በጣና ሃይቅ 13 ያህል መንገደኞችን ያሳፈረች ጀልባ መሰወሯ ተዘገበ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS
በጣና ሃይቅ 13 ያህል ሰዎችን ያሳፈረች ጀልባ መሰወሯን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ 13 የሚደርሱ ሰዎችን አሳፍራ በጣና ኃይቅ ጉዞ የጀመረችው አነስተኛ ጀልባ ሀምሌ 9 ፣ 2013 ዓ.ም ሌሊት ለጉዞ መነሳቷም ተገልጿል።
የወረዳውን ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ቸርነት አስማረን ዋቢ አድርጎ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ጀልባዋ የተሰወረችው አዲሰጌ ድንጌ ተብሎ ከሚጠራ ቀበሌ አባን ላይ ጎጥ ወደ ጎርጎራ ወደብ በሚደረግ ጉዞ ላይ ነው።
ከመነሻው እስከ መዳረሻው ያለው የውሃ ጉዞ የ15 ኪሎሜትር ርቀት አለው ተብሏል።
መንገደኞቹ መዳረሻቸው ጎርጎራ ወደብ የነበረ ቢሆንም በስፍራው እንዳልደረሱ ፖሊስ አረጋግጧል።
መንገደኞቹ ሐምሌ 9፣ 2013 ዓ.ም ሌሊት ድንች ጭነው በጀልባው መሳፈራቸውንም ፖሊስ ከቤተሰቦቻቸው መረጃ መሰብሰቡን ዘገባው ያስረዳል።
የመንገደኞቹ ቁጥር ከ10-13 ያህል ይሆናል የተባለ ሲሆን የአብዛኛዎቹንም ማንነትና የስም ዝርዝራቸውንም ማግኘት ተችሏል ተብሏል።
ፖሊስ፣ ከፖሊስና ከባለሙያዎች የተውጣጣ ሁለት ቡድን አዋቅሮ ከትናንት ጀምሮ ፍለጋ እያደረገ ቢሆንም እስካሁን ምንም አይነት ፍንጭ አልተገኘም ተብሏል።
መንገደኞቹ ጉዟቸውን የጀመሩበት ሰዓት ሌሊት መሆኑም ፍለጋውን አስቸጋሪ አድርጎታል ተብሏል።
ዘገባው አክሎም በዛሬው ዕለት ፍለጋው ቢቀጥልም ወቅቱ ክረምት መሆኑ መንገደኞቹ በማዕበል ተወስደዋል ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ጭነት ጀልባዋ ሰምጣለች በማለት ኮማንደሩ መናገራቸውም ሰፍሯል።
እነዚህን ሰዎች በህይወት የማግኘት እድሉም የጠበበ እንደሆነም ተጠቁሟል።












