የአርባ ምንጭ ታራሚ ወደ ሰላሳ ሚስማሮችና ብረታ ብረቶች በቀዶ ህክምና ተወገዱለት

ከታራሚው የወጡት ሚስማሮች

የፎቶው ባለመብት, South Radio and Television Agency

በአርባ ምንጭ የሚገኝ ታራሚ ወደ ሰላሳ የሚጠጉ ሚስማሮች፣ ብረታ ብረት፣ እስክርቢቶዎችና ሌሎች ባዕድ ቁሶች በቀዶ ህክምና እንደተወገዱለት ቢቢሲ ከአርባምንጭ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ተመስገን ተሾመ መረዳት ችሏል።

ታራሚው ሰባት አመት ተፈርዶበት በእስር ላይ የሚገኝ ሲሆን በማረሚያ ቤት ቆይታው የአዕምሮ ህመም እንዳለበት ተረጋግጦ ህክምና እየወሰደ እንደነበር አቶ ተመስገን ያስረዳሉ።

ግለሰቡ በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ግንቦት 17፣ 2013 ዓ.ም ሆዴን አመመኝ ብሎ ወደ አርባ ምንጭ ሆስፒታል የመጣ ሲሆን አቶ ተመስገን ከፍተኛ ህመም ላይ እንደነበር ይናገራሉ።

የህክምና ባለሙያዎች በርካታ ጥያቄዎች ሲያቀርቡለት ሚስማሮችን ይውጥ እንደነበር ምላሽ ሰጥቷል።

የታራሚውን ቃል በመስማት በአስቸኳይ ራጅ (ኤክስሬይ) እንዲነሳ የተደረገ ሲሆን ውጤቱም ባዕድ ነገሮች ሆዱ፣ አንጀቱ ውስጥ መኖራቸውን አሳየ።

አቶ ተመስገን እንደሚሉት ባዕድ ነገሮቹ ከመኖራቸውም በላይ ተባብሶ አንጀቱ ሙሉ በሙሉ እየዘጋ መሆኑ ከታዬ በኋላ ቀዶ ህክምና እንዲገባ ተደርጓል።

ቀዶ ህክምናው በሚካሄድበት ወቅት ውስጡ ላይ ጨጓራውን ጨምሮ በተለይም የአንጀቱን ክፍል እንደበሳሳውና በጥንቃቄ ከጨጓራውም ከአንጀቱም መለቀም እንደነበረበት አቶ ተመስገን ይገልጻሉ።

በቀዶም ህክምናውም ወደ ሰላሳ የሚሆኑ በአብዛኛው ሚስማሮች፣ አራት የሚሆኑ እስክርቢቶዎች፣ መርፌ፣ የተለያዩ ክሮች፣ ከሚስማርም ወፈር ያለ ብረትም ሆድ እቃው ውስጥ ተገኝቷል።

በቀዶ ህክምናም ከወጣለት በኋላ ኤክስሬይ እንዲነሳ እንደገና የተደረገ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ባዕድ ነገሮቹ መውጣታቸውንም የህክምና ባለሙያዎቹ ማረጋገጥ ችለዋል።

ከቀዶ ህክምናው በኋላ ታማሚው በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ቢቢሲ አቶ ተመስገንን የጠዬቀ ሲሆን "አሁን ያለበት ሁኔታ በጣም በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለው ምናልባት ቀጣይ የሆነ ምርመራ ሊያስፈልግ ይችላል። ምናልባት እየዋጠ የነበረው በጣም ሹልና ስለታም ቁሶች ስለነበር በርካታ የሰውነቱን ክፍሎች ጎድቶ ሊሆን ይችላል።"ብለዋል

በተለይም ጉሮሮውና ጨጓራ አካባቢ ላይ ቁስለት ፈጥሮ ከነበር ሌሎች ምርመራዎች እንደሚያስፈልግ አፅንኦት የሰጡ ሲሆን ካገገመም በኋላ ሌሎች ተጨማሪ ምርመራዎች እንደሚደረግም ተናግረዋል።

በተጨማሪ ደግሞ የስነ ልቦና ህክምናም እንደሚያስፈልገው ያስረዳሉ።

ኃላፊው ለቢቢሲ እንደገለፁት ታራሚው ማረሚያ ቤት ከመግባቱ በፊት የአዕምሮ ህመም ታሪክ እንደሌለው ነው።

ማረሚያ ቤት ከገባ በኋላ የአዕምሮ ህመምተኛ መሆኑ የታወቀ ሲሆን ከዚህ በፊት ምንም ችግር እንደሌለበት ስራ አስኪያጁ የግለሰቡን ጓደኛ ዋቢ አድርገው ተናግረዋል።