ሳዑዲ 'ከመስጅድ የሚወጣ ድምፅ ይቀነስ ማለቴ ትክክል ነው' እያለች ነው

የመካ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት ከመስጅድ የሚወጣ ድምፅ መጠንን መገደባችን ትክክል ነው እያሉ ነው።

የሃገሪቱ እስላማዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ባለፈው ሳምንት የመስጅድ ድምፅ ማጉያዎች ድምፃቸውን ከአንድ ሶስተኛ በላይ ከፍ እንዳያደርጉ ሲሉ አውጆ ነበር።

የእስላማዊ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አብዱላቲፍ አል-ሼይኽ ይህን ያደረግነው ከሕዝብ በቀረበልን ቅሬታ አማካይነት ነው ብለዋል።

ነገር ግን አብዛኛው ሕዝቧ ወግ አጥባቂ የእስልምና እምነት ተከታይ በሆነባት ሃገር ይህ አዲሱ መመሪያ ቁጣ ቀስቅሷል።

በተለይ ደግሞ ማሕበራዊ ድር አምባ ተጠቃሚዎች አዲሱን የመንግሥት አዋጅ በፅኑ ተቃውመውታል።

ሰዎች በምግብ ቤቶችና በካፌዎች ከፍ ያለ ድምፅ ያለው ሙዚቃ ይከልከል ሲሉ 'ሃሽታግ' በመጠቀም በማሕበራዊ ድር አምባዎች ድምፃቸውን አሰምተዋል።

ሚኒስትር ሼይኽ እንዳሉት ቅሬታ ካቀረቡት መካከል ልጅ ያላቸው ወላጆች ሲሆኑ ልጆቻችን እንቅልፍ መተኛት አልቻሉም ሲሉ አማረዋል ብለዋል።

በሃገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈ መልዕክት ላይ ነው ሚኒስትሩ ፀሎት ማድረግ የሚሹ ሰዎች የኢማሞችን ጥሪ መጠበቅ የለባቸውም ያሉት።

በበይነ መረብ አማካይነት የመንግሥትን አዲሱን መመሪያ የተቃወሙ ሰዎችን "የሳዑዲ አገዛዝ ጠላቶች" ናቸው፤ "የሕዝቡን ሐሳብ ለማደበላለቅ እየተንቀሳቀሱም ነው" ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።

ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን ሃገራቸው ሳዑዲ አረቢያ 'ሊበራል' እንድትሆን እና ኃይማኖት በሕዝባዊ አኗኗር ላይ ያለው ተፅዕኖ እንዲቀንስ ጥረት እያደረጉ ባለበት ወቅት ነው ይህ መመሪያ የወጣው።

ሳዑዲ አረቢያ በቅርቡ የተለያዩ ገደቦችን ማንሳት መጀመሯ ይታወሳል።

ከእነዚህም መካከል አንደኛው ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩ መፍቀድ ነው።

ነገር ግን አልጋ ወራሹ ሐሳብን በነፃነት መግለፅን በተመለከተ ጠበቅ ያሉ እርምጃዎች እየወሰዱ ነው ተብለው ይወቀሳሉ።

በርካታ የንጉሡ ወቃሾችና ከሳሾች እሥር ቤት ውስጥ ይገኛሉ።