ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ ከዛፍ ላይ ተሰቅሎ የተገኘው ኢትዮጵያዊው አማኒ ሞት ያስነሳው ጥያቄ
አማኑኤል ታምራት ኪልዲያ (አማኒ) በአምስት ዓመቱ ከአሜሪካ ለመጡ ነጭ ባልና ሚስት በማደጎ ተሰጠ። አዲስ አበባ የተወለደው አማኒ አማርኛ ብቻ ነበር የሚናገረው ግን የማደጎ ቤተሰቦቹ እንደሚሉት "አዕምሮው ብሩህ ስለነበር እንግሊዝኛ በአጭር ጊዜ ነው አቀላጥፎ መናገር የቻለው።"
አዲስ አገር፣ አዲስ ቤተሰብ ሁሉ ነገር "ባዕድ" ወደሆነባትም አሜሪካ፣ ኒውጀርሲ፣ ሞሪስ ከተማ በጨቅላነቱ አቀና።
አማኒ በአሜሪካ ውስጥ አስራ አምስት ዓመታትን እንዲሁም በዚህች ዓለም ላይ ደግሞ ሃያ ዓመታትን ብቻ ነው መኖር የቻለው። ሊውስ ሞሪስ ፓርክ በሚባል ስፍራም ዛፍ ላይ ተሰቅሎም ሰኔ 21/2012 ዓ.ም ሞቶ ተገኘ።
አማኒ የሞተበት ፓርክ ከሚኖርበት ሰፈር የአንድ ሰዓት ያህል ርቀት ላይ ይገኛል። ከምሽቱ 2፡47 አካባቢ አንድ የፓርክ ጎብኝ በድን የሆነውንና ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ የነበረውን አስከሬኑን በማየቱ ለፓርኩ ፖሊስ አሳወቀ።
የሞሪስ ግዛት አቃቤ ሕግም አማኒ ራሱን አጥፍቷል የሚለው መደምደሚያ ላይ የደረሰው በፍጥነት ነበር። በርካቶች ግን አንድ ወጣት ጥቁር ዛፍ ላይ ተሰቅሎ መገኘት ጥያቄን አጭሮባቸዋል ምክንያቱም አሜሪካ በጥቁር ዜጎቿ ላይ ለምዕተ ዓመታት ያህል የፈፀመችው የጭካኔ ታሪክ መገለጫ በመሆኑ።
አፍሪካውያን በባርነት ተግዘው እግራቸው አሜሪካንን ከረገጠባት ዕለት ጀምሮ "እምቢተኝነትን" አሳዩ ተብለው መገረፍ፣ መገደል እንዲሁም በዛፍ ላይ መስቀል በታሪክ ብቻ የሚታወቅ ሳይሆን፤ ነፃነታቸውን ከተጎናፀፉ በኋላም ዛፎች ላይ እያንጠለጠሉ መግደል የአሜሪካ እውነታ ነው።
ለዘመናት ጥቁሮችን ዛፍ ላይ በመስቀልና ጥቁሮችን በማቃጠል የሚታወቀው የኬኬኬ (ኩ ክሉክስ ክላን) ከተመሰረተበት ከጎርጎሳውያኑ 1865 እስካሁን ድረስ ተመሳሳይ ግድያዎችን ይፈፅማል።
ከቀናት በፊት በጠራራ ፀሐይ የነጭ የበላይነትን በሚሰብኩ ግለሰቦች ዛፍ ላይ ሊሰቅሉት ሲሉ የተረፈው ጥቁር ዜና በአሜሪካ ውስጥ መሰማትና ሌሎች ጥቁሮችም እንዲሁ በነጭ ዘረኞች ከመገደል ጋር ተያይዞ አማኒ ራሱን አጥፍቷል መባሉ ተቀባይነት አላገኘም።
የአማኒ አሟሟት ትርጉም ያልሰጣቸው አካላትም ፍትህን እየጠየቁ ነው። 'ቼንጅ' በተሰኘ ድረገፅም ላይ 245 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ኢትዮጵያዊ- አሜሪካዊው ታዳጊ ፍትህ እንዲያገኝ በመጠየቅ ፊርማቸውን አኑረዋል።
"በጥቁርነቱ ምክንያት ተገድሎ ይሆናል እናም ያለምንም ምርመራ ራሱን አጥፍቷል የሚለው ነገር ተቀባይነት የለውም። የተሻለ ፍትህ አማኒ ይፈልጋልም" በማለት ፅሁፉ አስፍሯል።
ፅሁፉ አክሎም "መሰላልም ሆነ ሌላ ነገር በሌለበት፤ እንዴት አንድ ሰው ያለማንም እርዳታ ራሱን ከዛፍ ላይ የሚሰቅለው? አሟሟቱ ላይ የተደረገው ምርመራ እንደገና መጀመር አለበት" በማለት ጥያቄን አጭሯል።
የግዛቲቱ ፖሊስ ራሱን አጥፍቷል ቢልም የብላክ ላይቭስ ማተር እንቅስቃሴ አራማጆችና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ አስተያየታቸውን እየሰጡ ያሉ ሰዎች ዘንድ "ራሱን ገድሏል" የሚለው መደምደሚያ ተቀባይነት አላገኘም።
ነገር ግን የሞሪስ ግዛት ዐቃቤ ሕግ ፍሬዲሪክ ናፕ ባወጡት መግለጫ "ወንጀል ተፈፅሟል ብለን አናምንም። የህክምና ምርመራ ውጤትም እንደሚያሳየው ራሱን ማጥፋቱን" ነው ቢሉም በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ እንቅስቃሴ መፈጠሩንም ተከትሎ ከዚህ በፊት የሰጡትን መግለጫ ለመቀየር ተገደዋል።
"በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንደሚባለው ሳይሆን ምርመራው አሁንም ክፍት ነው። አጠቃለን እንዲህ ነው የሚባል ውሳኔ ላይ አልደረስንም። የመጀመሪያ መግለጫችንም የምርመራው የመጀመሪያ ውጤት ነው። አሁንም ቢሆን ከተለያዩ የፍትህ አካላት ጋር በመጣመር አሟሟቱ ላይ የሚደረገው ምርመራ ቀጥሏል" ብለዋል።
በሞሪስ ግዛት የብላክ ላይቭስ ማተር መስራች ቲያና ኪምቦርግ ዐቃቤ ሕጉ መግለጫቸውን አሻሽለው ከማውጣታቸው በፊትም "የግዛቷ ዐቃቤ ሕግ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም። ግልፅነት ይጎላቸዋል። ምርመራ ከመካሄዱ በፊት በሞተ ሰባ ሁለት ሰዓታት ውስጥ ራሱን አጥፍቶ ነው ብሎ መናገር ፍትሃዊነት የጎደለውና የአካባቢውን ማኅበረሰብም የናቀ ድርጊት ነው" ብላለች።
አማኒ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ ኤፍቢአይን ወይም ሲአይኤን የመቀላቀል ህልም እንደነበር የምትናገረው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ "ገና ሃያ ዓመቱ ቢሆንም ማኅበረሰቡን ከማገልገል ወደኋላ አላለም። ከጓደኞቹም ጋር በመሆን ኒውጀርሲ ያሉ ህፃናትን ኢላማ ያደረጉትን ደፋሪዎችን የሚያጋልጥ ቡድንም መስርተው ከ30 በላይ የሚሆኑትን አጋልጠዋል" ብላለች።
ህፃናት ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ሰዎችን በማጋለጡ እንደተገደለም ታምናለች። "አማኒ ለማኅበረሰቡ ይሰራ የነበረው ሥራ ደፋርና ጀግና መሆኑን ቢያሳይም አደገኛ ነበር። ምንም እንኳን ዐቃቤ ሕግ ለግድያ የሚያበቃ ምክንያት የለም ቢልም፤ እኛ ግን እሱን ዝም ማስባል የሚፈልጉ ምክንያት አላቸው። ወንጀለኞቹን ማጋለጡ ለበቀል አነሳስቷቸዋል ብለን እናምናለን" ብላለች።
"ደግ አይበረክትም"
አንዳንድ ሰዎች ወደዚህ ዓለም የሚመጡት የአጭር ጊዜ አላማን ለማሳካት ሲሆን፤ ዓለምን በደግነታቸው ሞልተዋት፤ ከሚኖሩት ጊዜ በላይ በርካታ ነገሮችን ሰርተው ያልፋሉ የሚባል እምነት በበርካታ አገራት ያለ ሲሆን በኢትዮጵያም "ደግ አይበረክትም" ይባላል። አማኑኤልም በኖረባት አጭር ህይወት ደግነቱ የተትረፈረፈ እንደነበር የሚያውቁት ሰዎች እንዲሁም ቤተሰቦቹ ይመሰክራሉ።
"አማኒ ደግ፣ ቀና፣ ልቡ ሩህሩህና የዋህ ነበር። የሰው ሁሉ ስሜት ይሰማው የነበረ፣ የብዙዎችን ሐዘን እንደራሱ አድርጎ የሚወስድ ነበር። ትልቅ፣ ትንሽ ሳይባል ያወቀው በሙሉ ያደንቀውና ይወደው ነበር። ሁሉም ሰው ይወደኛል የሚለውን ሃሳብ ቢጠራጠርም እኛ ግን ሁሉም ይወደው እንደነበር እናውቃለን" በማለትም የማደጎ ቤተሰቦቹ ቄስ ቶም ኪልዲያና ባለቤታቸው ጃኒስ የህይወት ታሪኩ ላይ አስፍረዋል።
ወንድሙና እህቶቹ ይወዱት እንደነበር እንዲሁም ወላጅ እናቱ ገነት፣ አክስቱ፣ አጎቶቹና የአጎቶቹ ልጆችም ለእሱ የተለየ ፍቅር እንደነበራቸው የህይወት ታሪኩ ላይ ሰፍሯል።
ሌላኛው የትምህርት ቤት ጓደኛው ኦውን ኮውልድ እንደ አማኒ አይነት ሰው እንደማያውቅም በማዘን መስክሯል "በጣም አስቂኝ፣ ጎበዝና ለሰው ከልቡ የሚያዝን፣ ሩህሩህ ነበር። እንደሱ አይነት ሰው መቼም የማገኝ አይመስለኝም። ሁሌም ፈገግታ ከፊቱ አይጠፋም። ከሰዎች ጋር ብዙ ስንጣላም የሚያስቀን እንዲሁም የሁላችንም ሰብሳቢ እሱ ነበር" ብሏል።
ሌሎችም በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ህይወቱን እየዘከሩ ያሉ ሰዎች ስለ አማኒ ተመሳሳይ አስተያየት የሰጡት ነገር ቢኖር "ለሰው ልጅ ያለው አዛኝነት ጥልቅና ሩህሩህ መሆኑን ነው።"
በነጭ ባልና ሚስት በማደጎ ከቤተሰቡ ተነጥሎ ወደ አሜሪካ የሄደው አማኑኤል በሚኖርበት አካባቢ ከፍተኛ ተሳትፎን ያደርግ ነበር።
ህፃናትን የሚደፍሩና፤ ኢላማ ያደረጉ ግለሰቦችን የሚያጋልጥ 'ፔዶ ጋት ኮውት' የተባለ እንቅስቃሴንም ከመሰረቱት መካከልም አንዱ ነው።
እሱና ጓደኞቹ የሚያደርጉት ይህ ተግባር ደፋሪዎችን በትልልቅ መደብሮች ወይም የሕዝብ ቦታዎች ላይ በመቅጠር ቪዲዮ በመቅረፅ ለሕዝብ የሚያጋልጥ እንቅስቃሴም ነው። የእነዚህን ግለሰቦች የሚያሳፍር ሥራ ለማሳወቅም ኢንስታግራምን ይጠቀማሉ።
ቡድኑ የከንቲባ ልጅን ጨምሮ ከሰላሳ በላይ ህፃናትን ኢላማ የሚያደርጉ ግለሰቦችን እንዳጋለጠና ለፍርድም እንዳቀረበም ከበርካታ ዘገባዎች መረዳት ይቻላል።
ይሄ ሥራቸው በግዛቲቱ አስተዳደሪዎችንም ሆነ፣ በፖሊስ ሥራ ጣልቃ ገብተዋል ከሚሉ አካላት እንዲሁም በሚያጋልጧቸው ሰዎች ዘንድ ቅሬታን ፈጥሮ ነበር።
እናም ለዚህ ነው በርካታ ሰዎች የአማኒ ሞት ከሚታገልልለት የማኅበራዊ ፍትህ ሥራዎች ጋር ተገናኝቶ ሊሆን ይችላል ብለው የሚጠይቁት።
እነዚህ ያጋለጣቸው ከ30 በላይ ግለሰቦችና ከእነሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው በፖሊስ ተመርምረው እንደሆነ ከሚጠይቁት መካከል ቲያና አንዷ ናት።
በአሁኑ ሰዓትስ ሊያጋልጣቸው የነበሩ ደፋሪዎችስ ነበሩ ወይ? እንዴት ወደ ፓርኩ መጣ? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው ትላለች።
ቤሰተቦቹ ካሰፈሩት የህይወት ታሪኩ እንዲሁም በእሱ ዙሪያ ከተሰሩ ዘገባዎች መረዳት የሚቻለው አማኒ ለእግር ኳስና ለቅርጫት ኳስ ለየት ያለ ፍቅር እንደነበረው ነው። በተለይም ህፃን እያለ ኳስን ከእሱ መነጠልም አስቸጋሪ ነው በማለት ቤተሰቦቹ ምስክርነት ሰጥተዋል።
"በተፈጥሮውም ድንቅ አትሌት ነው" የሚልም ፅሁፍ በህይወት ታሪኩ ላይ ሰፍሮ ይገኛል።
ዌስት ሴንትራል የተባለ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው አማኒ፤ በትምህርት ቤትም ውስጥ ቅርጫት ኳስ እንዲሁም እግር ኳስ ይጫወት ነበር።
ዌስት ሞሪስ ሴንትራል ወልፍ ፓክ ለሚባል ቡድንም ጋር እግር ኳስ ይጫወት ነበር። ለጨዋታና ለማሸነፍ ትልቅ ቦታ የነበረው አማኒ ብሩህ አዕምሮም ያለው ነበር በማለት ብዙዎች ገልፀውታል።
ብዙ ጊዜ በማደጎ ከተለያዩ አገራት ወደ አሜሪካ የሚሄዱ ህፃናት ፈታኝ ህይወት እንደሚኖሩና አድገውም ማንነታቸውን ፍለጋ እንደሚባዝኑ መስማት የተለመደ ነው።
በተለይም ጥቁር ህፃናት በነጭ ቤተሰብ ውስጥ ሲያድጉ ልጆቹ የመጡበትን ባህልና ታሪክ አለመገንዘብ፤ መነጠላቸውን አለማሰብ እንዲሁም በሄዱባቸው አገራት የሚያጋጥማቸውን ማኅበራዊ መገለሎች እንዲሁም መዋቅራዊ ዘረኝነት እንደሚገጥማቸው በዚህ ህይወት ውስጥ ያለፉ በርካቶች ሲናገሩም ተሰምተዋል።
የአማኒም የቤት ውስጥ ህይወት ቀላል እንዳልነበረ ቤተሰቦቹ ከፃፉት የህይወት ታሪክም መረዳት ይቻላል። ይሄንም አባቱ አማኒን ደግ ቢሆንም "በጥባጭ" ነው ያሉት ሲሆን "ቤት ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ለአማኒ ፈታኝ የነበረ ቢሆንም ከልባችን እንወደው ነበር። ከእኛም ሆነ ከዓለም በመለየቱ በቃላት መግለፅ የማይቻል ሃዘን ተሰምቶናልም" በሚልም የህይወት ታሪኩ ላይ ሰፍሯል።
ሆኖም ግን ቤተሰቡ አማኒ ያከናውናቸው በነበሩ ተግባራቱና ማኅበረሰቡን ለማገልገል በነበረው ቁርጠኝነት ይኮሩበት እንደነበርም በፅሁፋቸው ገልፀዋል።
ሪዲመር ሉተራን በተባለ ቤተክርስቲያን ውስጥ ፓስተር የሆኑት አባቱ "እንደ ማንኛውም ሰው ቢሮ ውስጥ ገብቶ መስራት ለእሱ አይዋጥለትም ነበር" በየካቲት ወር ላይ የወታደርነት ስልጠና ወስዶ መመረቁን በማውሳት እንዴት ለቤተሰቦቹ ኩራትም እንደነበር ተናግረዋል።
'አርሚ ሪዘርቭስ' ከሚባለው ተቋምም የውትድርናና የፖሊስ መሠረታዊ የሚባል ስልጠናን ወስዷል። ከእሱ ጋር ይህንን ስልጠና የወሰደ ኖህ ብራመር የተባለ የልብ ጓደኛው "ስልጠናውን አስደሳች አድርጎታል። ፈገግታው እንዲሁም ቀልዱ አሁንም ፊቴ ድቅን ይላል። እሱን አለመውደድ አይቻልም፤ ምንም አይነት ድብታም ሆነ ጭንቀት አይቼበት አላውቅም። የነገረኝ ነገርም የለም" ብሏል።
አማኒ የአሜሪካውን የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይን ወይንም ሲአይኤን የመቀላቀልም ህልም እንደነበረው ስለሱ የሚያዉቁ ሰዎች ይመሰክራሉ። በዚህ አመትም ጄምስ ማዲሰን ዩኒቨርስቲም ገብቶ ትምህርቱንም ለመከታተል በጉጉት እየጠበቀ ነበር ተብሏል።
ህልሙን እውን በማድረግ የተለያዩ አስተዋጽኦዎችን ለማኅበረሰቡ ለማበረክት ይጥር የነበረው አማኒ፤ በግዛቲቱ ውስጥ ባለፉት ሁለት ወራት ዛፍ ላይ ተሰቅለው ከሞቱት ሰዎች መካከል አራተኛው ነው።
ሞቱ አወዛጋቢ ቢሆንም ቤተሰቦቹ ግን ራሱን አጥፍቷል የሚለውን ውሳኔ በፀጋ ተቀብለውታል ተብሏል። ቤተሰቦቹ እንዲህ ያለ ምርመራ መቀበላቸው በበርካቶች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። ከፍተኛ ትችትም ቀርቦባቸዋል።
ዐቃቤ ሕጉ አጠቃላይ እየተካሄደ ስላለው የምርመራ ሂደት ሙሉውን መረጃ ለሕዝብ ይፋ ባያደርግም የህክምና ምርመራ ውጤቶችን ግን ማጣጣል ተገቢ አይደለም እተባለ ቢሆንም፤ ቲያኒ በበኩሏ ነፃ በሆነ አካል የአስከሬን ምርመራ እንዲደረግም ጠይቃለች።
"በርካታ ጥቁር አሜሪካውያን በተለያዩ ሕዝባዊ ቦታዎች ላይ በዛፍ ተንጠልጥለውና ተገድለው ተገኝተዋል። እነዚህም ያለምንም መረጃ ራስ ማጥፋት ነው በሚል ድምዳሜ ተደርሶባቸዋል፤ ይህ ተቀባይነት የለውም" ብላለች።
(ምንጭ፦ ኒውጀርሲ ሂልስ፣ ቼንጅ ኦርግ፣ ሪቮልት ቲቪ፣ ሞሪስታውን ግሪን፣ፓሪስ ፓኒ ፎከስ፣ ሄቪ፣ ኒውስ ዋን፣ቴክደይ 24፣ የአማኒ የህይወት ታሪክና ከማኅበራዊ ሚዲያዎች የተጠናቀረ)