲክዷቸው በጊዜያትም ውስጥ ሴቶች እራሳቸው ማንነታቸውን ያደበዝዙታል" ይላል።
በአፍጋኒስታን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ዝናን ከተጎናፀፉት መካከል አርያና ሳይድ አንዷ ስትሆን የሴቶች መብትም ታጋይ ናት። ዘመቻውን ብትደግፍም እንዲህ በቀላሉ ይሳካል የሚል ተስፋ የላትም።
"ፀሐይና ጨረቃ አላይዋትም "
"የሴቶችን ማንነት የመንጠቅ መሰረቱ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሰፈነው ጨቋኙ አባታዊ ሥርዓት ሲሆን ለወንዶች ክብር ሲባል ሴቶች ሰውነታቸውን እንዲደብቁ ብቻ ሳይሆን ስማቸውም እንዳይጠራ ተደርጓል" በማለት አሊ ካቬህ የተባለው የማኅበረሰብ አጥኚ ይናገራል።
"በአፍጋኒስታን ማኅበረሰብ ዘንድ ጨዋ (ድንቅ) ሴት የምትባለው ድምጿ የማይሰማ እንዲሁም ልታይ ልታይ የማትል ናት። ይህንንም ለማጠናከር ፀሐይና ጨረቃ አላይዋትም የሚባል አባባል አለ" ይላል።
"ቆፍጠን ያሉ ወይም ደግሞ ጨካኝ ወንዶች በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚከበሩና ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው። በቤተሰቡ ዘንድ ቀለል ያሉና ፈታ ያሉ ሴቶች ቅሌታምና ክብርን ያዋረዱ አድርገው ይቆጠራሉ" በማለትም ስር ስለሰደደው ሥርዓት ያስረዳል።
በእንግሊዝ ተቀማጭነቱን ያደረገው ሱሬ ቴክኖሎጂ ማዕከል የቴክኖሎጂ ሥራዎች ፈጣሪ የሆነችውና በርካታ ሽልማቶችን የተጎናፀፈችው የህክምናና የፊዚክስ ባለሙያ ሻክሮዶክት ጃፋሪ "ለአፍጋኒስታን ሴቶች ከማንም ጥገኛ ያልሆነ ማንነት እንዲኖራቸው የገንዘብ፣ ማኅበራዊና ከሌሎችም ስሜቶች ነፃ ሊሆኑ ይገባል" ትላለች።
አክላም እንደ አፍኒጋኒስታን ባለሉ አገሮችም "የሴቶችን ማንነት የሚነጥቁትም ሆነ የሚክዱት ላይ መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ ሊወስድ ይገባል" ትላለች።
የታሊባን መንግሥት ከወደቀበት ከሁለት አስርታት በኋላ የአገሪቱ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሴቶች ወደ አደባባይ እንዲመለሱ እየሞከሩ ነው።
ነገር ግን እንደ ራቢያ ያሉ ሴቶች ለሐኪሞች ስማቸውን በመንገራቸው አሁንም ክፉኛ ይደበደባሉ።
ሻክሮዶክት እንደ አፍጋኒስታን ባለ ጨቋኝ አባታዊ ሥርዓት ስር በሰደደበት ባህላዊ ማኅበረሰብ ውስጥ የማኅበረሰቡ ትግል ብቻ ሳይሆን መንግሥት ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃትና ጭቆና ለማስቆም ሕጋዊ መንገዶችን ሊያረጋግጥ እንደሚገባም ትናገራለች።
የስም ጉዳይ በአፍጋኒስታን ፓርላማ ውስጥ ቢነሳም ፖለቲከኞቹ 'ስሜ የት አለ?' ለሚለው ምን አይነት ምላሽ አላቸው የሚታይ ይሆናል።