ምርጫ 2013፡ ከ840 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ምርጫ አሃዞች ሲቃኙ

ከቀናት በፊት ውጤቱ የተገለጸው የሰኔ 14ቱ ምርጫ፤ ለ436 የፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም ለሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች እና ለሰባት የክልል ምክር ቤቶች የተለያዩ ብዛት ላላቸው መቀመጫዎች ውድድር የተደረገበት ነው።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሦስት የምርጫ ክልሎች የተሰጡ ድምጾች ዳግም እንዲቆጠሩ፣ በሌላ አስር የምርጫ ክልሎች ላይ ደግሞ በድጋሚ ምርጫ እንዲደረግ መወሰኑን ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 3/2013 አስታውቋል።
ከነዚህ ውጪ ባሉ የምርጫ ክልሎች የተሰጡ ድምጾችን ቦርዱ አጽድቋል።
ሰኔ 14 ስለተካሄደው ምርጫ ቁጥሮች ምን ይላሉ?
በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ከ38 ሚሊዮን 200 ሺህ በላይ ዜጎች ለመምረጥ የተመዘገቡ ሲሆን፤ ሰኔ 14 በተካሄደው ምርጫ ወደ 33, 900, 070 ሺህ የሚጠጉ መራጮች ድምጽ መስጠታቸውን የቦርዱ መረጃ ያሳያል።
እንደ መረጃው፤ በክልሎች የምርጫ ካርድ ከወሰዱ ዜጎች አንጻር በዕለቱ [ሰኔ 14] ከፍተኛ ድምጽ ሰጪዎች የተሳተፉት በሲዳማ ክልል ነው። በክልሉ የተመዘገቡት መራጮች በሙሉ ድምጻቸውን ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የምርጫ ካርድ ከወሰዱት 1 መቶ 62 ሺህ 600 መራጮች ውስጥ ድምጽ የሰጡት 89 ሺህ 4 መቶ 34 ያህሉ [55 በመቶ] ናቸው። ከሌሎች ክልሎች አንጻር ዝቅተኛ የመራጮች ቁጥር የተመዘገበበት ነው።
ቦርዱ መራጮችን በ50 ሺህ የምርጫ ጣቢያ ለመመዝገብ አቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ መራጮች የተመዘገቡት ግን በ42 ሺህ 580 ጣቢያዎች ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
ሰኔ 14 የተካሄደው የመጀመሪያው ዙር ምርጫ በ70 የምርጫ ክልሎች [የትግራይን ሳይጨምር] በተለያዩ ምክንያቶች ድምጽ አለመሰጠቱ የተጠቆመ ሲሆን በተቀሩት ድምጽ ተሰጥቷል።
በምርጫው ዕለትና ከዚያ በኋላ ባሉ ቀናት በ165 የምርጫ ክልሎች ላይ ከ30 ፓርቲዎችና ከሰባት የግል ዕጩዎች አቤቱታ ቀርቧል።
ቦርዱም አቤቱታዎችን ተመልክቶ "በዋናነት አስተዳደራዊ እርምጃን፣ ውጤት ስረዛንና ድጋሚ ምርጫን" መወሰኑን የምርጫውን አፈጻጸም እና ውጤት ሪፓርት ያቀረቡት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ውብሸት ገለጻ "ቦርዱ ውጤት ሊቀይሩ የሚችሉ የአሠራር ግድፈቶችን መርምሮ" በሦስት የምርጫ ክልሎች ላይ በድጋሚ ቆጠራ እንዲካሄድ ወስኗል።
ከዚህ ውስጥ ሦስቱ ለፌዴራሉ ፓርላማ የተደረጉ ውድድሮች ናቸው። "የታዛቢዎችና የወኪሎች መከልከል [ምርጫ ጣቢያ እንዳይገኙ]፣ የምርጫ ሂደቱ በአካባቢው መስተዳድር መዋቅር ተጽዕኖ ሥር መውደቁ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው መራጭ እንዳይመረጥ መደረጉን" ተከትሎ በአማራ፣ በደቡብ፣ በአፋር እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ በሚገኙ ስምንት የምርጫ ክልሎች ምርጫው በድጋሚ እንደሚደረግ ተገልጿል።
በድጋሚ ድምጽ ከሚሰጥባቸው የምርጫ ክልሎች ውጪ ጳግሜ 1/ 2013 ዓ.ም. በ64 የምርጫ ክልሎች ከ5 ሚሊዮን በላይ መራጮች ይሳተፋሉ።
ምርጫው 9 ሺህ 500 ዕጩዎች እንዳሉትና 148ቱ የግል ተወዳዳሪዎች እንደሆኑ ገልጸዋል። ከነዚህ ውስጥ ወደ 1 ሺህ 900 የሚጠጉት እንስት ሲሆኑ፤ አጠቃላይ ዕጩዎቹ በ49 አይነት የምርጫ ምልክቶች የተወከሉ ናቸው።
ለምርጫ ቁሳቁሶች 845 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገ የጠቀሱት አቶ ውብሸት፤ የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን በሁለት አገራት ለማሳተም 9 ሚሊዮን ዶላር [በወቅታዊ ምንዛሬ 395 ሚሊዮን ብር] ወጪ መደረጉን ተናግረዋል።
ይህ ገንዘብ ለቁሳቁስ ከወጣው ገንዘብ ጋር ተጨማሪ ይሁን አይሁን የጠቀሱት ነገር የለም።
ሰኔ 14/ 2013 ዓ.ም. የተከናወነውን ምርጫ 152 ሺህ 700 አስፈጻሚዎች ተሰማርተው አስፈጽመዋል።
ለመራጮች ትምህርት ለመስጠት 169 የሲቪል ማኅበራት ፍቃድ የወሰዱ ሲሆን፤ 46 ማኅበራት ደግሞ ምርጫ ለመታዘብ ፍቃድ አግኝተው 44 ሺህ 560 ታዛቢዎች በተለያዩ ጣቢያዎች መሰማራታቸው ተገልጿል።
ምርጫውን ለመዘገብ ቢቢሲን ጨምሮ 70 መገናኛ ብዙኃን፤ 1 ሺህ 971 ዘጋቢዎችን የላኩ ሲሆን፤ 160ዎቹ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን የወከሉ ጋዜጠኞች ነበሩ።

ሰኔ 14 የተደረገው ምርጫ በጨረፍታ
- ውድድሩ ለ445 የፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ የተደረገ ነው
- በ10 የምርጫ ክልል ድጋሚ ቆጠራ፣ በ10 የምርጫ ክልሎች ደግሞ በድጋሚ ምርጫ ይደረጋል
- ሰኔ 14/2013 ዓ. ም. [ከትግራይ ክልል ውጪ] በ70 የምርጫ ክልሎች ድምጽ አልተሰጠም
- 33 ሚሊዮን 9 መቶ 70 ሺህ የሚጠጉ መራጮች ድምጽ ሰጥተዋል
- ድምጽ አሰጣጥ ላይ በ165 የምርጫ ክልሎች ላይ ከ30 ፓርቲዎችና ከ7 የግል ዕጩዎች አቤቱታ ቀርቧል
- ለምርጫው ቁሳቁሶች 845 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል
- ለድምጽ መስጫ ወረቀቶችን ህትመት 9 ሚሊዮን ዶላር [በወቅታዊ ምንዛሬ 395 ሚሊዮን ብር] ወጪ ተደርጓል
- ምርጫው በ152 ሺህ 700 አስፈጻሚዎች የተከናወነ ነው
- 46 የአገር ውስጥ የሲቪል ማኅበራት በምርጫው ዕለት 44 ሺህ 560 ታዛቢዎች አሰማርተዋል
- ምርጫውን ከ70 መገናኛ ብዙኃን የተወጣጡ 1 ሺህ 971 ጋዜጠኞች ዘግበውታል
- በምርጫው ለፌዴራል ፓርላማ ብልጽግና ፓርቲ 410 መቀመጫ በማግኘት መንግሥት መመሥረት የሚስችለውን ድምጽ አግኝቷል
የሰኔ 14 ምርጫ ውጤት
በምርጫው ገዢው ብልጽግና ፓርቱ ቀጣዩን የፌደራል መንግሥት ለመመስረት ከሚያችለው 274 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ በእጅጉ የበለጠ በማግኘት አሸንፏል።
በዚህም መሠረት ብልጽግና ምርጫው በተካሄደባቸው ሁሉም ክልሎች ከፍተኛውን ውክልና በማግኘት 410 መቀመጫዎችን ለማሸነፍ ችሏል።
በምርጫው በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕጩዎችን አቅርበው የተወዳደሩ ቢሆንም ከሦስቱ በስተቀር በፌደራሉ ምክር ቤት መቀመጫ ያገኘ የለም።
ሦስቱም ቢሆኑ የጎላ የሆነ ውክልና ያላገኙ ሲሆን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አምስት፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አራት እና የጌዲዮ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሁለት መቀመጫን አግኝተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በግል ከተወዳደሩ 125 ዕጩዎች መካከል አንድ ከአዲስ አበባ፣ ሦስት ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርጠዋል።

















