ሰሜን ኮሪያ ወጣቶች የደቡብ ኮሪያን መደበኛ ያልሆነ ቋንቋ እንዳይጠቀሙ አስጠነቀቀች

የፎቶው ባለመብት, AFP VIA GETTY IMAGES
የሰሜን ኮሪያ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ወጣቶች የደቡብ ኮሪያ መደበኛ ያልሆነ ቋንቋ እንዳይጠቀሙና የሰሜን ኮሪያን መደበኛ ቋንቋ እንዲገለገሉ አሳሰቡ።
ወጣቶች ከደቡብ ኮሪያ የተቀዱ የፋሽን፣ የፀጉር ስታይል እንዳይጠቀሙ እና ሙዚቃ እንዳያዳምጡ የሰሜን ኮሪያ ይፋዊ ጋዜጦችም አዲስ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር።
ይህ የውጭ ጫናን ለማስቆም ያለመና ከባድ ቅጣት የሚያስከትለው አዲስ ሕግ አካል ነው።
ሕጉን ጥሰው የተገኙም ከእስራት እስከ ሞት ድረስ ሊቀጡ ይችላሉ።
ሮዶንግ ሲንመን ጋዜጣ ወጣቶች የደቡብ ኮሪያን የፖፕ ባህል መከተላቸው የሚያደርስባቸውን ተፅዕኖ አስጠንቅቋል።
"በተዋበና በቀለም ባሸበረቀ ስክሪን ሰርስረው የሚገቡ ርዕዮተ ዓለሞችና እና ባህሎች የጦር መሣሪያ ከያዙ ጠላቶች ይበልጥ አደገኛ ናቸው" ብሏል ጋዜጣው።
ጋዜጣው አክሎም ወጣቶች ኮሪያ ላይ የተመሠረተ የፕዮንግያንግ ቋንቋን በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አሳስቧል።
የውጭ ተፅዕኖው ኪም የሚመሩት የሰሜን ኮሪያ ኮሚዩኒስት ሥርዓት ስጋት ተደርጎ ይታያል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን 'ኬ ፖፕ' [ደቡብ ኮሪያ መሰረቱ የሆነ የሙዚቃ ስልት] የሰሜን ኮሪያ ወጣቶችን አዕምሮ ጨምድዶ የያዘ 'የማይለቅ ካንሰር' ሲሉ መጥራታቸውን ኒዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
ከደቡብ ኮሪያ፣ ከአሜሪካ ወይም ጃፓን ከፍተኛ መጠን ያለው ሙዚቃ ይዞ የተገኘ ማንኛውም ሰው የሞት ቅጣት ይጠብቀዋል። ይህንን ሲመለከት የተያዘ ሰውም የ15 ዓመታት እስር ይተላለፍበታል።
ቅጣቱ ከባድ ቢሆንም ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚገባው የውጭ ጫና ግን አሁንም አልቆመም። ጉዳዩም እጅግ ውስብስብ ሲሆን በዚህ ሳቢያ የታገዱ ሚዲያዎችም በሕገ ወጥ መንገድ መስራታቸውን ቀጥለዋል።
አንዳንድ ሰሜን ኮሪያውያን ተገንጣዮች የደቡብ ኮሪያ ድራማ ማየታቸው አገራቸውን ጥለው ለመውጣታቸው አንዱ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
በሰሜን ኮሪያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ያንግ ሞ ጂን በስዊትዘርላንድ የተማሩት ኪም ጆንግ ኡን "ኬ ፖፕ ወይም የምዕራባውያን ባህል በቀላሉ ወደ ወጣቶች ሊገባ እንደሚችልና በሶሻሊስት ሥርዓት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ያውቃሉ" ሲሉ ለኮሪያ ሄራልድ ተናግረዋል።
"መሪው ይህ ባህልም ለሥርዓቱ ጫና እንደሚሆን ያውቃሉ። ስለዚህም ነው ይህንን ማስቆም የፈለጉት። ኪም ወደፊት የሚመጡ ችግሮችን ለመከላከል እየሞከሩ ነው" ብለዋል ፕሮፌሰሩ።












