የናይጄሪያ ተዋጊ አውሮፕላን በሽፍቶች ተመትቶ መውደቁን ጦሩ አሳወቀ

የፎቶው ባለመብት, NAF
በናይጄሪያ የሚገኙ ሽፍቶች ባልተለመደ ሁኔታ የአየር ኃይል አውሮፕላንን መትተው ጥለዋል፡፡
የናይጄሪያው አየር ኃይል እንዳለው ከሆነ አብራሪው በጠላፊዎች ላይ ጥቃቱን ከጨረሰ በኋላ ነው ጥቃቱ የደረሰው ብሏል ፡፡
ጥቃቱ የደረሰው በሰሜናዊ የዛምፋራ እና የካዱና ግዛቶች ድንበር ላይ ነው፡፡
በአካባቢው "ሽፍቶች" በመባል የሚታወቁት ታጣቂዎች በቅርቡ በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ ለተፈጠሩት ጠለፋ ተጠያቂ ናቸው ተብለዋል፡፡
በጠለፋው ተማሪዎች ዒላማ የተደረጉ ሲሆን ከታህሳስ ጀምሮ ከ 1ሺህ በላይ የሚሆኑት ታፍነው ተወስደዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ገንዘብ ተከፍሎ የተለቀቁ ሲሆን የተወሰኑት ግን ተገድለዋል፡፡
በቅርቡ ፕሬዝዳንት ሙሃሙዱ ቡሃሪ በካትሲና፣ ዛምፋራ እና በካዱና ግዛቶች "ወንጀለኛ ሽፍቶችን" ለማስወጣት ወታደራዊ ኃይሉ የሚፈልገውን ሁሉ እንዲያደርግ አዘዋል፡፡
የናይጄሪያ አየር ኃይል ከምድር ኃይል ጋር በመቀናጀት ሽፍቶች ላይ ሌት ተቀን የአየር ጥቃት ማድረሱን ገልጿል፡፡ በዚህ ዘመቻ ነበር እሑድ ዕለት አንድ ተዋጊው አውሮፕላን ተመትቶ የወደቀው።
የናይጄሪያ አየር ኃይል በሰጠው መግለጫ "በእነዚህ ጠንካራ የአየር ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሽፍቶች የተገደሉ ሲሆን በርካታ መደበቂያዎቻቸውም ወድመዋል" ብሏል፡፡
በዚህ ዓመት በርካታ ወታደራዊ አውሮፕላን አደጋዎች ቢኖሩም በታጣቂዎች ተመትቶ እንደወደቀ ሪፖርት ሲደረግ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
በግንቦት የጦር ኃይሉ አዛዥ ሌፍተናንት ጄነራል ኢብራሂም አታሂሩ ከሌሎች 10 መኮንኖች ጋር በአውሮፕላን አደጋ ሲገደሉ በ በናይጄሪያ ድንጋጤ ተፈጥሮ ነበር፡፡
በመጋቢት ደግሞ የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች በስፋት ከሚንቀሳቀሱባቸው አንዱ በሆነው በቦርኖ ግዛት ሌላ አልፋ ጄት ተከሰከሰ፡፡ በጂሃዲስቶች ተመትቶ ስለመውደቁ የሚገልጹ ዘገባዎችን መከላከያው አስተባብሏል።
በየካቲት ወር የታገቱ ተማሪዎችን ለመፈለግ ወደ ኒጀር ግዛት ያቀና የነበረ አንድ ወታደራዊ አውሮፕላን ተከስክሶ በውስጡ የነበሩት ሰባት ሰዎች በሙሉ ህይወታቸው አልፏል፡፡
ሃገሪቱ ኤ -99 ሱፐር የተሰኙ 12 ቱካኖ አውሮፕላኖችን ከአሜሪካ በ 496 ሚሊዮን ዶላር የገዛች ሲሆን ስድስቱን በዚህ ወር የመጀመሪያ ትቀበላለች።












