ሦስቱ አገራት በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የተፈራረሙት የመርሆዎች ስምምነት ይዘት ምንድነው?

የህዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በሚያደርጓቸው ድርድሮች ላይ የመርሆዎች ስምምነትን ብዙ ጊዜ ይጠቅሳሉ።

በተለይም የሕዳሴ ግድብ ሙሌትም ጋር ተያይዞ ግብጽና ሱዳን የሕዳሴ ግድብ የትብብር መግለጫ ስምምነትን (የመርሆዎችን ስምምነት) በመጥቀስም ሲሟገቱ ይሰማል።

ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን ከስድስት ዓመታት በፊት መጋቢት 14/2007 ዓ.ም ላይ የመርሆዎች ስምምነት ላይ ፊርማቸውን አኑረው ነበር።

ይህን ስምምነት የፈረሙት በኢትዮጵያ በኩል የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሲሆኑ በግብጽ በኩል ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ እንዲሁም የቀድሞ የሱዳን ፕሬዝደንት ኦማር አልበሽር ፊርማቸውን አኑረዋል።

በሦስቱ አገራት እድገት ከፍተኛ ሚና ያለው ድንበር ተሻገሪ የሆነው የናይል ወንዝን የመጠቀም ፍላጎት መጨመሩን መሠረት በማድረግ ሦስቱ አገራት የወንዙ አጠቃቀም ላይ የመርሆች ስምምነቱ ስለማድረጋቸው በስምምነቱ መግቢያ ላይ ሰፍሯል።

የትብብር መርህ

ሦስቱ አገራት የጋራ ተጠቃሚነት፣ ሁሉን አሸናፊ በሚያደርግ፣ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን መሠረት በማድረግ የላይኛው እና የታችኛው የተፋሰስ አገራት የውሃ ፍላጎታቸውን በመረዳት የትብብር ለማድረግ በመርህ ላይ የተመሠረተ በመሆኑን በተፈራረሙት የመርሆች ስምምነት ላይ ተመልክቷል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዓላማ ኃይል ማመንጨት፣ ለኢኮኖሚ እድገት ድርሻ ማበርከት እና ዘላቂ እና ንፁህ ኃይል በማመንጨት ድንበር ተሻጋሪ የሆነ ቀጠናዊ ትብብር ማምጣት

ከፍተኛ ጉዳት ያለማድረስ መርህ

ሦስቱ አገራት በደረሱት ስምምነት መሠረት የትኛውም አገር የናይል ወንዝን ሲጠቀም በሌሎች የተፋሰሱ አገራት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አለማስከተሉን ማረጋገጥ አለበት።

ይሁን እንጂ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ሲረጋገጥ፤ ወንዙን በመጠቀሙ ጉዳት ያስከተለው አገር ጉዳት ከደረሰበት አገር ጋር በመወያየት ችግሩን ለመቅረፍ አለበት አስፈላጊ ከሆነም በካሳ ጉዳይ ሊነጋገሩ ይችላሉ።

የመርሆች ስምምነቱ አንቀጽ 5 ስለ ግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት እና አሰራርን በተመለከተ ስለሚደረግ ትብብር ያትታል።

በግድቡ ግንባታ የተለያዩ ደረጃዎች ላይ የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ፓናል ምክረ ሃሳብን መተግበር እና የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ የመጨረሻ ሪፖርትን ማክበር የሚል ይገኝበታል።

በዚህ የምርህ ስምምነት ላይ ሕዳሴ ግድቡ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር የታችኛው የተፋሰስ አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ይላል።

የመረጃ ልውውጥ መርህ

የስምምነቱ አንቀጽ ሰባት ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ለሚያካሂዳቸው ጥናቶች በፍጥነት በመልካም መንፈስ መረጃዎችን ያቀርባሉ ይላል።

የግድቡ ደህንነት በተመለከተ ኢትዮጵያ በግድቡ ግንባታው ወቅት የግድቡን ደህንነት ለማረጋገጥ የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ፓናል ሪፖርት መተግበር ይጠበቅባታል።

ግጭት እና አለመስማማት መፍታትን በተመለከተ፤ የዚህ ስምምነት አተረጓጎምም ወይም አፈጻጸም ተከትሎ የሚከሰት አለመግባባት በመልካም መርህ ላይ ተመስርቶ በውይይት ወይም በድርድር የሚፈታ ይሆናል ይላል።

ይሁን እንጂ ሦስቱ አካላት አለመግባባቱን በምክክር ወይም በድርድር መፍታት ከተሳናቸው በጋራ ዕርቅ፣ ማስታረቅ ወይም ለአገራቱ ርዕሰ ብሔራን ጉዳዩን ሊወስዱት ይችላሉ።

ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እየተከናወነ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን መጋቢት 14፣ 2007 ዓ.ም በመሪዎቻቸው አማካኝነት በሱዳን፣ ካርቱም በፈረሙት የመርሕ ስምምነት መሠረት እንደሆነ ተገልጿል።