በአሜሪካ 300 ሺህ ሄክታር በሚሸፍን ደን ላይ ሰደድ እሳት ተነሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ ሶስት መቶ ሺህ ሄክታር በሚሸፍነው ደን ላይ የተከሰተው ሰደድ እሳት በርካቶችን አፈናቀለ።
በአሜሪካ የኦሪገን ግዛት የተቀሰቀሰውና በሀገሪቱ ታሪክ ትልቁ በመንደድ ላይ የሚገኝ ነው የተባለው የእሳት ቃጠሎ ከ300 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን መሬትን የሚሸፍን ሲሆን ሺዎች ለመፈናቀላቸው ምክንያት ሆኗል።
በኦሪገን ታሪክ ታይቶ የማይታወቀውን ይህንን ሰደድ እሳት ለመቆጣጠር ከ200 ሺህ በላይ የአደጋ ተከላካይ ሰራተኞች መሰማራታቸውም ተሰምቷል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት የተቀሰቀሰው ሰደድ እሳቱ ከሎስ አንጀለስ ከተማ የሚልቅ ስፋት ያለው አካባቢን አዳርሷል።
ይህ የኦሪገን እሳት በሙቀት እና በከባድ ነፋሶች ምክንያት በ13 የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ ከተከሰተው ከ80 በላይ ከተቀሰቀሰው እሳት አንዱ ስለመሆኑም ተነግሯል።
የምንጭ ውሃ በሚመረትበት አቅራቡያ ቃጠሎው በመነሳቱ ምክንያት 'ቦትሊግ' የሚል ስያሜ የተሰጠው ሰደድ እሳቱ እስካሁን ቢያንስ ከ 2 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንዲሸሹ አስገድዷቸዋል ፡፡
ከተፈናቀሉት አብዛኛዎቹ በገጠራማ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ ናቸው። በአደጋው ቢያንስ 160 ቤቶች እና ሕንፃዎች ወድመዋል ፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቃዮች ማዕከላት ተከፍቷል።
የእሳቱ ከሸፈነው አከባቢ አንድ አራተኛ የሚሆነው በቁጥጥር ስር መዋሉም ተጠቁሟል።
የብሔራዊ የእሳት አደጋ ደህንነት ማዕከል እንደገለጸው በተያዘው ዓመት በተለይም በምዕራብ ግዛቶች ውስጥ ከ 1.2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የአገሪቱን መሬት ለእሳት አደጋ ተዳርጓል።
ዘንድሮ እስካሁን ድረስ ከ 4000 በላይ የእሳት አደጋዎች በማዕከሉ ተመዝግበዋል ። ይህም ባለፈው ዓመት [እንደ አውሮፓውያኑ 2021] ከተመዘገበው አንጻር እጥፍ ገደማ ነው ፡፡
በካሊፎርኒያ ብቻ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በአምስት እጥፍ የሚበልጥ ሄክታር ተቃጥሏል ፡፡












